መስከረም 4
“ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ።” ዮሐ. 14፡18 ።
ቅዱሳን ሐዋርያት ላለፉት 3 ዓመታት ጌታ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ ፣ ከአፉ ትምህርት እየተማሩ ፣ ከእጁ ተአምራት እየተባረኩ ኖረዋል ። ጌታችን ምድራዊ ተልእኮውን የሚያጠናቅቀው በሞቱ መሆኑን በሰሙ ጊዜ ታላቅ ኀዘን ተሰማቸው ። የተሰማቸው ኀዘን የሙት ልጆች የሚሰማቸው ስሜት ነበረ ። የሙት ልጆች ብዙ ሰው ከቧቸው ባዶነት ይሰማቸዋል ። ይህን ስሜት ባለሥልጣኖች ፣ ዝነኞችና ባለጠጎች የሚያልፉበት ነው ። የሙት ልጅ ስሜት ወይም የእጓለ ማውታነት ስቃይ ብርቱ ነው ። “የሙት ልጆች ከደኅና ቁርስ በኋላም ኀዘነተኛ ናቸው” ይባላል ። ይህ ስሜት በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል ።
እግዚአብሔር ትቶኛል ብለው የሚያስቡ ሰዎች በሰማይና በምድር የመተው ወይም የመጣል ስሜት ይሰማቸዋል ። ይህ ስሜት ከታላቅ ድል በኋላ የሚሰማ የብቸኝነት ድምፅ ነው ። የሚወዱትን በሞት ያጡ ሰዎች ለዚያ ሰው ማድረግ የሚገባቸውን ባለማድረጋቸው በዚህ ማዕበል ይናጣሉ ። በማይጨበጠው ትላንት ውስጥ ፣ ሕይወትን ወደ ኋላ መልሶ ለመኖር የምኞት ቤት ይሠራሉ ። ከዚህ በኋላ አልፈለግም ብለው የሚያስቡ ፣ የደገፋቸው ሕዝብ እንደ ተራራ የተናደባቸው ፣ ስህተታቸውን ሲደጋግሙ የሚኖሩ በዚህ ጅራፍ ይገረፋሉ ። ተስፋ ያደረጉት ነገር ድንገት ሲጨልምባቸው ፣ በዚህ ስሜትን በሚያዘበራርቅና የእንባ ከረጢትን በሚፈትሽ ድባብ ውስጥ ያልፋሉ ። ለራሳቸው በጣም ማዘን የሚወዱ ፣ “የእኔ ነገር” የሚል ነጠላ ዘፈን የሚያዘወትሩ የሙት ልጅ ስሜት ይጫናቸዋል ።
የሙት ልጅ ስሜት ወላጅ ስለ ሞተ ሳይሆን ወላጆች እያሉአቸው ብዙዎች ያልፉበታል ። ባስ ሲልም በሕይወት ያሉ ወላጆቻቸውን “ሞተዋል” እያሉ ማውራት ይቀናቸዋል ። የማልቀሻ ቦታ ፣ የማልቀሻ ምክንያት ይፈልጋሉ ። ኀዘንን ማሳደድ ፣ ጉድ ጉድ የሚያሰኙ ወሬዎችን ማነፍነፍ ይቀናቸዋል ። ነገሮችን አጋነው ማውራት ፣ ሌሎችን የኀዘናቸው ተባባሪ ለማድረግ የእንባ እርዳታ ይለምናሉ ። ይህ ስሜት እጅግ የሚያሰቃይ ፀሐይ ወጥታም በጨለማ ውስጥ የሚያስቀምጥ የነፍስ በረሃ ነው ። የሙት ልጆች ስሜት ብዙ ዓይነት ነው ።
የሙት ልጆች ስሜት፦
1- ሁሉም ነገር ጨለማ መስሎ ይታያቸዋል፡-
ፀሐይ ስትጠልቅ ጨረቃና ከዋክብት ይወጣሉ ። ጨርሶ አይጨልምም ። የሙት ልጅ ስሜት ያላቸው ግን ሁሉም ነገር ያበቃለት ይመስላቸዋል ። “ምነው በተደበላለቀ” የሚል ምኞት ይፈታተናቸዋል ። በዚህ ስሜት ውስጥ የሚያልፉት አንዳንድ ዕድለ ቢሶች ሳይሆኑ ሁላችንም በዚህ ለማለፍ የምንገደድበት ዘመን አለ ። በሕይወት ውስጥ የተዘጉ በሮችን ትቶ ያልተዘጉትን ማየት ብልህነትም መንፈሳዊነትም ነው ። ሰይጣን ለማዘን ጉድለቱን ሲያሳየን መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ለማመስገን ያለንን ያሳየናል ። ጨለምተኝነት ለሁሉም ነገር ክፉ ትርጉም መስጠት ፣ ሰውን ሁሉ መጠራጠር ፣ ፍቅርንም ጥላቻንም በጥንቃቄ ማየት ይወዳል ። ተጎድቻለሁና ልጎዳ እችላለሁ የሚል ስሜት ነው ። ይህ ስሜት ያላቸው ሰዎች ምነው በሞትኩ ይላሉ ፣ ትንሽ ሲያማቸው ግን ምርመራ ያከናውናሉ ፣ ከራስ በላይ ነፋስ በማለት ተረጋግተው ምግባቸውን ይበላሉ ። ምክንያቱም ለራሴ ያለሁት እኔው ነኝ የሚል ስሜትን ስላዳበሩ ወዳጅን ከመጥራት ምግቦችን መጥራት ይቀላቸዋል ። ማንም የለኝም የሚለው ስሜታቸው ራስ ወዳድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ። እኔ ብቻ ተጎድቻለሁ በሚል ስሜታቸውም ለሌላው ማዘን ይሳናቸዋል ። ከራሳቸው አጥር ወጥተው ስለሌሎች መኖር አይሹም ። የተቸገረ ሰው ሲያዩም ደግ ሰው ፈልገው አስተዛዝነው ይነግሩለታል እንጂ እኔም ድርሻ አለኝ ብለው አያምኑም ። ይህ ስሜት ገና ከጠዋቱ ከልጅነት የሚዳብር ሊሆን ይችላል ። በዓለም ላይ የማይተዉ ሰዎች የሉም ፤ የማይተወው ክርስቶስ ግን ከዚህ ስሜት ይታደጋል ።
ይቀጥላል
ዕለተ ብርሃን 4
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም.