የትምህርቱ ርዕስ | አምላካችን

“አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝ. 45 ፡ 1 ።)

እግዚአብሔር አምላክ ነው ። ፍጡራን አምላክ ብለው ያልሰየሙት ፣ አምላክ ያላደረጉት ነው ። አምላክነቱ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ፣ አምላክ ሳይሆን ያልኖረ ፣ አምላክነቱን አጣዋለሁ ብሎ የማይሰጋ ብቸኛ አምላክ ነው ። ለአምላክነቱ የጊዜና የቦታ ዳርቻ የሌለው የሁሉ ዘመን ፣ የሁሉ ስፍራ አምላክ ነው ። አምላክነቱ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ታውቆ የኖረ ፣ ለአምላክነቱ እንኳን ሕያው ፍጡር ግዙፍ ሰማይ አንደበት ያለው ፣ “አምላክ ነው” ብሎ የሚመሰክርለት ነው ። የእርሱ አምላክነት ከፍ ብሎ ቢታየን ፣ የሚያስጨንቁን ከፍታዎች አይኖሩም ነበር ። ሁሉ ከእርሱ አምላክነት በታች ሲሆን እርሱ ግን ማነስ የማይስማማው የዘላለም ክብር ባለቤት ነው ። “ለከፍተኛነቱም ፍጻሜ የለውም” የተባለለት ፣ በአርያም አገሩ በዓይነ ምሕረት ድሆችን የሚመለከት ነው ። ራሳቸውን አምላክ አድርገው የቀቡ ብዙ ኃያላን ነበሩ ። “ቄሣር ጌታ ነው ፣ ቄሣር የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ብለው ያወጁ ፣ ለምስላቸውም በመንፈስ እንዲሰገድ ያዘዙ ነበሩ ። ለምስላቸው በመንፈስ ያልሰገደውን ፣ “ቄሣር ጌታ ነው” ብሎ ያልመሰከረውን በሰይፍ ይገድሉ ፣ በእሳት ያቃጥሉ ነበር ። እነዚህ ሰዎች አምላክ ነን አሉ ፣ ግን በግድ አምልኩኝ የሚሉ ነበሩ ። ሐሰት ጭካኔ ይከተለዋልና ብዙዎችን ጨረሱ ። እውነተኛው አምላክ ግን በነጻነት የሚገዛ አምላክ ነው ። የአንድ አገር ዜጋ ሁሉ ለመንግሥቱ ግብር እንዲከፍል የሰማዩ መንግሥትም ግብሩ አምልኮ ነው ።

አንድ ሰው አሥራቱን ሲሰጥ እንዲህ ሲል ሰማሁ፡- “አሥራቴን የሚቀበለኝ በማግኘቴ በምድር ላይ ዕድለኛ ሰው ነኝ” አለ ። አሥራታችንን እናቆማለን እያሉ የሚያስፈራሩ ምእመናን ባሉበት ዓለም እንዲህ የተረዳ ሰው ማግኘት ደስ ይላል ። ዕድለኛው መንፈሳዊ አገልጋዮች ወይም ቤተ ክርስቲያን አይደሉም ፣ አሥራት ሰጪው ሰው ተቀባይ ማግኘቱ ነው ። የአገራችን ሕዝብ የማይባረከው መሠረታዊ ችግሩ አሥራትን ከማይሰረቀው እግዚአብሔር ስለሚሰርቅ ነው ። አሥራትን የሚሰርቁ የእንቧይ ካብ ይክባሉ ። የሠሩት ቤትና ኑሮአቸውን ጨረስኩት ሲሉ መፍረስ ይጀምራል ። አገልጋዮችም የአሥራት አሥራት የማውጣት ግዴታ አለብን ። አሊያ ያልተባረከ ኑሮና ቤተሰብ እንይዛለን ። አዎ የምናመልከውን እውነተኛውን አምላክ ማግኘት ዕድለኛነት ነው ። ብዙዎች አላገኙም ። የአጋንንት አምልኮ ያለባቸው ሰዎች ግብር ሲደርስ ይጨነቃሉ ። ርኵስ መንፈስ ሽቶ እያስጠጣ ፣ እሳት እያስበላ ሲያሰቃይ ይታያል ። ሰይጣን ወዳጅ አያውቅም ። ስለ እግዚአብሔር ሀልወት ሳይሆን ስለ ሰይጣን አብዝተው የሚያወሩትን ብንነቅፍም ሰይጣን እንዳለም እናውቃለን ። አክብሮ የሚገዛውን ጌታ ማግኘት መታደል ነው ። ሰይጣናዊ አምልኮ ልጅን ሳይቀር መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡበት ነው ። የተከለከለው ለልጃችን እንኳ የማይራራ በእሳት ውስጥ አሳልፉልኝ የሚል ጨካኝ ስለሆነ ነው ። እኛ ግን ልጅን የምንሠዋለት ሳይሆን አንድ ልጁን ሳይራራ ለመስቀል ሞት የሰጠውን እናመልካለን ።

“እግዚአብሔር አምላኬ ነው” ማለት ድንቅ ምስክርነት ነው ። እግዚአብሔር አምላኩ የሆነው ሕዝብም የታደለ ፣ የተመሰገነ ነው ። ነቢዩ ዳዊት “አምላካችን” ይለዋል ። ልዕልናው ቅርበትን ያልከለከለው ፣ ከፍታው ትሑትነትን ያላስቀረበት አምላክ አለን ። ስናከብረው የማያዋርደን ፣ ስንቀርበው የማይሸሸን አምላክ አለን ። እርሱ አምላካችን መሆኑን እንመሰክራለን ። የአገሩ መሪ ልጃቸው ቢታዘዛቸውም ባይታዘዛቸውም እርሳቸውን የሚጠላ ልጃቸውንም ሊጠላ ይችላል ። እኛም እግዚአብሔርን ብንታዘዘውም ባንታዘዘውም የእርሱ በመሆናችን ብቻ ጠላት አትርፈናል ። እርሱን የሚጠላ ይጠላናል ። እርሱን ያገኘ መስሎት ያዋርደናል ፣ ይገድለናል ። እንዳይገድሉን አድርጎ ሳይሆን እየገደሉን እንድንበዛ አድርጎ ይረዳናል ።

እግዚአብሔርንም ሰይጣንንም አናምንም የሚሉ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ ። እግዚአብሔርን የምናምነው ስናምነው ብቻ ነው ። ሰይጣን ግን ረክሷልና እየሰደብነውም ሥራውን ከሠራንለት እንዳመለክነው ይቆጥረዋል ። እግዚአብሔርም ሰይጣንም የለም የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ ። እግዚአብሔርን አለ ብሎ አለማመን ዋጋ ያስከፍላል ። አንድ ሰው በጎዳና ወጥቶ መንግሥት የለም ቢል በዝምታ አይታለፍም ። ሰይጣን ግን የለም ሲሉት የበለጠ ይደሰታል ። ምክንያቱም ጠላት የለም ብለው ሲዘናጉለት ማጥቃት ይችላል ። አምላክ ያለው ሕዝብ ፈራጅ አለው ። እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ደመና ተጋርዶለት ፣ የውርጭ ገበታ ተዘርግቶለት ፣ መና እየወረደለት ምድረ በዳውን የሰነጠቀ ነው ።

ያለብን ችግር ምንም ይሁን ፤ ብቻ አምላክ አለን ! እርሱ እኛን ልጆቼ ማለት ካላፈረ እኛ እርሱን አምላኬ ማለት አያሳፍረንም ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም