ብስጩነት ያጠቃቸዋል
መስከረም 7
የእጓለ ማውታነት /የሙት ልጅነት/ ስሜት የተጫናቸው ሰዎች ብስጩዎች ናቸው ። ብስጩነት የአንዳንድ ጊዜ ገጠመኝ ሳይሆን የዘወትር ሕይወታቸው ይሆናል ። መልካም አሳብን ፣ ጥሩ ቃልን ሳይቀር በብስጭት ባሕር ውስጥ ሆነው ስለሚሰሙ በፍቅር የሚቀርቧቸውን ያሳቅቃሉ ። ያለማቋረጥ የሚሰሙት ጎደለኝ የሚሉትን ነገር ስለሆነ ያለ ርእሱም ቢሆን ይናደዳሉ ፤ በሰውም ፣ በአየሩ ጠባይም ይበሳጫሉ ። ለመዝፈን ምክንያት የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ለመበሳጨት ምክንያት ፈላጊዎችም አሉ ። እነዚህ ሰዎች የነገሩን ምንነት ሳይመረምሩ ፈጣንና ኃይል የተሞላ መልስ ይሰጣሉ ። እንደ ግስላ ብስጩዎች ፣ እንደ ነበር ቍጡዎች ናቸው ። ሰዎችን ወደ ሕይወታቸው ዐውድ ካቀረቡ ፣ ተግባብተው ከተነጋገሩ ራሳቸውን የሚያጡት ስለሚመስላቸው ሽሽትን በብስጩነት ያጅቡታል ። በውስጣቸው ፍቅር ቢኖራቸውም ፍቅራቸውን የመግለጥ አቅም የላቸውም ። በዚህ ምክንያት እነርሱ የሚወዱአቸውንም ሰዎች እየወደዱአቸው ይገፉአቸዋል ።
ብስጩነታቸውንም መጀመሪያ ቤተሰብ ያጸድቅላቸዋል ፣ ቀጥሎ አካባቢው “ጠባዩ ነው” ይላቸዋል ። በዚህ ምክንያት በዘመድ መካከል ቢኖሩም በቤት ውስጥ ክፍል ለይተው ፣ በር ቆልፈው የሚቀመጡ ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ የተገለሉ ይሆናሉ ። ንግግር የመናገር ልምድ የሚፈልግ በየጊዜው የሚያድግ ሳለ እነዚህ ሰዎች የመናገር ፍርሃት ስላለባቸው አሳባቸውን በቀላሉ መግለጥ አይችሉም ። አንዳንድ ቢሮዎች መሄድ ግድ ሲሆንባቸው “ከሰው ጋር ስለማልግባባ ኑልኝ” በማለት ንግግር አዋቂ ሰው ይጠራሉ ። ኑሮአቸውም በአስተርጓሚና በወኪል ስለሆነ ማግኘት የሚገባቸውን ሳያገኙ የገዛ ገንዘባቸውን እንኳ ሳይቀበሉ ይቀራሉ ። ይህን ጠባያቸውን ባይወዱትም ትክክል አይደለሁም ማለት የኖሩበትን ዘመን መሰረዝ ይሆንባቸውና ከጭቃ ጠባያቸው ጋር መሞት ይፈልጋሉ ። ፍቅር እስከ መቃብር እንደሚባለው ብስጩነት እስከ መቃብር ይሆናል ።
እነዚህ ሰዎች ትክክል አይደለሁም ከማለት ትክክል አይደሉም የሚለውን ሰበብ በመደርደር ከፈውሳቸው ይዘገያሉ ። የለውጥ ትልቁና ቀዳሚው እርምጃ ተሳስቻለሁ ማለት ነው ። እነዚህ ሰዎች ለመልእክት የማይታመኑ እንደ ሕፃን የሚታዩ ይሆናሉ ። እነርሱም ራሳቸው በሚያደፋፍር ሱስ ውስጥ ይደብቃሉ ። ቁምነገር አልባ ሆነው ይኖራሉ ። ብስጭት ቤትን ቀጥሎ ራስን የሚያፈርስ ጥቁር መዶሻ ነው ። ብስጩዎችን ብልጦች ሲያገኙአቸው እያወዳደሱ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን በጠራራ ፀሐይ ይዘርፉአቸዋል ። ያለ ውለታ ጉልበትና ገንዘባቸውን ይጨርሳሉ ። እነዚህ ሰዎች ለውዳሴ ከንቱ የሮጡትን ያህል ለትዳራቸው አይገኙም ።
የሙት ልጅ ስሜት የሚያመጣው ብስጩነት ከሰው መገለልን ብቸኝነትን ያመጣል ። “አመል ያወጣል ከመሐል” እንዲሉ ከቤተ ዘመድ ጉባዔ ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ የተራራቁ ይሆናሉ ። በአንድ ሰው ላይ ይበልጥ በእናት ላይ ጥገኛ ይሆናሉ ። የቅርብ ሰዎቻቸውን ሲያጡም የሕይወት ካርታው ይጠፋቸዋል ። ብስጩነት የአንዳንድ ጊዜ ገጠመኝ ሳይሆን ኑሮ ሊሆን ይችላል ። ወደ እነርሱ የሚመጣው ሰውና የሚሰሙት ንግግር ሁሉ ምክንያቱን ሳይገነዘቡ በብስጭት ይገፉታል ። በሚያበሳጭና በማያበሳጭ ነገር ቱግ ማለት ፣ በጩኸት ለማሳመን ሳይሆን በቃ በቃ ይሁንለት ወይም ይሁንላት የሚባለውን ንግግር ይወዱታል ። ብስጩዎች እንኳን አኗኗሪ በመጨረሻ ቀባሪም ሊያጡ ይችላሉ ። ሰው ሁሉ የራሱ ጉዳይ አለውና እነዚህን ሰዎች ሊሸከም የሚችል ማንም የለም ። ይህ ጠባይ በገዥዎች ላይ ከተከሰተ የተለየ አሳብ የሰጣቸውን “ስለሚጠላኝ ነው የተቃወመኝ” ብለው ይሰሙታል ። አንዳንድ ብስጩዎች በፊታቸው ላይ ሲታወቅ ሌሎች ደግሞ በልባቸው ላይ ውስጣዊ ማዕበል ሁኖ ይኖራል ። ምክር በሚሸጥበት በዚህ ዘመን በነጻ አሳብ የሚሰጡአቸውን የሚያሳድዱ ብስጩ ገዥዎች አሉ ።
ክርስቶስን ማግኘት የሚያስፈልገን ራሳችንን ለማግኘትም ነው ። በራሳችን ልንተወው ያልቻልነውን ፣ በከተማ ውስጥ ብቸኛ ያደረገንን ጠባይ ያስወግድልናል ። እርሱ ወራጁን ብስጭትን ሳይሆን ምንጭ የሆነውን የሙት ልጅ ስሜት ያስወግድልናል ። “አልተዋችሁም” የሚለን እስከ ዛሬም ያልተውን ጌታ ነው ። ቃሉ እንዲህ ይላል፡- “ጌታ ለዘላለም አይጥልምና” ሰቆ. ኤር. 3፡31።
ዕለተ ብርሃን 6
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም.