መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ችግሩ ከማን ነው?

የትምህርቱ ርዕስ | ችግሩ ከማን ነው?

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ                 
                                                           ሰኞ መስከረም 19 2007 ዓ.ም.
ትዳራቸውን ፈትተው፣ ልጆቻቸውን በትነው፣ ጐረቤት አሳዝነው፣ ለአገር ዕዳ አኑረው፣ ለሕሊናቸው ፀፀት አትርፈው ያለፉ፣ ከባልንጀራቸው ተቆራርጠው፣ ከሥራ ባልደረባቸው ተሟግተው፣ ከእውነት ተጣልተው፣ ከአብሮነት ብቸኝነትን መርጠው፣ ከመግባባት በልዩነት ውስጥ መኖርን  አጽድቀው ክፉ ምርጫቸውን እያገለገሉ ብዙዎች አልፈዋል፡፡ ዛሬም ከመወያየት መነቃቀፍን ወግ አድርገው፣ እኛ ካልገባን ውሸት፣ እኛን ካልጣመን መናኛ፣ እኛን ካልሞቀን ብርድ፣ ከእኛ ካልተስማማ እርም የምናደርገው ነገር የበዛ በመሆኑ “ችግሩ ከማን ነው?” ብሎ ራስን መጠየቅ ግድ ይሆናል፡፡ ምን ያህል ጊዜ በጊዜው የነበረው ሁኔታ ካለፈ፣ የደፈረሰው ከጠራ፣ ግብግቡ ካበቃ፣ ከድንፋታም ከሰከንን በኋላ ችግሩ በዚያኛው ወገን ሳይሆን በእኛ ወገን እንዳለ ተረዳን? ካፈርኩ አይመልሰኝ ብለንስ በጀመርነው መንገድ ምን ያህል ጊዜ ዘለቅን? ከጉዞ በፊት ቆም ማለት፣ ከውሳኔ በፊት ዙሪያ  ገባውን ማስተዋል፣ ከመናገርም በፊት ከልብ ጋር መማከር ትውልድንም አገርንም ከኪሳራ ያድናል፡፡ በመሰለኝና በይሆናል እንደ መነዳት ያለ መሃይምነትም የለምና ችግሩ ከማን ነው? ማለትን መልመድ ይኖርብናል፡፡
ለዚህ ጽሑፍ እንደ መነሻነት ያገለገለን በማቴ. 13፥1-9 ያለው የዘሪው ምሳሌ ነው፡፡ ጌታ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ላልተሰጣቸው፣ የመንፈስ ዓይናቸው፣ የልብ ጆሯቸው ለማያይና ለማያስተውሉ በምሳሌ ይናገር ነበር፡፡ በዚህ ኪዳን ውስጥ ከተናገራቸው ምሳሌዎች መካከል ከቃሉ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ከሚተረጐሙት አንዱ ይህ ክፍል ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የሚለውን ለመስማት ከእርሱም አሳብ ጋር ብቻ ለመስማማት በወሰነ አቋም ውስጥ ሆነን ክፍሉን በጸሎት ብናጠናው የምንረዳቸው ቁም ነገሮች የተትረፈረፉ ናቸው፡፡ ዘሪ ሊዘራ ወጣ፡፡ በዘራም ጊዜ አንዱ በመንገድ ዳር፣ ሌላው በጭንጫ፣ አንዱ በእሾህ መካከል ሌላው ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ወደቀ፡፡ 


በዚህ ክፍል ውስጥ አራት ዓይነት የቦታ ሁኔታ እንጂ አራት የዘር ዓይነት አናስተውልም፡፡ አንዱ ጤፍ ሌላው በቆሎ ደግሞ ሌላው ስንዴ የሆነበት ሁኔታም የለም፡፡ ያው አንድ ዓይነት ዘር በአራት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ አረፈ፡፡ ውጤቱም ግልጽ ነው! ወፎች የለቀሙት፣ ፀሐይ ያጠወለገው፣ እሾህ ያነቀው የመጨረሻውም እንደ መቶ ባለ ፍሬ የተገለጠ ሆነ፡፡ ከዚህ ቦኋላ የመንገዱ ዳር ዘሩን አልያም ዘሪውን ምን ሊለው ይችላል? ወይስ ጭንጫው ምን ዓይነት ተቃውሞ ሊያሰማ ይቻለዋል? የእሾህስ አቤቱታ ምን ሊመስል ይችላል? ዘሪው ታማኝ፣ ዘሩም ፍጹም ነውና፡፡ የሰማይና የምድር እልፈትን ያቀለለ፣ የማር ወለላን ጣፋጭነትም ያስናቀ፣ ከወጣ ሳያደርግ፣ ከተነገረ ሳይፈጸም የማይመለስ ራሱ ትእዛዝ ራሱ ፈጻሚ፣ ራሱ ምክር ራሱ አቅኒ፣ ራሱ ተግሣጽ ራሱ ቀጪ የሆነ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና በመምጣት ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ ከሆኑ ድቅድቁ ጨለማ በክርስቶስ ደም ተረግጦላቸው ወደሚደነቅ ብርሃን ከፍ ካሉ በኋላ እንደ ገና ወደ ኋላ በመመለስ የጌታን ፍቅር ቀምሰው እንዳልቀመሰ፣ የእግዚአብሔርን ክብር አይተው እንዳላየ፣ ለዘላለም የተቀጠረላቸውን ዕረፍት የቀረላቸውን ተስፋ አስተውለው እንዳላስተዋለ መኖር ለጀመሩ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጉመው ጭንቅ ነው” (ዕብ. 5፥11) ይላል፡፡ በዚህ ክፍል ሐዋርያው የጽድቅን ቃል ለማወቅ የለመደ ልቡና የሌላቸውን ክርስቲያኖች ይገስጻል፡፡ በክርስትና ውስጥ እንዳስቆጠሩት ዘመን፣ በሕይወታቸው እንደ ፈሰሰው የቃሉ ጠል አስተማሪዎች ሊሆኑ ሲገባቸው ዳሩ ግን የሕፃንነት ትምህርት በሚያስፈልገው ማንነት ገና እንዳሉ በመጠቆም የቃሉን ወተት ያዝላቸዋል፡፡ ስለ አዳምና ሔዋን ታሪክ ስንሰማ በውስጡ የያዘውም ትምህርት ሲነገረን እውነት ነው ብለን እንደምናጣጥመው ሁሉ ስለ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በዚያም ስለሚከናወነው የመለኮት አሳብ ሲነገር ቢጠነክርም የዚያኑ ያህል እውነት ነው፡፡ እንዲህ ካልሆነ ግን ይህ የእኔን የመረዳት ደረጃ ዝቅተኛነት እንጂ የቃሉን እውነት አለመሆን አያሳይም ማለት አለብን፡፡
የእግዚአብሔር የዘላለም አባትነት እኛን አልገባንም ማለት እግዚአብሔር አባት አይደለም ማለት አይደለም፡፡ አንድ ልጅ አባቱን ስለ ካደ የአባት አባትነት ሊሻር አሊያም ማሻሻያ ሊደረግበት አይችልም፡፡ የክርስቶስን ጌትነት አልተረዳነውም ማለት ጌትነቱ ይቀራል ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ሠራጺነት (ከአብ መውጣት) ለመረዳት ከብዶብናል ማለት ትክክል አይደለም ማለት ሊሆንም አይችልም፡፡
በዘሪው ምሳሌ መሠረትም ዘሩን መለወጥ አሊያም ቀይና ጥቁር ማድረግ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ መፍትሔው ያለው በጭንጫው መስተካከል፣ በእሾሁ መመንጠር፣ በመሬቱ መለስለስ ላይ ነው፡፡ አንድ ሕግ አዋቂ ክርስቶስን ሊፈትነው ወደ እርሱ ቀረበና መምህር ሆይ የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ላድርግ? በማለት ጠየቀው (ሉቃ. 10፥25)፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ ይህ የሕግ አዋቂ በኋላ ሲናገር እንደምናነበው ስለ ዘላለም ሕይወት ያስተዋለው የተወሰነ ነገር አለ፡፡ ጥያቄውም የእግዚአብሔርን ጽድቅና መንግሥት በቀዳሚነት የሚሹ ሁሉ ሊጠይቁት የተገባ ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ሰው ችግር የቱ ጋር ነው ያለው? ብለን ብንጠይቅ እንዲህ ያለው ጥያቄ የወደቀበት ልብ ላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጥያቄው ቀና ቢሆንም ልቡ ጠማማ ነበር፡፡ ጌታ የሚመልስለት የሚያሳርፍ ቢሆንም እንኳን አዋቂው ግን የሚሰማው እየባዘነ ነበር፡፡
ተወዳጆች ሆይ ችግሩ ከማን ነው? ከዘሩ ወይስ ከወደቀበት ስፍራ፣ በአጥንት ደረጃ ከሚነገረው ቃል ወይስ ከሚሰሙት የሕጻንነት ስፍራ፣ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ በእኛ ካደረገው ጌታ ወይስ ቃሉን በመጠማት መንፈስ ሳይሆን በፈታኝ ልብ ከመጣው ሕግ አዋቂ? ችግሩ ከማን ነው?  ከእውነቱ ወይስ ትኩረቱ ውሸት ከሆነው ኑሯችን? ከሞተልን ጌታ ወይስ ከኖርንለት ኃጢአት? ደሙን ካፈሰሰልን መድኅን ወይስ ወዛችንን ከገበርንላት ዓለም? ችግሩ ከማን ነው? ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ከተፃፈው ቃል ወይስ በሥጋና በደም ምክር ከጸናው ልማዳችን? በእርግጥ ችግሩ ከማን ነው?
ከባልንጀራው ተንኮል ይልቅ የራሱ ክፋት እንደ ጐዳው፣ ከወገኑ በደል ይልቅ የልቡ ቂም እንደ በላው፣ ጠላት ከማሰው ጉድጓድ ይልቅ የወዳጅ ሥጋው ምኞት ወደ መቃብር እንዳንደረደረው፣ ከእግዚአብሔር ዝምታ ይልቅ የእርሱ ከንቱ መለፍለፍ በረከት አልባ፣ ሰላም የለሽ እንዳደረገው የተረዳ ሰው ችግሩ የእኔ ነው ይላል፡፡ እንደ ጠቢቡ ዓይኖቹን ከሰውና ከሁኔታ ላይ ያነሣል፤ በራሱም ላይ ያደርጋል፡፡ ከሰው ሳይሆን ከራሴ አውጣኝ የዘወትር ጸሎቱ ይሆናል፡፡ የሲኦል ኃይል ሳያንበረክከው በፊት በንስሐ ጉልበት ይንበረከካል፡፡ የዘራውን ሳያጭድ በደሙ ምሕረትን ይቀበላል፡፡ ችግሩ ከማን እንደሆነ መለየት በሳይንሱ ለመፍትሔው መንገድ እንደማጋመስ ይቆጠራል፡፡ ገንፈል ገንፈል ሲያደርገን፣ ጩኽ ጩኽ ሲለን፣ ቁረጥ ቁረጥ ሲያሰኘን፣ ከሰው ጋርም መግባባት ሲያቅተን፣ የምንሰማው ሲጸንብን፣ የምናየው ሲከብድብን ችግሩ ከማን ነው? ማለት ያስፈልገናል፡፡
አንድ ጊዜ ስለ እውነት የተነገረ ምሳሌ ትዝ ይለኛል፡፡ ሜዳ ላይ አንዲት ፍየል ነብርና ዝንጀሮ በማዘውተሪያቸው ላይ ሆነው ይተያያሉ፡፡ ለነብሩ ፍየሏ ጥሩ ምግብ ናት፡፡ ለዝንጀሮው ግን ከመዝናኛነት ያለፈ ትርጉም የላትም፡፡ ግን በሁለቱም ዓይን ፊት ፍየሏ አንድ ናት፡፡ የሚለያየው እይታቸው ነው፡፡ ነብሩ ሲቋምጥ ዝንጀሮ ፈገግ ይላል፡፡ ነብሩ ሲያደፍጥ ዝንጀሮው ከዛፍ ዛፍ ይዘላል፡፡ በነብሩ ዝምታ ውስጥ ዝንጀሮ ግን ያወካል፤ ምክንያቱም ልባቸው በእኩልና በአንድ ዓይነት መንገድ አይመለከትምና ነው፡፡ ዳዊት ከአስተማሩት ይልቅ እንዳስተዋለ ይነግረናል (መዝ. 118÷99)፡፡ የሚያንሰው እንዴት ከሚበልጠው በላይ የሚበልጠውን ማስተዋል አገኘ? ግዙፋን እያሉ እግዚአብሔር እንዴት በተናቁት ሊሠራ ቻለ? በእኛ ፊት ሚዛን የደፉ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ቀለሉ? በእኛ ዘንድ የተናቁ እግዚአብሔር ፊት እንዴት ከበሩ? እኛ ውሸት ባልነው ሌሎች አምነው ተባርከው እውነት ባልነው ነገር እንዴት መንፈስ ራቀን? ደግመን ብንጠይቅ እውነት እንዲህ ይላል፡፡ “ችግሩ ከማን ነው?”፡፡ እትዉ በማስተዋል!  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም