የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አልተዋችሁም

“ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ ።”
                     
ዮሐ. 14፡18 ።

እግዚአብሔር ለሚያቃስተው ምእመን በፍቅር ተናገረ፡-

ልጄ ሆይ ፣
ከባድ ቃላትን አይደለም ዝምታንም ማዳመጥ እንደ ጀመርህ ፣ ትችትን አይደለም ፣ ጎበዝ የሚል ድምፅን ማጣጣም እንዳቃተህ ፤ ጩኸትን አይደለም የለኆሳስ ንግግርን መቋቋም እንደ ተሳነህ ፣ ክስን አይደለም ወቀሳንም መስማት እንደ ቸገረህ አውቃለሁ ። መተንፈስንም እንደ ሥራ ቆጥረህ እንደ ደከመህ ፣ ሞትን እየተመኘህ ላለመሞት ብዙ እንደምትመገብ እገነዘባለሁ ። ሞትና ሕይወት የልብህን ከበሮ ሲደልቁት የቱን መምረጥ እንዳለብህ አቅቶህ ስትዋትት አይሃለሁ ፤ ላንተ ለመቸር ከተሰየሙት ከፀሐይና ከዝናብ ጋር እንደ ተጣላህ አውቃለሁ ። ልብስህ ባለ መድረቁ ትበሳጫለህ ፣ ፀሐይ በመውጣቷ ደግሞ ትተክዛለህ ። ደመናው ጨገገኝ ትላለህ ፣ ዋዕዩ አላስወጣ አለኝ ብለህ ደግሞ ታዝናለህ ። በቀጣይ ዓመት ራብ እንዳይመጣ ብለህ ትሰጋለህ ፣ ዝናቡን ደግሞ ታማርራለህ ። ልጄ ሆይ ፣ የምትፈልገውን ባለማወቅ እንደ ደከምህ ባውቅም ሳልታዘብ አይሃለሁ ። እኔ ስታዘብ ፍቅር መሆኔ ይቀራል ። ራሴን አልክድምና መታዘብ በእኔ ዘንድ የለም ። የምትለምነውን ባልሰጠሁህ ዘመን ደስተኛ ነበርህ ፣ ሳትለምን እየሰጠሁህ ግን አመስጋኝ አይደለህም ። ጊዜ ብታገኝ ብዙ እንደምትሮጥልኝ ነግረኸኝ ነበር ። ያገኘኸውን ጊዜ ግን ለድንዛዜ ሰጥተኸዋል ። የራስህን ድምፅ መልሰህ የምትሰማበት ፣ ቅዱስ ቃሌን ለማሰስ እጅ እግርህ የተያዘበት ይህ ማመንታት በጎ አይደለም ። ቀኑን አጋምሰህ ከመኝታህ ትነሣለህ ፣ ስሜ ሲቀደስ ግን በመኝታህ ላይ ሁነህ ትሰማለህ ። ሌሊቱን ነቅተህ ያለ ክፍያ ዘበኛ ሆነህ ራስህን ታደክማለህ ።

ልጄ ሆይ ፣
አዲሱ ቀን አዲስ ሁኖ አይታይህም ። የተደገመ ቀን አድርገህ ታየዋለህ ። የገዛሁልህን ልብሶች እንኳ ለመልበስ መነሣሣት ታጣለህ ። ብርሃኑን ምሽት ፣ ዕድሉን አጋጣሚ ፣ በረከቱን መሆን ስላለበት የሆነ ፣ ረዳቶችህን መሄጃ እንዳጡ ትቆጥራለህ ። ላለማየት ፣ ላለመስማት ፣ ላለመናገር ሁልጊዜ ትምላለህ ። መሐላህን በማፍረስህ ደግሞ ታዝናለህ ። ፍቅር ትንሽ ፈገግ ያደርግሃል ፣ ጥላቻ ግን ዓመት ሙሉ ያስለቅስሃል ። ዕድሜ ለቂም እንጂ ለይቅርታ አልሰጠህም ። የዳነው ስሜትህ መልሶ ያውክሃል ። ረግረጉ ጉዞ ወጣሁ ስትል ያስቀርሃል ። ትላንት የሚቀልህ የገዛ አካልህ ዛሬ እንደ በድን ይከብድሃል ። በፈተና ውስጥ ለበጎ ነው ይል የነበረው ብርታትህ በብርሃን ውስጥ ማመስገን አልቻለም ። እንደ ቀላል የነጋ መስሎህ ወደ ሥራህ ትሄዳለህ ፣ ግድ ስለሆነ የመሸ እየመሰለህ ወደ መኝታህ ትሰየማለህ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ልታመሰግነኝ አልቻልህም ። የበዛብህ የምስጋና ዕዳ ደስታህን እየተጋፋው ነው ። ለመሥራት የተፈጠሩ እጆችህ ስለለሰለሱ ሰውነትህ እየተሳሰረ ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት እንድትሄድ የተፈጠረው እግርህ ስለሰነፈ አካልህ እየከበደህ ነው ። ስለሚሰቃዩት ማሰብ ባለመቻልህ ወደ ራስህ በጣም እያተኮርህ ነው ። ድሆችን ስለዘነጋህ የውሸት ፍቅር እያደከመህ ነው ።

እጆችህ ሱስ ስላለባቸው ይሰጣሉ እንጂ ደስታ እየተሰማህ አትሰጥም ። መራራትህ የእግዚአብሔርን ባሕርይ መካፈል መሆኑን ዘንግተህ ከመደሰት ትጸጸትበታለህ ። ሰዎች ባንተ ደስ የሚላቸውን ያህል አንተ በራስህ ደስ አይልህም ። የወላጆችህን መከተል እንደ ቀላል ታየዋለህ ፣ ሲፈልጉህ ትበሳጫለህ ። በሰርግ ጀምረህ በእሮሮ መኖርህን ታዝንበታለህ ። ሰዎች ያሻቸውን አድርገው ሲተኙ ምነው እንደ እነርሱ ለመሆን በቻልኩኝ ትላለህ ። ፍጻሜአቸውን ሳታይ በጅምራቸው ትቀናለህ ። ብታደርገውም እውቀት ቀድሞ በውስጥ ገብቷልና እንደ አላዋቂዎች መደሰት አትችልም ። በአሻንጉሊት ሕፃናት የሚደሰቱትን ያህል አዋቂዎች መደሰት አይችሉምና ።

ልጄ ሆይ ፣
መሪው ላይ ተቀምጠህ መሪውን ለቀሃል ፣ በአባትነት ሹመት ውስጥ ሁነህ የልጆችን ዓለም ተቀላቅለሃል ። እሳት ጥደህ ረስተሃል ፣ ልጅ አስተኝተህ አገር ለቀህ ሂደሃል ። ሰዎችን ሁሉ በጥቂት ክፉዎች መዝነህ ከሁሉ ርቀሃል ። አንድ ጊዜ ሞክረህ አቁመሃል ። እግዚአብሔርም ከሰው ጋር ያደመ መስሎህ ተቀይመሃል ። በመንፈሳዊነት ጀምረው በሥጋ ሲጨርሱ ፣ ቤተ ክርስቲያን ያገር ልጅ ዕድር ሲሆን ፣ የክርስትና ፍቅር በሥጋ ፍቅር ሲጠናቀቅ አዝነሃል ። የምትወዳቸውን ስትፈልግ የሚወዱህን ረስተሃል ። ብትጮህ የማይሰሙህን ስትጣራ የሚፈልጉህን ችላ ብለሃል ። ያልከውን ባለማግኘትህ እልህ ይተናነቅሃል ፣ የፈቀድኩትን በማግኘትህ ደስታ አጥተሃል ።

ልጄ ሆይ፣
የሚሞቱ እናትና አባትን የምሰጥ የማልሞተው እናትና አባት እኔ ነኝ ። አንተ “አባታችን ነህ ፣ አንተ እናታችን ነህ” ተብዬ በአባቶችህ የተመሰገንሁ ነኝ ። አንተ ግን ስሜትህ እንደ ሙት ልጅ ስሜት ቶሎ የሚከፋ ፣ ለማልቀስ ምክንያት የሚሻ ፣ ሲገፈትሩት ለመውደቅ በጥፍሩ እንደ ቆመ ሰው ነህ ። የጎደለህን እንጂ ያለህን ብዙ ማየት አልቻልህም ። የሞትና የወረት ገደብ ካላቸው ሰዎች ጋር ለዘላለም ፍቅር ትጀምራለህ ፣ ስለዚህ እልፍ ሲሉ መኖርን ትጠላለህ ። ባለህ ነገር ከመደሰት በሌለህ ነገር ውስጥ ደስታህን ታስሳለህ ። ዛሬ ያለህ ትላንት ያልነበረህና አልቅሰህ የጨበጥከው ነው ። ዓለም እንደ ተስፋው ፍጻሜው አያስደስትም ። በእኔ ካላረፍህ በሥጋዊም በመንፈሳዊም በረከት ማረፍ አትችልም ። ድውይ ብትፈውስ ፣ ሙት ብታስነሣም ደስተኛ አትሆንም ።

ልጄ ሆይ ፣
የመተው ስሜት ፣ የመጣል ዕዳ ውድቆብሃል ። በሰው መካከል ብቸኝነት ፣ በለማው ከተማ በረሃማነት እያሰቃየህ ነው ። የስሜት ሥዕልህን በጣም ታምነዋለህ ። የአሳብ ጎጆህም ስትነቃ እየፈረሰ ትበሳጫለህ ። እኔ ግን ካንተ ጋር ነኝ ። ቅዱስ መንፈሴም አይለይህም ። ዓርብ ሞት ቢመጣም እሑድ ትንሣኤ ነው ። ከመሬት በታች ብትከተትና ዝናህ ቢረሳ ዕርገት በአርባኛው ቀን ነው ። ትጥቅህ ቢፈታ የበዓለ ሃምሳ ደስታ በቤትህ ነው ። የተሰማህና እውነቱ ለየራስ ነው ። እኔ ካንተ ጋር ነኝ ። እኔ ከሺህ ወዳጆች ፣ ከሺህ ዕድሎች እበልጣለሁ ። በዚህ ቃል ተጽናና።

ምእመኑ በእንባ መለሰ፡-

ጌታዬ ሆይ ፣ እውነት ነጻ ታወጣለች ብለሃል ፤ እውነትም እኔ ነኝ ብለሃል ። በእውነትህ ከአሳቤና ከክፉ ምኞቴ ፍታኝ ። ወደ ውስጤ ጠልቀህ በአሳቤ አደባባይ ያለውን ጦርነት አንሣልኝ ። የሚታዘንልኝ ሰው ለመሆን ምስኪንነትን እንዳልለማመድ የትንሣኤህ ሠራዊት አድርገኝ ። እኔ ትቼህ አንተ ተውከኝ እልሃለሁ ፣ አለመኖር ውስጥ ሆኜ የለህም እልሃለሁ ። በውስጤ ሳለህ በደጅ እፈልግሃለሁ ። ለሌሎች ላደርስ የሚገባኝን ከልክዬ የራሴ በረከት ተይዞብኛል ። ደስታዬ ጎረቤቴ ድሀ ውስጥ ሳለ የባሕር ዳርቻ ላይ እፈልገዋለሁ ። አንተ የነገርከኝን ተጠራጥሬ የጠላትን ድምፅ እውነት ብዬ እቀበላለሁ ። እባክህን ጌታዬ ከስሜቴ ቃልህ ፣ ከፍርሃቴ እምነት እንዲበልጥብኝ እለምንሃለሁ ። ሆደ ባሻነቴ በልበ ሰፊነት ይለወጥ ። እያስፈራራሁህ ማገልገሌ ቀርቶ እየፈራሁህ እንድገዛልህ እርዳኝ ። አንተ ሕያው ጌታዬ ነህና የሙት ልጅ ስሜትን ፣ የእጓለ ማውታ ፍርሃትን ከእኔ አርቅ ። በዘላለማዊ ሥልጣንህ ፣ ከመቃብር በላይ በገነነው ክብርህ አሜን ። የሰማይ መላእክት አሜን ይበሉ ።

የፍቅር ድምፅ /3

ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም.

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ