“እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት ።” ኤፌ. 3 ፡ 7 ።
ኃይል የሚለካው መግደል ማጥፋት በመቻል ነው ። የዚህ ዓለም ኃይልም ሰው እርሱን የሚመስለውን ወገን የሚገድልበት ነው ። በምድር ላይ ብዙ የጦር መሣሪያዎች ተሠርተዋል ፣ የሚገድሉት ክፋትን ቢሆን መልካም ነበረ ። የሚገድሉት ግን ሕይወቱን እንድንጠብቅ የታዘዘውን ሰውን ነው ። ወደ ባዕድ አምልኮ የሚሄዱ ሰዎች በቀል ፈላጊዎች ናቸው ። የሚያመልኩት አምላክ ተብዬ እንዲበቀልላቸው ይፈልጋሉ ። አምላካቸውም አስፈሪ ፣ ሩቅና የማይደረስበት መሆኑን በትረካቸው ያጣፍጡታል ። አምላካችን ከሁሉ የበላይ ሲሆን ትሑት ሁኖ ፣ በመግደል ሳይሆን በመሞት ፍቅሩን ገልጦ የመጣ ነው ። ክርስትናን ጥበብ የሚያደርገው የማይሞተው አምላክ በለበሰው ሥጋ መሞቱ ነው ፤ እርሱ የሰው ልጆችን ደዌና ሕማም እየፈወሰ ፣ ከጭንቀት እያሳረፈ መጣ ። እርሱ ክፋትና ራስ ወዳድነትን ተበቀለ ። ኀዳጌ በቀልነትን ይቅርታ በመስጠት አሳየ ዓለምን በዓይን ጥቅሻ ማሳለፍ ሲችል እንዲመቱት ፈቀደ ። አምላካችን የሚገድል ነው ቢባል የተለመደ አማልክታዊ ትረካ ነው ። እርሱ ግን ስለእኛ የሞተ ነውና በእምነት ካልሆነ ልንረዳው የማንችለው ነው ። ሰውን በትዕቢት መግደል ቀርቶ በበቀል ስሜትም መጉዳትን ከለከለ ። ፍቅር ከመብት በላይ መሆኑን መሰከረ ። ገዳዮች ጥይት ቢተኩሱባቸው አይደነቁም ፣ እየገደሉ ምሕረት ሲለምኑላቸው ግን ልባቸው ያንን መቋቋም አይችልም ። በምድር ላይ ካሉ ታላላቅ የጦር መሣሪያዎች ፍቅርን የሚያህለው የለም ። አሸናፊ የመሆን ምሥጢሩ ፍቅር ነው ።
የኃይሉ ሥራ ወንጌል ነው ። ወንጌል በክርስቶስ የመስቀል ሞት የተወለደች የእግዚአብሔር ኃይል መግለጫ ናት ። ሞቶ ኃያል ክርስቶስ ነው ። እነ እስክንድር ጦር ይዘው ቢወጡ ዓለምን ለማስገበር ነው ። ርስተ መንግሥተ ሰማያት ግን በወንጌል ይገኛልና ትልቅ ድል ነው ። ብዙዎችን እነ ቄሣር ገድለዋል ። ፍላጎትን ገድሎ ፣ ዓለምን ንቆ እግዚአብሔርን መከተል ግን ከሁሉ ይበልጣል ። በሰዎች ላይ ሳይሆን በራስ ላይ የበላይ የምታደርግ ወንጌል የእግዚአብሔር ኃይል አለባት ። ሽፍታው ባሕታዊ ፣ ሌባው መጽዋች ፣ ገዳዩ ታዳጊ ፣ ጨለምተኛ ባለ ተስፋ የሚሆነው በእግዚአብሔር ወንጌል ነው ። ቀናተኛውን ጳውሎስን ሐዲስ ሐዋርያ ያደረገች ፣ ያፈረሳትን ቤተ ክርስቲያን እንዲያንጽ ፣ ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ያደረገችው ወንጌል ናት ። የትላንት ከሀዲን ፣ የትላንት አሳዳጅን ሐዋርያ የምታደርግ ፣ እናንተን አልችልም ብላ ዓመፀኞችን የማትመልስ ወንጌል ናት ። ወንጌል ከውስጣቸውና ከውጭ የፍርድ ድምፅ ለሚሰሙ የምሥራች ናት ።
የእግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ ነው ። ስጦታ ነውና በገንዘብ ልግዛው ቢሉት እንደ ሲሞን መሠርይ ያስረግማል /የሐዋ. 8፡18 ።/ ገንዘብ ልሰብስብበት ቢሉም እንደ ግያዝ ከደቀ መዝሙርነት ጥሪ ያስቀራል /2ነገሥ. 5፡20-27/። ስጦታው የተሰጠው በመጠን ነው ። ስለዚህ ሁሉም ጸጋ ያለውና ምንም ጸጋ የሌለው ሰው የለም ማለት ነው ። የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ። ከሰው የተቀበልነው መስሎን መፍረት አይገባም ። በብቃታችን ያገኘነው ሳይሆን የእግዚአብሔር ደግነት መገለጫ ነው ። ሐዋርያው በወንጌል አመነ ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ አገልግሎት ጀመረ ። አሁን ደግሞ “አገልጋይ ሆንሁት” ይላል ። እግዚአብሔር አለሁ ሲለን ደስ ይለናል ፣ እኔ አለሁልህ እንደማለት ምን የሚያስደስት ነገር አለ ? እግዚአብሔር ደግ ሰዎችን እንድንመርጥለት ሳይሆን ደግ አድርገህ ሥራብኝ እንድንለው ወደ እኛ በጥሪ ድምፅ ይመጣል ። ወዮ ! ይህ ሁሉ ትውልድ የሚጠፋው ጥሪ የሌላቸው መድረኩን ሞልተውት ፣ ጥሪ ያላቸው በፍርሃት ተሸሽገው ነው ። እያንዳንዱ የምድር መከራ እሺ ብለው ለአገልግሎት ያልወጡ ብዙ ሠራዊት መኖራቸውን ያሳያል። “እኔ የጠቅል አሽከር” እየተባለ በሚፎከርበት ዓለም ፣ “ከአለቃዬ በፊት ያስቀድመኝ” በሚባልበት ምድር “አለሁልህ ጌታዬ” ማለት ክብርና ተገቢም ነው ። ለሞተልን ጌታ መኖር ካቃተን ትልቅ አለማወቅ ነው ።