የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አምነው ሞቱ

አምነው ሞቱ

“በውድ ልጁም ፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን ፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት ። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ።” ኤፌ. 1 ፡ 7-8 ።

ክርስቶስ ውድ ነው ። እንደ እርሱ የሚወደን የለም ። እኛም ከሁሉ አብልጠን ብንወደው ኖሮ በታደልን ነበር !! እንኳን ውድ ልጁን ፣ የበደለ ልጁን ለሞት አሳልፎ የሚሰጥ ወላጅ የለም ። ልጃቸውን ለዘመቻ በላኩ ወላጆች እንደነቃለን ። “ማን በሞተለት አገር ልትኖር ነው !” ብለው ሲልኩ ፣ “የእርሱን ሞት ማን ይሙትለት ” ብለው ሲፎክሩ መስማት ይገርማል ። እነዚህ ሁሉ ጠላትን ገድለው አገርን እንዲያድኑ ልጆቻቸውን ልከዋል ። ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ግን ልጁን ግደል ሳይሆን ሙትላቸው ብሎ ልኮታል ። ይህ ልጅም ውድ ልጅ ነው ። ልጆች ሁሉ ከአባታቸው ቤት ወጥተው ርቀው ይኖራሉ ። የአባታቸውን ስም ሲያስጠሩ ይኖራሉ ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከአባቱ ለቅጽበት ሳይለይ “የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይመስገን” ተብሎ አባቱን ሲያስጠራ ሲያስመሰግን ይኖራል ።

በዘመናት ሁሉ እኔ ልሙትልህ የሚል መሐላ ነበረ ። ሞቶ ያሳየ ግን ላይኖር ይችላል ። እኔ ልሙትላችሁ ብሎ ምሎ የመጣ ፣ ሞቶ ያሳየን ግን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። የፍቅር ጥግ የሆነውን ለሌላው የመሞትን መሥዋዕትነት ለዓለም ይገልጥ ዘንድ ወደ ዓለም መጣ ። በመለኮታዊ ባሕርይው ሊሞት አይችልምና የእኛን መዋቲ ሥጋ ለብሶ በመስቀል ላይ ዋለ ። መለኮት በሥጋ ሞተ ። ሥጋ ብቻውን ቢሞት የዕሩቅ ብእሲ/የፍጡር ሞት ዓለምን ማዳን ባልተቻለው ነበር ። ሥጋም በመለኮት ከበረ ። ሞትን ድል ነሺ ሆነ ። ይህ ሁሉ የተደረገልን በውድ ልጁ ነው ። ሰው የድኅነቱን አድራሻ ማወቅ ክርስቲያናዊ ግዴታው ነው ። እርሱ ያዳነንም እንድንፎክር ሳይሆን መልካም እንድንሠራ ነው ። በሥራ ብቻ ልዳን የሚል እምነትን ሲጥል ፣ በእምነት ብቻ የሚልም በአፉ ብቻ ጌታን አከብራለሁ ባይ ነው ። እምነታችን የሚያሠራ ፣ ሥራችንም የሚያምን መሆን ይገባዋል ።

ነቢያት ነባዮች ቢባሉ ስለ ክርስቶስ ትንቢት ተናግረው ፣ ሐዋርያት ሐዋርያት ቢባሉም ስለ ክርስቶስ ሰብከው ፣ ሰማዕታት ሰማዕታት ቢባሉ ስለ ክርስቶስ ሞተው ነው ። ሁሉ ስለ እርሱ ይወደዳሉ ። እርሱ በባሕርይው ውድ ነው ። ሙሽራ ነውና ሚዜዎች አሉት ። ቅዱሳንም ከክርስቶስ አይለዩም ። ሚዜዎችም ሙሽራውን ያጎላሉ ፣ ቅዱሳንም ክርስቶስን ለዓለም ያሳያሉ ። ሙሽራ የሌለው ሚዜ ፣ ሚዜም የሌለው ሙሽራ የለም ። እርሱ ቤዛ ሁኗልና የቅዱሳን ምልጃም ወደዚህ ቤዛነት እንደርስ ዘንድ ንስሐና እምነትን ገንዘብ እንድናደርግ የሚረዳን ነው ። ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን የአንድነት መለኪያዋ ምልጃ ነው ። እግር ሲመታ ላይ ያለው ዓይን የሚያለቅሰው አካል ስለሆነ ነው ። በሰማይ ያሉት ቅዱሳንም ስለ እኛ በማሰባቸው አንድ አካል መሆናችንን ይገልጣሉ ። እጸልይልሃለሁ እያለ የሚናገር ሰው በሰማይ የሚያድሩት ቅዱሳን መጸለያቸው ክርስቶስን ይጋርዳል ብሎ ካሰበ አስቸጋሪ ነው ።

በእርሱ ያመኑ ሕያዋን ናቸውና የሕያውነት ሥራ ይሠራሉ ። ያረፉ ቅዱሳን ሙታን አይደሉም ። ይህ ክርስቶስን የሙታን አምላክ ብሎ እንደ መናገር ነው ። እርሱም በቃሉ፡- “እኔ የአብርሃም አምላክ ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን ? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም ።” ማቴ. 22፡31-32። ይህ ቃል ሲነገር አብርሃምና ይስሐቅ ከሞቱ ሁለት ሺህ ዓመት ሁኗቸዋል ። እነርሱ ግን ሕያዋን ናቸው ። የአብርሃም አምላክ መባልን የወደደ የድንግል ልጅ ስንለው ይበልጥ ደስ ይለዋል ። በክርስቶስ ሆነው የሞቱም በዕረፍት አሉ ። ክርስቶስ ለኑሮአችን ትርጉም ፣ ለሞታችንም አድራሻ ነው ።

አቤቱ በሃይማኖት ሁነው ያረፉን አባቶቻችንን አስብ ። እኛንም አምነን ለመሞት የበቃን አድርገን ። አሜን ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /14

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም.

እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ