የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቶማስ ሐዋርያ

 “ነገር ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ኢየሱስ በመጣ ጊዜ ከእነርሱ ጋር አልነበረም ። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርቱ። ጌታን አይተነዋል አሉት ። እርሱ ግን፦ የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው ።” ዮሐ. 20፡24-25
በሦስቱ ወንጌላት ከሐዋርያት ጋር ስሙ ተጠቅሶ የምናገኘው በዮሐንስ ወንጌል ግን ጥቂት ጠባዩና ድርጊቱ የተጻፈለት ሐዋርያ ቶማስ ነው ። ቶማስ በአረማይክ መጠሪያ ስሙ ሲሆን በግሪኩ ዲዲሞስ ተብሏል ። የሁለቱም ፍቺ “መንታ” ማለት ነው ። አይሁድ በዓለም ሁሉ ተበትነው ይኖሩ ነበርና አንዱን ስም በዕብራይስጥና በግሪክ ቋንቋ መጥራት ልማድ አድርገውት ነበር ። ግሪክ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሲሆን አረማይክ ወይም ዕብራይስጥ ደግሞ የአገር ቤት ቋንቋ ነው ። ኬፋ በአረማይክ ሲሆን በግሪኩ ጴጥሮስ ተብሏል ። የሁለቱም ትርጉም “ዓለት” ማለት ነው ። ጳውሎስ የሮማዊ ስሙ ሲሆን ሳውል ደግሞ የዕብራይስጥ ስሙ ነው ። እንዲሁ በአረማይክ “ቶማስ” ሲባል በግሪኩ “ዲዲሞስ” ተብሏል ።

ቶማስ አስደናቂ ጠባያት የታዩበት ሐዋርያ ነው ። እንደ ግትርና እንደ ተጠራጣሪ ቢታይም እውነተኛ ማንነቱ ግን እንደዚህ አይደለም ። አንድ ነገርን ቶሎ የማይቀበሉና ከተቀበሉ በኋላ የማይለቁ ሰዎች አሉ ። ቶማስ አንድን ነገር ለመቀበል በቂ እውቀት የሚፈልግ ሲሆን ላመነበት ነገርም ቆራጥ የሆነ ሐዋርያ ነው ። ቶማስ ክርስቶስን መከተል ሞትን እንደሚያስከትል አውቆ ዋጋ ተምኖ የሚጓዝ ከክርስቶስ ጋር ለመሞትም ዝግጁነቱን የገለጠ ፣ ደፍሮ ሌሎችንም በማደፋፈር የታወቀ ሐዋርያ ነው ። ሕይወቱንም አስቀምጦ የተከተለ ነው ። ጌታ ወደ አልዓዛር መቃብር እንደሚሄድ በተናገረ ጊዜ፡- ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት፡- ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ። /ዮሐ. 11፡16 ።/ ይህ ጉዞ ታላቅ መከራ እንዳለበት ሐዋርያው ቶማስ ተገንዝቦአል ። ታላላቅ ተአምራቶች ታላላቅ ፈተናዎችን ያሥነሣሉ ። ጌታችን ከዚህ ቀጥሎ ወደ መስቀል የሄደው በሳምንቱ ነው ። ቶማስ ስለ ክንውኖች ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ ስለሚመጡ ነገሮች የሚያይና የሚመዝን ነው ። ምንም እንኳ በጌታ የመከራ ሰዓት አብሮ ለመቆም ባይችልም እውነተኛ የልቡ አሳብ ግን ከክርስቶስ ጋር መሞት ነበረ ። በዚህም አሳብና ኃይል የሚባሉ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን ። ሰው ለመቀደስም ለክርስቶስ ለመሞትም አሳብ አለው ፣ ቦታው ላይ ሲደርስ ግን ኃይል ያጣል ። አሳብ ከውለታ የማይቆጠረው በሰው ዓለም ነው ፣ እግዚአብሔር ግን የልብንም አሳብ ያያል ፣ ከውለታ ይቆጥራል ። ቶማስ ልቡ ከክርስቶስ ጋር እንደሚሞት እርግጠኛ ነው ። በራሳችን ላይ ግን የምናውቀውና የማናውቀው ማንነት አለ ። ለዓርብ ዕለት ባይገኝም በሕንድና በፋርስ ወንጌል ሰብኮ በ72 ዓ.ም. በሰማዕትነት አርፏል ። እስክንበረታና እስክናድግ እግዚአብሔር ይጠብቀናል ።
ቶማስ ያልገባውን ነገር እንደ ገባው ለመምሰል የሚሞክር ሰው አልነበረም ። አንድ ነገር ካልገባው አልገባኝም ለማለት አያፍርም ። በዚህም ምክንያት ወደ ትክክለኛ እውቀት ይደርሳል ። ጌታችን “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” በማለት የተናገረው ተወዳጅ ንግግሩ ለቶማስ ጥያቄ የተሰጠ መልስ ነው ። ጌታችን፡- ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ”ብሎ ሲናገር ቶማስም፡- ጌታ ሆይ ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም ፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን ? አለው ።” /ዮሐ. 14 ፡ 4-5/ ሌሎቹ ሐዋርያት የጌታን ንግግር አልተረዱት ይሆናል ፣ እንደ ገባቸው ሁነው ዝም ሲሉ ቶማስ ግን አልገባኝም ለማለት የሚያፍር ሰው አልነበረም ። በእውቀት የሚያድጉ ሰዎች እንዴት በሰው ፊት አልገባኝም እላለሁ ብለው የሚኮፈሱ ሳይሆኑ በትሕትና አልተረዳሁም የሚሉ ሰዎች ናቸው ። የማወቅ መሠረቱ አለማወቅን መቀበል ነው ። ቶማስ ጥያቄ ልፍጠርና ርእስ ልሁን ፣ ሌላውን የማስጮህ ምክንያት ልሁን የሚል ፣ የአትርሱኝ ስእለት ያለበት አይደለም ። አንዳንድ ሰዎች ቆባቸውን ቀደው የሚሰፉ ፣ ያልበላቸውን ነገር የሚያክኩ ፣ መልሱን ደርሰውበት ጥያቄ የሚጠይቁ ፣ የአእምሮ ጡንቻቸውን ለማፍታታት ክርክር የሚፈጥሩ ፣ በሰላም የተቀመጠውን ካላስጮኹ ደስ የማይላቸው ፣ የተረሱ ሲመስላቸው መምህራንን በአጉል ጥያቄ የሚያበሳጩ ናቸው ። ቶማስ ግን ለመረዳት ብቻ የሚጠይቅ ፣ የተማሪነት ቦታውን ያልረሳ ደገኛ ሰው ነው ።
እንኳን ከክርስቶስ ከመምህራንም የምንጠቀመው ዝቅ ስንል ነው ። እየበሰልን ስንመጣ ደስ ከሚያሰኘን ንግግር አንዱ “አልገባኝም” የሚለው ንግግር ነው ።
አውቀን ከጨረስን የምንኖርበት ምክንያት የለንም ። ገና የማናውቀው ነገር መኖሩ ሕይወትን እንግዳ ያደርጋታል ።
ቶማስን የምናገኘው ጌታችን ከሙታን ከተነሣ በኋላ ነው ። ጌታን ያዩት ደቀ መዛሙርት በነገሩት ጊዜ ካላየሁ ካልዳሰስሁ አላምንም አለ ። ከሐዋርያት የጌታን ትንሣኤ ዘግይቶ የተቀበለ ቶማስ ነው ። የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው።” ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቶማስ ንግግር መሠረት ቅዱሳን ክርስቶስን የሚለዩት በችንካሩ ምልክት ነው ። ለአንድ ቅዱስ ሰይጣን “ክርስቶስ ነኝ” ብሎ ተገለጠለት ። ያ ቅዱስ ግን፡ “የችንካሩ ምልክት የት አለ?” ቢለው ሰይጣን እንደ ጉም ተነነ ፣ እንደ ጢስ በነነ ። ጌታችን ቶማስ እንደሚፈልገው ተገልጦ እንዲያምነው አደረገ ። በርግጥም ትንሣኤው ምትሐት ሳይሆን እውነት መሆኑን ፣ የተነሣው የሞተው ክርስቶስ መሆኑን አወቀ ። ቀጥሎ ያለው ንባብ ይህን ይገልጥልናል ።
“ከስምንት ቀን በኋላም ደቀ መዛሙርቱ ደግመው በውስጥ ነበሩ ፥ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበረ ። ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።” ሰላም ለእናንተ ይሁን የሚለው ማዕበልን የሚገሥጽ ቃል ነው ። እኛ ዳግም ትንሣኤ የምንለው ይህን ቀን ነው ። ጌታችን ለቶማስ ትንሣኤውን የገለጠበት ቀን ነው ። በተዘጋው ደጅ መግባቱ አምላክነቱን ሲያሳይ የተወጋ ጎኑን ማሳየቱ የሞተበትን ሥጋ ጥሎ እንዳልተነሣ የሚያሳይ ነው ። አምላክ በሥጋ ባይሞት ድኅነት አይኖርም ነበር ። በፍጡር ሞት ዓለም አይድንምና ። በተዘጋው በር ሲገባ በተዘጋው የቶማስ ልብም ለመግባት ነው ። ጌታችን ቶማስ እንዲያምነው አገዘው እንጂ አልፈረደበትም ።
“ከዚያም በኋላ ቶማስን፡- ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ ፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው ፤ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው ።” ጌታችን ጎኑ እንዲዳሰስ ፣ የተቸነከሩ እጅና እግሮቹ እንዲታዩ ፈቀደ ። ትንሣኤውን ካላመኑ ሐዋርያት መሆን አይችሉምና ። እኛም ትንሣኤውንም ካላመንን ክርስቲያን መሆን አይቻለንም ። በመጨረሻው ቀን ሲመጣም የተቸነከሩ እጆቹንና እግሮቹን የተወጋ ጎኑን እያሳየ ይመጣል ። ችንካሩ የፍቅር ፊደል ነው ። ይህን ፊደል አንብቦ በክርስቶስ ያላመነ ይፈረድበታል ። ቶማስ ግን አመነ ። ጌታዬ አምላኬም ብሎ መለሰለት።” ጌትነቱንና አምላክነቱን አመነ ። ጌታችንም ጌታና አምላክ ነውና ተቀበለው ።
ደጆች ቢዘጉም ፣ ለማመን ልባችን እየከበደ ቢመጣም ፣ ጌታ ሆይ አምንህ ዘንድ እርዳኝ እንበለው ። እርሱ ራሱን በመግለጥ የታወቀ አምላክ ነው ።
ጸሎት
ጌታዬ ሆይ እያየሁህ አንተን ማየት ፣ እየዳሰስኩህ አምላኬ ማለት አልቻልኩም ። የማምነው በዓለም ወሬ እንጂ በወንጌል አይደለም ። ራሴን አይና በእኔ አቅም አንተን እለካለሁ ። እባክህን በልቶ ካጅ እንዳልሆን እማጸንሃለሁ ። አለማመኔን አንተን በማመን ለውጠው ። ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ /11
ግንቦት 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
https://t.me/Nolawii
እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

ያጋሩ