የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ነፍሴን አነሣለሁ

“አቤቱ ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ ።” መዝ. 24 ፡ 1 ።

የፍጥረት ሩጫ ሲገታ ፣ ተራራ ስምጥ ሲሆን ፣ የገዘፈው ሲረቅቅ ፣ የጀመረው መፈጸም ሲሳነው ፣ የታየው ሲታጣ ፣ አለሁ ያለው ከጎን ሲጠፋ ፣ ያቀፈው ክንድ ሲነቀል ፣ ያወደሰው አፍ ዲዳ ሲሆን ፣ ያሳመነው ሲያስክድ ፣ ያገለገለው ክፉ ጌታ ሲሆን ፣ የሞላለት ሲጎድልበት ፣ የቸረው ልመና ሲወጣ ፣ ያፈቀረው ሲያፍር ፣ የወደደው በወደደው ሲቀጣ ፣ ሙሉው ሲጎድል ፣ ቅዱሱ ሲረክስ ፣ ያስተማረው ሲታዘብ ፣ የተማረው ሲጨክን ፣ “ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ጦርነት ናት” ተብሎ ሲነገር ፤ እኔ ግን ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ ። ወደ ቡድን ነፍሴን ባነሣ ቡድንም ይበተናል ። ወደ ታተመው መዝገብ ነፍሴን ባነሣ የታተመም ይከፈታል ። ወደ ተደረገው ነፍሴን ባነሣ የሚያዩት ሁሉ ያቆስላል ። ወደ ፍቅር ነፍሴን ባነሣ ፣ የሰው ፍቅር ሻሽ አያደርቅም ። ወደ መልእክቶች ነፍሴን ባነሣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ያውጃሉ ። ወደ ሞላለት ነፍሴን ባነሣ ጎድሎበት አገኘዋለሁ ። ወደ አስቂኝ ነፍሴን ባነሣ ፣ ሲያለቅስ አገኘዋለሁ ። ወደ አገራት ነፍሴን ባነሣ ፣ ሲናጡ አያቸዋለሁ ። ወደ ተፈጥሮ ነፍሴን ባነሣ ፣ አቅሙ ሲሰበር አስተውላለሁ ። ወደ ቅርቦቼ ነፍሴን ባነሣ ፣ የገዛ ልቤም ሲከዳኝ አገኘዋለሁ ። አቤቱ ፣ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ ።

ብትምረኝም ብትገድለኝም ፣ ብታነሣኝም ብትጥለኝም ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ ። ከዓለም ሽልማት ያንተ ቅጣት ይሻለኛል ። ምድር ከምታለብሰኝ አንተ ብትገፈኝ ይበልጥብኛል ። አቤቱ መልካሙ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! በስቃይ ላሉት ዕረፍት ስጥ ። ከብረው ለተዋረዱት ምሕረት አድርግ ። ቀልባቸው ለከዳቸው መረጋጋትን አድል ። ውስጣቸው ለሚናወጥባቸው ሰላምህን ስበክ ። ከወንጌል ለራቁት በፍቅርህ ድረስላቸው ። ጌታ ሆይ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ ። አንተን ብቻ ተስፋ አደርጋለሁ ። የዘላለም ዕዳህ እኔ አለሁብህና ምን አለብህ ? አትባልም ። ጉዳይህ ስሆን አልጠላኸኝም ። ስበድልህ አልካድከኝም ። ሥጋዊ እግሬን ብዙ ዘመን አንሥቼአለሁ ፣ የእግር ደምበኛህ እንደሆንሁ አውቃለሁ ፤ ዛሬ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ ። ከሞት በሚቀሰቅሰው ድምፅህ ለዘላለሙ አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ