የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ ————— ማክሰኞ መስከረም 6/ 2007 ዓ/ም
(ማቴ 10÷40-42)
ሰዎች በሥርዓት እንዲኖሩ፣ ዓለምን እንዲንቁ፣ በችግርና በጉስቁልና ሁሉ ደስ እንዲላቸው ተከታዮቿን በቅጡ የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነች አይቻለሁ፡፡ ታዲያ በልጅነቴ ማን ፈጠረህ? ሥላሴ ከሚለው ትምህርት ባሻገር ዘራችሁ ምንድነው? ክርስቲያን፡፡ ሀገራችሁ የት ነው? ኢየሩሳሌም ሰማያዊት በሚሉ ትምህርቶች ያሳደጉን መምህራን ነበሩ፡፡ ከዚህ ውጭ ዘርና አገሩን የሚቆጥር ክርስቲያን አይደለም ይሉን ስለነበር በምድር ላይ የቀረን ነገር ያለ እስከማይመስለን ጉዳያችንን ሰማያዊ አድርገውት ነበር፡፡
ክርስቲያኖች ካገኙት አስደናቂ ስያሜ አንዱ አምባሳደር የሚለው ስያሜ ነው፡፡ አንድ ሰው ‹‹እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት የሚሠራው በቀደመው ታሪካችን መሠረት ሳይሆን በወደፊቱ ታሪካችን መሠረት ነው፡፡ ፍርሃት ለሚንጠው ጌዴዎን÷ ‹‹አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው÷ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው›› ብሎታል (መሳ.6÷12)›› ብሏል፡፡
አምባሳደር የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በግእዙ ‹‹እንደራሴ›› በአማርኛው ‹‹መልእክተኛ›› ተብሎ ተተርጎሟል (2ቆሮ.5÷÷20)፡፡
ዘራችሁ ምንድነው? ለሚለው የመምህሩ ጥያቄ ሕጻናት ሰንበት ተማሪዎች በአንድ ላይ ‹‹ክርስቲያን›› በማለት የሚመልሱት ከዓመታት በኋላ በጆሮዬ ያቃጨለው ‹‹አምባሳደር›› የሚለውን ቃል ለመፍታት ትኩር ባልኩበት ሰዓት ነው፡፡ አምባሳደር በአገሩ አምባሳደር አይሆንም፡፡ ከአገሩ ውጭ ነው አምባሳደር የሚሆነው፡፡ ወደ አገሩ ሲመለስም የአምባሳደርነት ሥራው ያበቃል፡፡ መጽሐፉ አምባሳደሮች-እንደራሴዎች ናችሁ ሲለን ከአገራችን ርቀን እንዳለን ግልጽ ነው፡፡ አምባሳደሮች ያለን ጳውሎስ፣ በሌላ ስፍራ ‹‹እኛ አገራችን በሰማይ ነውና›› (ፊልጵ.3÷20) ይለናል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ የእንግድነት ኑሮ እንደምንኖር በመቀባበል ነግረውናል (ዕብ.13÷13-14፤ 1ጴጥ.1÷17)፡፡ በአምባሳደርነት ሥራችንም ወንጌልን መስበክ ነው (2ቆሮ.5÷20)፡፡
አምባሳደር ለላከው የመንግሥቱ ሙሉ ወኪል ነው፡፡ አምባሳደር በሌላ አገር ላይ የሚኖር መንግሥት ነው፣ ግቢውም የአገሩ ግዛት ነው፡፡ አይደፈርም፣ መማፀኛም ነው፡፡ ጌታችን መንግሥተ ሰማያት በማለት ሲናገር ወንጌልንና ቤተክርስቲያንን ያመለክት ነበር (ማቴ.13÷44፣45፣47)፡፡ ሌላ ስፍራ ላይም ምእመናን የካህናት መንግሥት ተብለዋል (1ጴጥ.2÷9፤ራዕ.1÷5፣5÷9-10)፡፡
አምባሳደር ራሱን ወክሎ አይኖርምና እኔ ብሎ አይናገርም፡፡ የሚያንፀባርቀው የአገሩን ሕገ መንግሥትና አቋም ነው፡፡ ክርስቲያንም ከእውቀት ወይም ከሥጋ አንጻር የሚናገረው የለውም፡፡ ሊናገረው የሚገባው የእግዚአብሔርን ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ ማንም ራሱን ለአምባሳደርነት አያጭም፡፡ የእኛም የመጠራታችን ዋጋ መልካምነታችን ሳይሆን በቸርነቱ መመረጣችን ብቻ ነው፡፡
የዓለም አገሮች የሞቀ ግንኙነት ምልክቱ፣ በእነዚያ አገሮች የአምባሳደር ወንበር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር ላለን ግንኙነት መስመር እርሱ የላካቸውን አገልጋዮች መቀበል ስንችል ነው፡፡ አምባሳደር የተላከባት አገር ለእርሱ የምታደርገው ነገር ሁሉ ለግሉ ያደረገችለት ሳይሆን ለላከው ሕዝብና መንግሥት ያደረገችው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንዲሁም ለጌታ አገልጋዮች የምናደርገው ሁሉ ለክርስቶስ ያደረግነው ነው፡፡ እርሱ የአገልጋዮቹ ስደት የራሱ ስደት መሆኑን ‹‹ሳውል÷ ሳውል÷ስለምን ታሳደድኛለህ›› (የሐዋ.ሥራ.9÷4) በሚለው ቃሉ ሲገልጽ ለአገልጋዮቹ የሚደረገውን ቸርነትም ለእርሱ እንደተደረገ ይቆጥረዋል (ማቴ.10÷40-42)፡፡ የአንዲት ብርጭቆ ዋጋ እንኳ አታልፍበትም (ዕብ.6÷10)፡፡ እግዚአብሔር የማንም ውለታ ባለዕዳ አይደለምና፡፡ አምባሳደርነት ያስጠይቃልና የተላከበት ሕዝብና መንግሥት ይጠነቀቅለታል፡፡ እንዲሁም ወደ እኛ ስለተላኩት አገልጋዮች እግዚአብሔር እንደሚጠይቅ የምናውቅ ስንቶች ነን? እግዚአብሔር በአገልጋዮቹ በፍጹም አይደራደርም (መዝ.104(5)÷14)፡፡ አንተም አገልጋዩ በምታገለግላቸው ሕዝብ ሳይሆን በክርስቶስ ዕረፍ!