የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አምላካችን

አምላካችን ራሱን የሚገልጥ ፣ ራሱን የሚሰጥ ፣ ለተጨነቁት ወሰን የለሽ ብርሃኑን የሚለግስ ነው ። እግዚአብሔር፣ አምላክ የተደረገ ሳይሆን አምላክ የሆነ ነው ። እርሱ በፈጠረው ፍጥረት ይመለካል ። ጣዖታት ግን አምላክ የተደረጉ የሰው ልጆች ሁሉን የመዳሰስ ፍላጎትን ያሟሉ ናቸው ። ድንጋይ ለዝቦ ፣ እንጨት ተጠርቦ የተሠሩ የጠቢብ ሰው ሥራ ናቸው ። ሰው ለእርሱ ለተፈጠሩት ፍጥረታት ፣ ደግሞም በእጁ ላበጃቸው ነገሮች አምልኮ ይሰጣል ። እግዚአብሔር ግን ፈጥሮ የሚገዛ ፣ በህልውናው የሚመለክ ነው ። በጠሩት ጊዜ ከሩቅ መንገድ የማይመጣ ፣ ሲፈልጉት የማይታጣ ነው ። ይህ አምላክ በአስተርእዮ/በመገለጥ ብቻ የሚታወቅ አምላክ ነው ። ራሱንም የሚገልጥ እውነት ነው ። የሚደበቅ ሐሰት ሲሆን እውነት ግን ብርሃንን አይፈራም ። እግዚአብሔር በሰው ልጆች አቅም ልክ ራሱን ይገልጣል ። ባሕርይው ባሕርዩን አውቆት ፣ በራሱ ምስጋና ለዘላለም ይኖራል ። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንዲፈልግ ሁኖ በመፈጠሩ እርሱን እስኪያገኘው ድረስ ባካና ይሆናል ። ቁሳቁስና ሥጋዊ መሻቶች የማይሰጡትን ደስታ እግዚአብሔር ይሰጠዋል ።

ጣዖታት ስለ ራሳቸውም ስለሚያመልኳቸውም የሚናገሩት ቃል የላቸውም ። በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው እግዚአብሔር ግን የሚናገር አምላክ ነው ። ስለ እርሱ ያወቅነው ሁሉ “እኔ ነኝ” ብሎ በተናገረው ነው ። እርሱ እኔ ባይ አምላክ ነው ። እኛ እኔ እንዲህ ነኝ ባልንበት ነገር ፈጥነን እንታጣለን ። ቆንጆ ነኝ ብለን መስክረን ወዲያው እንረግፋለን ። እርሱ ግን እርሱ ነው ። ነቢዩ “አንተ ግን ፣ ያው አንተ ነህ” እንዳለው ነው (መዝ. 101 ፡ 27) ። ሃይማኖት ከምድር ጀምሮ ወደ ሰማይ የሄደ አይደለም ። ሃይማኖት የምርምር ውጤት ሳይሆን ከሰማይ ወደ ምድር የወረደ ብርሃን ነው ። ለዚህ ብርሃን ሰው የሚሰጠው መልስ እምነት ይባላል ። እግዚአብሔር የሚያስደስት ሀብትና ልጅ ፣ ትዳርና ሥልጣን አይሰጠንም ። ራሱ ደስታ ነው ። “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ” እንዳለ ጳውሎስ ሐዋርያ (ፊልጵ. 4 ፡ 4) ።

እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥ ብቻ ሳይሆን ራሱን የሚሰጥ አምላክ ነው ።

የፍቅሩን ተአምር አየነው ፣
ልጁን በመስቀል አገኘነው ።

ክፉ መናፍስት ልጆቻችሁን ሠዉልን ይላሉ ። ስንቱ ታዋቂና ባለጠጋ ልጁን ገብሮ እዚህ የደረሰ ነው ። የክርስቲያን አምላክ ግን አንድ ልጁን ፣ ለበደለው ባሪያ ሰጥቶ ያዳነን ነው ። ልጅን እንኳን ለበደለ ባሪያ ፣ ለጥሩ ወዳጅም ያውም ለሞት አይሰጡትም ። እኔ ልሙት ብሎ ብቻ የማለ ሳይሆን እኔ ልሙት ብሎ ፣ ምሎ የፈጸመ አማኑኤል ብቻ ነው ። ለዚህ ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ እርሱ እምነት ነው ።

ለተጨነቁት ብርሃንን የሚሰጥ አምላክ አለ ብለን ስናምን የከበደን ጥቁር ደመና እየተበተነ ይመጣል ። እያንዳንዱ ቀን የራሱ ጥያቄ አለው ። ግራ የሚያጋቡን ክስተቶች እንደ አሸን እየፈሉ ነው ። ብዙ ጨለማዎች በግልና በዓለም ላይ ሰፍነዋል ። መዳን ከየት ይሆንልናል የሚሉ ጠያቂዎች በዝተዋል ። ሰዎችን እንደ ማሽን እየተጠቀሙ ለመምራት የሚፈልጉ ነገሥታት በርክተዋል ። የሰው ልጅ ቍጥር መቀነስ አለበት ብለው የሚያስቡ ፣ ችግሩን ሳይሆን ሰውን ለመቀነስ የሚያልሙ ጠቢባን ተደራጅተዋል ። የሰው ልጅ ተስፋ በዙሪያው ካለው አዋቂና ዘመድ እየራቀ ነው ። በብርሃኑ ጨለማን የሚገፍፈው አምላካችን እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

የሰማይ አምላክ እጁን ይዘርጋላችሁ!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ