የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ና ተመላለስ

ያማረውን የፈጠርህልን ፣ እጅግም ያማሩ አድርገህ የፈጠርከን ፣ ቸል ያልናትን ነፍሳችንን ሰማይን ያየህላት ፣ ለሥጋችን ሕይወት የሰጠሃት ፣ የዓይንህ ማረፊያ ፣ የልብህ ደስታ እንድንሆን የፈቀድህ እግዚአብሔር እናመሰግንሃለን ። ለሚለምኑህ ትላንት የሰጠኸውን ችላ ብለህ እንደ ገና ትሰጣቸዋለህ ፤ አንተ የሰጠኸውን አትቆጥርም ። ላሰጣጥህም መስፈሪያ የለህም ። ለሚጠሩህም መልስ ትሰጣለህ ፣ ሰምተህ እንዳልሰማ አትሆንም ። ደግሞ ምን ፈለጉ ? ብለህ አትሰለችም ። ሳትሰማ አትበይንም ። ሁሉን እንደ አመሉ የቻልህ ፣ እንደ ጉድለቱ የሞላህለት አንተ ነህ ። ገንዘብ ሳይዙ የሚሸምቱብህ ገበያ ፣ የሕይወት ከተማ ክርስቶስ አንተ ነህ ። ያላስቀመጥነውን አምጣ እያልን ስናለቅስብህ በክብር የምትሰማን አንተ ነህ ። ልጅነታችን ባያስደስትህም አባትነትህ ግን አሳርፎናል ተመስገን ። በአንድ ልብ ሆነን ልናመልክህ ሰማይን እንናፍቃለን ። ዛሬ ከወሬ በኋላ ቃልህን ፣ ከዜና በኋላ ጸሎትን እናገፋፋለን ። ሰማይ ግን በአንድ ልብ እናመልክሃለን ። የምድር ኑሮ እንደ ድንጋይ መቀመጫ እያደር ቢቆረቁርም ከእርሱ ላለመለየት ብዙ እንጨነቃለን ። ከሰማይ እንዳንጎድል ግን ማሰብ እንኳ አንችልም ። እኛ የጨከንባትን ነፍሳችንን የራራህላት ምስጉን ነህ ።
ከሞት ወዲያ ዘመድም ወንድምም አንተ ነህ ። ምንነቱ በማይታወቅ ዓለም ፣ አረም በሚያበቅለው ሥጋ ውስጥ ፣ አበባ ሰጥተው አፈር በሚበትኑ በሰዎች መካከል ዛሬ አለን ። በሰማይ ግን ፍቅር ጽኑ ፣ ቅድስናም ብሩህ ነው ። በአገራችን ባንጋብዝህም በአገርህ ግብዣ እንዳታጎድለን አደራ እንልሃለን ። የውኃን ሙላት የምታጎድል ፣ የጎርፉንም ጽናት የምትገድብ ፣ ባሕሩን ገሥጸህ ሰላም የምትሰጥ ፣ መሻገሪያ አጥቶ ዙሪያው ባሕር ለሆነበት ጥፋትን የምታሸንፍለት አንተ ነህ ። አገርም መሸሻ ፣ ሥልጣንም ማምለጫ አይሆንም ። ሁሉም ነገር ያላንተ ከንቱ ነው ። እስከ ዛሬ መርከብ ማዕበል ያሰጋታል ፣ ማዕበልን ያሰጋ መርከብ ግን የለም ። የተጠለልንህ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ ሞገድ የማይበረታታብህ መርከባችን ነህ ። ሁሉን በሞት አንድ አድርገኸው እንደነቅ ነበር ፣ ሁሉንም በበሽታ አንድ አደረግኸው ። አንተ ስንመጣ ለእጅህ ጭብጥም የማንበቃ ነን ። ያመለክነውም አያድነንም ።
ተሸሽጎ የሚያለቅሰውን የምታይ ፣ እንባውን ሰው እንዳያይበት የሚፈራውን የምታስተውለው ፣ የልብን ትካዜ ከልብ ከተማ ላይ የምታስወግድ ፣ መንገድ ለጠፋው መንገዱ ፣ እውነቱ የት ነው ? ለሚል እውነቱ ፣ ሕይወቴ አለቀች ለሚል ሕይወቱ የሆንከው አንተ ክርስቶስ ነን ። የሥልጣንህ ዘንግ ፣ የጌትነትህ በትር ፣ የገዥነትህ ሕለተ ወርቅ ዛሬ ይዘርጋ ። እጅህን ካልዘረጋህልን የሚቀበለን ሞት ነው ። በአዳራሽህ ሞገስ ፣ በፊትም ደስታ ይሁንልን ። ከነቃን በኋላ መልሰን የተኛነውን እንደገና አንቃን ። በአንተ ጀምረን ያላንተ ለመኖር እቅድ ያወጣነውን ይቅር በለን ። ሰማዩም አፈሩም ያንተ ሳለ ልንሸሽህ ማቀዳችንን ልጅነት ነው ብለህ ውሰድልን ። በሚያስፈራው ሌሊት ከአጠገባችን እንዳትርቅ ። የክብር አክሊላችን ሲወርድ አንተ ክብራችን ሁንልን ። አመዱን አራግፈህ መጎናፀፊያን ፣ ማቁንም ቀደህ ወርቅ አልብሰን ። ዛሬም ያንተ ነውና ደስታን አብዛልን ። ከደመናት በላይ የምትመላለስ ፣ በምድራችንም ና ተመላለስ ። ምድሩ የእኛም ነውና ጋበዝንህ ። ጭንገፋንም አርቅልን ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 13
መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ