የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ነፍሴን አሸንፈህ ስጠኝ

 “ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን ? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ፥ እነሆ ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው ፥ ይላል እግዚአብሔር ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ ።” ኤር. 45 ፡ 5 ።

ጠቢባን ሽማግሌዎች ፣ ጸጋ እግዚአብሔር የበዛላቸው አባቶች ፣ የሚያስተውሉ ወጣቶች ፣ እንደ ሕዝቡ እየተመሳሰሉ መኖር አቅቶአቸው እብድ የተባሉ ሰዎች ፣ ቀን የጣላቸው ምስኪኖች ፣ መከራ እንደ በረዶ የወረደባቸው ምንዱባኖች ፣ ድህነት ዘመድ ሁኖ ያልተለያቸው ኅዙናን የሚናገሩትን ንግግር በጽሑፍ ማስቀመጥ በጣም ወሳኝ ነው ። ስንሰማው የማንጽፈው ነገር “ይህንማ አልረሳውም” የምንለውን ነገር ነው ። የሚገርመው ቀድመን የምንረሳው እርሱን ነው ። ምክንያቱም ሁለት ነው፡- የመጀመሪያው አእምሮአችን በማይመለከተው ነገር ስለተጣበበ የሚመለከተውን ነገር ለመያዝ ሙሉ ነው እያለ ይመልሳል ። ሁለተኛው፡- በተማመንበት ነገር ዝንጉ ስለሆንን እንረሳዋለን ። በፈተና የምንወድቀውም “እኔማ በዚህ አልወድቅም” በምንለው ኃጢአት ነው ። ምክንያቱም በዚያ ጉዳይ ስለማንጸልይ ነው ። ባሮክ ግን ስለ ሕዝቡ ፣ ስለ ሥነ መንግሥቱ ፣ ስለሚመጣው ዘመን በነቢዩ ኤርምያስ ይነገር የነበረውን ትንቢት በጥንቃቄ ይመዘግብ ነበር ። የመዘገበውንም ሕዝቡ በጾም በጸሎት ሕሊናው በሚሰበሰብበት ጊዜ ያነብ ነበር ። ለንጉሡም በድፍረት ያነብ ፣ ንጉሡ ሲያቃጥለውም ደግሞ ይጽፍ ነበር ። ባሮክ ማለት የስሙ ትርጉም “ቡሩክ” ማለት ነው ። ቡሩክ የሚባል ቁምነገርን መዝግቦ የሚይዝ ነው ። የእግዚአብሔርን ቃል በመዝገብ የሚያሰፍር ሰው ዛሬ እያነሰ ነው ። አባቶች፡- “በቃል ያለ ይረሳል ፣ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” የሚሉት ለዚህ ነው ። ፊደልና መጽሐፍ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው መገለጦች ቀዳሚ ናቸው ። ያልኖርንበትን ዘመንና የማንኖርበትን ዘመን የምናይበት መነጽር መጽሐፍ ነው ። 

መጽሐፍ ጽሞናን የሚጠይቅ ነገር ነው ። ባሮክ ግን ሕዝብና መንግሥት በራሳቸው ማስተዋል ተደግፈው በሚዋከቡበት ዘመን ፣ የሚያፈስሰ ጉልላት በሚደፍኑበት ዘመን በብራና ይመዘግብ ነበር ። በአስቸጋሪ ዘመን ያለውን የእግዚአብሔር መልእክት መዝግቦ መያዝ በጣም አስፈላጊ ነው ። እንዲህ ያለውን የመከራ ዘመንም የሚያልፉ እነዚህ አስተዋዮች ናቸው። በነቢዩ በሆሴዕ፡- “የማያስተውልም ሕዝብ ይገለበጣል” ይላል ። /ሆሴዕ . 4፡14።/

ታማኝ ወዳጅ መሆን ለራስ ያለን ክብር መገለጫ ነው ። ከዘመን ጋር የሚገለባበጥ እርሱ ታማኝ ወዳጅ መባል አይችልም ። በከፍታም በዝቅታም ከወዳጁ ጋር የሚቆም እርሱ ታማኝ ተብሎ በምድር በሰማይ ይከበራል ። ባሮክ የኤርምያስ የልብ ወዳጅ ነበረ ። የልብ ወዳጅነት በሰላም ዘመን ነው ። ታማኝ ወዳጅነት ደግሞ በመከራ ዘመን ነው ። ሰላምም ሁከትም ያልለወጠው ሰው ቢኖር ባሮክ ነው ። ምቀኛ ወዳጆች ስታገኙ ይርቃሉ ፣ ደካማ ወዳጆች ስትገፉ ይሸሻሉ ። እንደ ጴጥሮስ እንዳንክድ ፣ የመስቀል ሳይሆን የገበታ ወዳጅ ብቻ እንዳንሆን ተግተን መጸለይ ይገባናል ። ጸሎት ከዳተኝነት የተባለውን ዝንብ የምናባርርበት ጭራ ነው ። በዚያ ዘመን ከኤርምያስ አጠገብ መቆም ከባድ ነበር ። ኤርምያስ ሐሰተኛ ነቢያት ገበያችንን ይነካብናል ብለው ስሙን የሚያጠፉት ፣ ነገሥታት ባንዳ ነው ብለው ግዞት የሚሰዱት ፣ ሕዝቡ ደግ ደግ አያወራም ብለው እንደ ሟርተኛ የሚያዩት ሰው ነበር ። ያ ዘመን ሦስቱ ሕጎች በመንግሥትና በሕዝብ ተግባራዊ ተደርገው ነበር ። አንሰማም ፣ አናይም ፣ አንናገርም ። ኤርምያስ ግን የሐሰተኛ ነቢያት ምላስ ፣ የነገሥታት ጅራፍ ፣ የሕዝብ ውርደት ሳይከለክለው የሚመጣውን ነገር ይናገር ነበር ። ጥፋት እየመጣ መልካም ነው የሚሉት ነቢያተ ሐሰት እየተወደዱ እውነቱን የሚናገረው ኤርምያስ ግን ተጠላ ። በዚያ በደቦ ኃጢአት በሚሠራበት ዘመን የኤርምያስ ወዳጆች ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክና ባሮክ ነበሩ ። እነዚህ ሰዎች ከቤተ መንግሥቱ ጋር ቅርብ ግንኙነት ቢኖራቸውም ወዳጅን በንጉሥ ቍጣ አልለወጡም ። የኤርምያስ ቃል እንዲሰማ ባሮክ በጽሕፈት በስብከት ፣ ከሞት እንዲድን አቤሜሌክ በምክር አደግድገው ቆመው ነበር ። በዚህም ምክንያት የደረሰባቸው ክፉ ነገር የለም። 

ባሮክ በመጨረሻ ከነቢዩ ኤርምያስ ጋር ወደ ግብጽ የተሰደደ ነው ። ወዳጅነት መውረጃ ፌርማታ የለውም ። ወዳጅነት እስከ ሞት ነው ። አብሮ መብላት ቃል ኪዳን ነው ። መንፈቅ የማይቆየው የዛሬው ፍቅር ተገለባባጭ ትውልድ እያፈራ ነው ። የአገራችን ገጣሚ እንዲህ ብሏል፡-

“ቀይ ሰው ሲጠቁር ፣ 

ጥቁር ሰው ሲቀላ ፣ 

እርሳስ ሾልኮ ሲሄድ በሰውዬው ገላ ፣

ልብ አይታመንም እንኳን ባልንጀራ ፤ 

አሁን ምንድነው ? ቅብጥር ቅብጥርጥር ፣ 

እገጭ ያለ ለት ቋሚው በቍጥር”

በሰላሙ ቀን እወድሃለሁ ፣ እወድሻለሁ አበዛዙ ። ምስክርነት ፣ የአድናቆት ቀን ለእገሌ የሚባል ድግስ መደገሱ ። ችግር የመጣ ቀን ያ ሁሉ ወድቆ የሚቀረው ጥቂት ባልንጀራ ነው ። ሌላም ገጣሚ እንዲህ ብሏል፡-

“ረጅም መቀነት ሳይስቡት ይጠብቃል ፣

የዘመኑ ፍቅር ሳይጀምሩት ያልቃል ፤

አሁን ምን ይባላል ሐተታ መናገር ፣ 

እየሰሙ መቻል ሳለ ደግ ነገር ፤ 

ከዚያም ከዚያም አትበይ እንደ ቆዳ ገድጋጅ ፣

አምላክ ከወደደው ይበቃል አንድ ወዳጅ ። 

ባሮክ ግን ፍቅሩ ቁምነገር ያለው ቋሚ ነገርን ለመተው የሚጥር ፣ ንጉሥና ሕዝብን ሳይቀር እየሞገተ ኤርምያስን የሚያድን ነበር ። ለዚህ ታላቅ ሰው እግዚአብሔር የሰጠው ቃል በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ነው፡- 

“ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን ? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ፥ እነሆ ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው ፥ ይላል እግዚአብሔር ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ ።” /ኤር. 45 ፡ 5 ።/

ቤት መሥራት እንፈልጋለን ፣ አገር ከሌለ የት ልንኖርበት ነው ? ወይን መትከል እንሻለን ፣ አገር ከፈረሰ የት ሆነን ልንበላው ነው ? ትዳር እንሻለን ፣ አገር ከሌለን የት ሆነን ልንመራው ነው ? ልጆች እንፈልጋለን ፣ አገር ከሌለ የት ልናሳድጋቸው ነው ?

“አባት የሞተ እንደሁ በልጅ ይለቀሳል ፣

ባል የሞተ እንደሁ በሚስት ይለቀሳል ፣

ወንድም የሞተ እንደሁ በእኅት ይለቀሳል ፣ 

አገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል ፤” 

የተባለው ቀላል ነገር አይደለም ። እግዚአብሔርም ባሮክን ለራስህ ትልቅ ነገር ትፈልጋለህ ? ነገር ግን አትፈልገው አለው ። ኢየሩሳሌም ልትፈርስ ተቃርቦአልና ። አገር በሌለበት ሥልጣን ፣ ሀብት ፣ ዝና ፣ ከበሬታ ጥቅም የለውም ። በቅንጦት ይኖሩ የነበሩ ሶርያውያን ዛሬ ተበትነው ስናያቸው ያሳዝናሉ ። ክብራቸውን ፣ እውቀታቸውን የሚያውቅላቸው አጥተው በአውሮፓ ምድር ፣ በእኛም አገር ጎዳና ላይ ወድቀው ስናይ አገር ከሚሞት እኔ ልሙት ያሰኛል ። በፈረሰች አገር ላይ ካለ ባለጠጋ ፣ በቆመች አገር ላይ ያለ ለማኝ ክብር አለው ። ባሮክ ስደት እንደሚመጣበት እግዚአብሔር ከነገረው በኋላ፡- “ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ” አለው ። 

ነፍስን ምርኮ አድርጎ መቀበል ቀላል ነገር መስሎን እንዳንታለል አደራ እላለሁ ። ዛሬ በሰለጠነው አገር ከአራት ሰው አንድ ሰው ፣ የአእምሮ ሕመም አለበት ይባላል ። ይህ ነፍስን የሚመለከት ጉዳይ ነው ። ባሮክ በሚሰደድበት አገር፡-

ልቡ እንዳይሰበር ፣

ሕሊናው እንዳይጎዳ ፣

ስሜቱ እንዳይረበሽ ፣

ጥያቄ ውስጡን እንዳያተራምሰው ፣

ቀልቡ ልቀቀኝ ብሎ እንዳያመልጠው ፣

ፈቃዱ ኃጢአትን መርጦ እንዳያዋርደው እግዚአብሔር ነፍስህን ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ አለው ። 

ከጸሎት ሁሉ የሚበልጥ ጸሎት ልብን የሚመለከት ጸሎት ነው ። “አቤቱ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ” ፣ “አቤቱ ልቤን ጠብቅ” ፣ “አቤቱ ልቤን ወደ ክፉ ነገር አትመልሰው” ብሎ መጸለይ ትልቅ ጸሎት ነው ። 

ዓይንና ልብ የሕሊና መስኮት ናቸው ። በምናየውና በምንሰማው እንዳንሰበር ፣ የገዛ ልባችንን ማመን አቅቶን በማዕበል እንዳንመታ ፣ ሁሉም ነገር የዜሮ ድምር ሁኖብን ለመኖር ትርጉም እንዳናጣ እግዚአብሔር ነፍሳችንን ምርኮ አድርጎ ሊሰጠን ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ መድኃኒቱ ታማኝ ወዳጅ መሆን ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ጽፎ ለትውልድ ሁሉ ማሰማት ፣ አንቱ ያሉትን ሰው አንተ ለማለት አለመቸኮል ፣ እንዲሁም መጸለይ ወሳኝ ነው ። 

እግዚአብሔር በምንሄድበት ሁሉ ነፍሳችንን ምርኮ አድርጎ ይስጠን ። አሜን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ