ፍልፈል ስትወለድ በጣም ነጭ ናት ። አባቷ ግን አፈር ላፈር ስለሚኖር በጣም ይጠቁራል ። ፍልፈልም የራሷን ንጣት የአባቷን መጥቆር አየችና “አንተማ የእኔ አባት አትሆንም” አለችው ። ከአባቷም ሸሽታ አባት ስትፈልግ ፀሐይ በሁሉ ሰልጥና ታየቻትና አባት ብትሆነኝ ብላ አሰበች ። “ፀሐይ ሆይ አባት ሁኚኝ ?” አለች ። ፀሐይም፡- “አባት እሆንሽ ነበር ፣ ነገር ግን እኔን ደመና ያሸንፈኛል ፤ ብርሃኔን ወደ ምድር ስለቅቅ እያለሁ እንደሌለሁ ያደርገኛል” አለቻት ። ፍልፈልም እንግዲያው ደመና አባት ቢሆነኝ ብላ ደመናን፡- “አባት ሁነኝ ?” ብላ ጠየቀችው ። ደመናም ፡- “አባት ብሆንሽ ደስ ይለኝ ነበር ፣ እኔን ግን ነፋስ ያሸንፈኛል” አላት ። ፍልፈልም የነፋስን ኃያልነት ሰምታ ነፋስን አባት እንዲሆናት ጠየቀችው ። ነፋስም፡- “እኔ አባት ብሆንሽ ደስ ይለኝ ነበር ፣ እኔን ግን ተራራ ያሸንፈኛል ፣ ሁሉን ጥሼ ስመጣ እርሱ ይገድበኛል” አላት ። ፍልፈልም ወደ ተራራ መጣችና “አባት ሁነኝ?” አለችው ። ተራራም አባት ቢሆናት ደስ እንደሚለው ነገራትና ችግሩ ግን “እኔን ፍልፈል ያሸንፈኛል ፣ በዚህ ቆፍሮ በጀርባዬ ይወጣል” አላት ። በዚህ ጊዜ የፍልፈል ልጅ ወደ አባቷ ሄዳ ይቅር በለኝ አለችው ። ፍልፈልም፡- የሰው አባት ፣ አባት አይሆንም ፣ ትንሽ የመሰለሽ ያንቺ አባት በሩቅ ባሉት ዘንድ የተከበረ ነው” አላት ይባላል ።
ፍልፈል የዛሬው ንጣቷ ወደ ጥቁረት እንደሚለወጥ አላወቀችም ። ሁሉም ፍልፈል ሲጀምር እንደ እርስዋ መሆኑን አታውቅም ። ዓለም ጥቁር ጭቃ ይዞ እንደሚጠብቅ አላስተዋለችም ። ገና አዲስ ሯጭ ፣ ገና አዲስ ግልብጥ ናት ። የቆየው ማረሩ አዲሱ ግልብጥ መንጣቱ እሳቱ እስኪያገኘው ነው ። አባቷን ያጠቆረ እርስዋንም እንደሚያጠቁር ገና አላወቀችም ። ትልቁን የደፈረ እርስዋን የሚያፍር መሰላት ። በተወለደችበት ቀን ኑሮን መመዘን ፈለገች ። በእንግድነት ቀኗ አባቷን መለካት ጀመረች ። “ሀ” ግእዝ ስትል ሊቁን መተቸት ፈለገች ። እንደ አለማወቅ ደፋር የሚያደርግ ምን አለ ? እርስዋም ገና እንደምትጠቁር ፣ እርስዋም በልጇ እንደምትጠላ አልገባትም ። የአባቷ ጥቁረት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው እንደዚህ የነበረ መሰላት ። የእርስዋም ንጣት ሁልጊዜ የሚኖር መስሎ ተሰማት ። የጠቆረው ነጭ ነበረ ፣ የነጣውም መጥቆሩ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የሚቀር አይደለም ። የዛሬው መንጣት ለጊዜው ነው ። ፍልፈል ከነንጣቱ ልኑር ቢል ምግቡንም ማደሪያውንም አያገኝም ። ነጥቶ ለአንድ ቀን ከመኖር ፣ ጠቁሮ ለብዙ ዘመን መኖር አለበት ። የፍልፈል ልጅ ግን ገና አዲስ ጎብኚ ናትና ስለ መጥቆር ትተቻለች እንጂ ለምን እንደ ጠቆረ አታውቅም ። ነገ እርስዋንም የሚጠብቃት ዓለም መሆኑን አትረዳም ።
አባት ፍለጋ ወደ ፀሐይ ሄደች ። ፀሐይ በሁሉ የሰለጠነች መሆኗን ደግሞም ልዕልናዋን አይታ መረጠቻት ። ፀሐይ ግን ራስዋ የምታውቀው ሌላው ግን የማያውቅላት አሸናፊ አላት ። እርሱም ደመና ነው ። ብርሃኗን ጨለማ ፣ ሙቀቷን ብርድ የሚያደርግ ፣ ከምድር የሚለያት ፣ እያለች እንደሌለች የሚያደርጋት ደመና አለባት ። ትንሹ ደመና ትልቋን ፀሐይ ይጋርዳል ። የጥላ ጦርነት መቋጫ የለውም ። እንኳን አፈር ላፈር የሚሄደው ፍልፈል ለካ ፀሐይም አሸናፊው ደመና ሲመጣ ትጠቁራለች ? ደመናም የሚዋደዱትን ፀሐይና ምድርን ፣ ሰውና ብርሃንን እንደለየ አይኖርም ። ሁሉ የራሱ ትግል ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚሸነፍበት የራሱ ደካም አለው ። በአንድ ነገር አሸናፊ የሆነ በሌላው ነገር ተሸናፊ ነው ። ደመና ፀሐይን ቢያሸንፍ እርሱ ግን በነፋስ ይሸነፋል ። ነፋስ የተባዘተውን ደመና ፣ የተቆለለውን የአየር ላይ ኩንታል ይበትነዋል ። የደመና አቅሙ መሰብሰብ ፣ መከመር ነበር ። ነፋስ ግን ይበትነውና አየር ያደርገዋል ። ንጣቱንም ጥቁረቱንም ይወስደውና መጋረጃነቱን ይቀደዋል ። ነፋስም ሁሉን ማቅለል ልማዱ ነው ። የሚከብደው ሁሉ በነፋስ ፊት ገለባ ነው ። ቤቱን እየጠረገ ፣ ማዕበሉን እያስገመገመ መሬትን ባሕር ፣ ባሕርንም መሬት ያደርገዋል ። ነፋስ ኃይለኛ ነው ። እርሱም ግን በጸናው ተራራ ይሸነፋል ። አገር አልባው ነፋስ ፣ አድራሻ ባለው ተራራ ይገደባል ። ተሸክሞት የመጣውን ተራራው ጋ ሲደርስ አፍሮ ይጥለዋል። ሩቅ አገር እደርሳለሁ እንዳላለ በአጭር ርቀት ይቀራል ። ተራራ የእግዜር ፎቅ ነው ። ከፍታንና ስፋትን የያዘ እንደ ተራራ ማን አለ ? በርግጥ የእግዚአብሔር ልዕልና በተራራ ፣ ጥልቀቱም በውቅያኖስ ፣ ከፍታውም በአርያም አይለካም ።
ተራራም ዛሬ የጀመሩ ሰው ሠራሽ ዋሻዎች ፣ የባቡርና የመኪና መንገዶች ሳይመጡ በፍልፈል እየተቦረቦረ ሆድና ጀርባው አንድ ይሆን ነበር ። የሰፋውና ከፍ ያለው ተራራ በትንሹ ፍልፈል ይሸነፋል ። አልነካም ባይነቱ ያበቃል ። ለካ በሁሉ የሰለጠኑ የመሰሉት የሰለጠኑ አይደሉም ። ለካ ብርሃንን እንጋርዳለን የሚሉት መጋረጃቸው በማይታየው ነፋስ ይበናል ። ሁሉን ያቀለለውና ተሸክሜ ልሂድ ያለው ነፋስም በተራራ ይገደባል ። በጽናቱ የተንጣለለው ተራራ ለካ በትንሹ ፍልፈል ሆድ ዕቃው ይዘረገፋል ። አዎ አባት የሚሆነው ያ የወለደው ነው ። አባትነት ምርጫ አይደለም ። የእገሌ አባት ለመሆን ፣ የእገሌም ልጅ ለመሆን የመረጠ ማንም የለም ። አባትነት የሚሰየመው ከታላቁ አባት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው ።
ፍልፈል የዕለት መልኳን በዘመናት የአባቷ መልክ ለካችው ። አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል ይባላል ። አዲስ ተማሪም ሁሉን ይንቃል ። አዲስ አስተማሪም ሁሉን ይነቅፋል ። የራሱ ንጣት ፣ የሌላው ጥቁረት ጎልቶ ይታየዋል ። መንጣቱ ልክ ነው ። ዕድሜው የዕለት ስለሆነ ነው ። ያኛው መጥቆሩ የከረመበት ትግሉ ነው ። ተራራ መግፋቱ ያጠቁራል ። ትልልቆቹ አስተማሪዎች ሲበሳጩ አዲሱ አማኝ “እንዴት ?” ይላል ። የዕለት መልክ በዘመናት መልክ ይገረማል ። ጥቁሩም የጀመረው ከነጩ ነው ። ነጭ መነሻ ነው ። መድረሻው ነጭ እንዲሆን ካልጸለይን መካከሉ ላይ የማይጠቁር ማንም የለም ። በእውነት ዛሬ የ30 ዓመት አብያተ ክርስቲያናት የሦስት ሺህ ዓመት አብያተ ክርስቲያናትን ሲነቅፉ ይገርማል ። የአራት መቶ ዓመታት ታሪክ ያላቸው አገራት የአምስት ሺህ ዓመት ታሪክ ያላቸውን አገራት ለማጥፋት ሲሹ በጣም ያስደንቃል ። የእነዚህም እርጅና ወጉ ፣ የእነርሱም አዲስነት እውነቱ ነው ። በወጉ ማርጀት ፣ በወጉ አዲስ መሆን ደስ ይላል ። ስለ ሃይማኖትም ከምዕራብ አይጠየቅም ። የሃይማኖት መገኛው መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ነው ። ሁሉም እምነት የበቀለው ከዚህ ስፍራ ነው። ከምዕራብ የተገኘው በአብዛኛው ክህደት ነው ። በዘመናዊነት ቢመሰገኑም በሃይማኖት ግን ተጠያቂ አይሆኑም ። የሃይማኖትን ሥር ለማግኘት እስራኤልን ፣ ሶሪያን ፣ አንጾኪያን፣ ግብጽን ፣ ኢትዮጵያን መጠየቅ ያስፈልጋል ። የእነ አትናቴዎስ ፣ ቄርሎስ ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ፣ ማኅሌታይ ያሬድ መፍለቂያው ይህ ስፍራ ነው ። ምንጭን ፍለጋ ወደዚህ ክልል በእግርም ፣ በአሳብም ፣ በጥናትም መምጣት ያስፈልጋል ።
አባትነት የምኞት ውጤት አይደለም ። ባሕርያዊ ትስስር ነው ። አባትነትም ብዙ ነው ። በሥጋ ፣ በእውቀት ፣ በሃይማኖት ፣ በማሳደግ ሰው አባት ይሆናል። አባት ለመሆን የሚያስፈልገው መውለድ ነው ። ልጅ ለመሆንም መወለድ ግድ ነው ። አሊያ ሽል ነው ። የእኛን አባት ስናይ የኑሮ ጥቁረቱ እንድንርቀው ያደርገን ይሆናል ። የእኛ ንጣት ግን ያለው በዚያ ጥቁረት ውስጥ ነው ። የእኛ አባት መሬት ለመሬት የሚማስን ሊሆን ይችላል ። እንደ ፀሐይ ዝናቸው በዓለም የወጣ ፣ እንደ ደመና መገደብ የሚችሉ ፣ እንደ ነፋስ የሚበትኑ ፣ እንደ ተራራ የሚገድቡ ያምሩን ይሆናል ። ከአገር ቤት ባይወጣም ፣ አቅሙ ደካማ ቢሆንም ፣ እንደ ነፋስ ሌላውን ማቃለል ባያውቅም፣ እንደ ተራራ ኮርቶ ባይቀመጥም እውነተኛ አባት ያ ጥቁሩ ፣ ያ አፈር ላፈር የሚሄደው ነው ። ባሕርያዊ ዝምድና ያለን ከእርሱ ጋር ብቻ ነው። ፀሐይ ስልጡን ፣ ደመና የሚጋርድ ፣ ነፋስ የሚበትን ቢሆን እንኳ ሕይወት ያለው ያ ጥቁር አባት ብቻ ነው ።
አባት የሚሆነን አባት ይሁን የተባለው ብቻ ነው ። በማመልከቻ አባት አይገኝም ። አባትነት ተፈጥሮአዊ ሰንሰለት ነው ። በልደት ማሰሪያ የተገመደ ነው ። ብዙ አባቶች ሊኖሩ አይችሉም ። ለአንድ ሰው አንድ አባት ብቻ አለው ። ሐዋርያው እንዳለው፡- “በክርስቶስ አእላፍ ሞግዚቶች ቢኖሩአችሁ ብዙ አባቶች የሉአችሁም እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ በወንጌል ወልጄአችኋለሁና” ይላል /1ቆሮ. 4፥15/። ብዙ አሳዳጊዎች ሊኖሩ ይችላሉ ፣ በእግዚአብሔር ቃል ግን የወለደን አንድ አባት ብቻ ነው ። የምናወራው አባትነቱ ጥያቄ ውስጥ ስለማይገባው ስለ እግዚአብሔር አይደለም ። አባት ስለሆኑት መንፈሳውያን ወላጆቻችን ነው ። እነዚህን አባቶች ገፍተን አባት ፍለጋ እንዞር ይሆናል ። እንደ ፀሐይ የሰለጠኑ ፣ በዓለም ሁሉ የሚታዩ አባቶች ያምሩን ይሆናል ። ነገር ግን እግዚአብሔር የመደበልን ያ አፈር ላፈር የሚሄደው በትግል የጠቆረው አገልጋይ ነው ። ማንም ሰው ንጉሡ አባቱ ቢሆኑለት ይመኛል ። ነገር ግን አባቱ ያ ድሃው ነው ። ችግሩ ንጉሡን ለአባትነት የሚመኙት ብዙዎች ቢሆኑም ንጉሡ ግን “ልጄ” ሊላቸው አይፈልግም ። ልጄ የሚል የወለደን ብቻ ነው ። ያልወለዱን ልጄ ሲሉን አፋቸው ላይ እየተንቀዋለለ ነው። ቋንቋው ረገጥ አይልም ። ንግግር እንጂ ስሜት የለውም ። ፀሐይ አባት ብትሆን ታሞቅ ይሆናል ። ማቀፍ ግን አትችልም ። ማጥባትም ጸጋዋ አይደለም ። ከፀሐይ ትልቅነት የእኛ አባት ትንሽነት ለሕይወት አስፈላጊ ነው። መለኪያው ከፍታው ሳይሆን ለሕይወት ምን ይጠቅማል የሚለው ነው ? ከፀሐይ መሰልጠን የእኛ አባት የተረሳ መሆን ጠቃሚያችን ነው ። ብዙዎችን ለአባትነት ብንመኝም አባት የሚሆነን ግን የተመኘነው ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ የተመኘልን ያ ሰው ብቻ ነው ።
አንድ ቤተ ክርስቲያን ሲከፈት ሰው ይበዛል ። አረሚ ተጠምቆ ፣ ዓለማዊ ንስሐ ገብቶ አይደለም ። ከገንቦ ገንቦ የሚገላበጥ ነው ። ወጥ ቀማሽ እንጂ ማዕድ ተመጋቢ እየጠፋ ይመስላል ። የጠቆረውን አባት ለፀሐይ የሚያሙ አሉ ። እርሱ ብሔራዊ ብቻ ነው ፣ እንዳንቺ ዓለም አቀፋዊ አይደለም ይሏታል ። ለደመና የሚያሙም አሉ ፣ እርሱ መጋረድና መቋቋም አይችልም። ጥሩ የሰርግ አዳራሽ ፣ ጥሩ የመቃብር ስፍራ የለውም ይላሉ ። ለነፋስ የሚያሙም አሉ ፣ ብዙ ደጋፊዎች የሉትም ፣ ማስታወቂያ ከሌለው ጥሩ ነገር ፣ ማስታወቂያ ያለው መጥፎ ነገር ይሻላል ይላሉ ። ለተራራም ያማሉ። ስፋትና ከፍታ የለውም ። የእርሱ ቤት አነስተኛ ነው ። ታዋቂም አይደለም ይላሉ ። ፀሐይ ግን ስትመክር፡- መሰልጠንም የደመና ጠላት ያመጣል ትላለች ። ደመናም፡- ሌላውን ጋርዶ መቆምም መበተንን ያስከትላል ትላለች ። ነፋስም፡- ሁሉን አቅልሎ ፣ ራስን አጉልቶ ማውራት፣ የጸኑት ፊት ሲደርስ ባዶ መሆን ነው ይላል ። ተራራም፡- ስፋትም በማነስ ፣ ከፍታም በዝቅታ ይጠናቀቃል ብሎ ይመልሳል ። ፀሐይም ያንቺ አባት አታውቂውም እንጂ እኔ የተፈጠርኩት እርሱን እንድመግብ ነው ትላለች ። ደመናም ላንቺ አባት እርካታ ለመሆን ነው ዝናብ የተሸከምኩት ትላለች ። ነፋስም ያንቺን አባት እስከ ዛሬ ማንሣት አልቻልኩም ትላለች ። ተራራም ያንቺ አባት ነው ሆድ ዕቃዬን ከፍቶ የሚያውቀኝ ትላለች ።
የገዛ አባታቸውን ንቀው ሲሄዱ በሄዱበት ስፍራ የሚሰሙት የአባታቸውን ዝና ነው ። አባት ሁኑኝ የሚሏቸው የሚናገሩት ያ የጠቆረውን አባት ጠቅሰው ነው። የምንንቃት አገር ብትጠቁርም አገራችን ናት ። ስለ እርስዋም ብዙ ንቀት ስንናገር ፡፣ አባት ለማግኘት ስንሰድባት እነርሱ ግን የሚሉን ታሪካችሁን ታውቃላችሁ ? ትልቅ ሕዝብ ነበራችሁ ይሉናል ። እውነት ነው ዲሲን የሚያውቀው ኢትዮጵያዊ ደሴን አያውቅም ። ኤፍል ታወርን ያየ የአገሬ ሰው የአክሱም ሐውልትን አልጎበኘም ። ከግእዝ እንግሊዝኛ ፣ ከሳባ ፊደል የላቲን ፊደል የራሱ መስሎት ለሚባዝን አባታችሁ ትልቅ ነው የሚል መልስ ብቻ ያገኛል ። በተነባበረው የአውሮፓ ካቴድራሎች የሚደነቀውን “እናንተ እኮ ሥረ ወጥ የሆነ የላሊበላ ውቅር አላችሁ” ይሉናል ። ስለ አንድ ነገር ጥናት ብንሠራ በእንግሊዝኛ አንድ ሺህ ጥናት ተሠርቶበታል ። ስለ ግእዝና ስለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ብንሠራ ግን ገና ያልተበላ እንጀራ ነው። የራሳችንን አላወቅነውም ። እውቀት በሌለበት ክብር የለም ። ሌሎችን ለማስደሰትና ቤተ ክርስቲያናችን ሠውተን ለመታረቅ ፣ አባት ሁኑኝ ስንላቸው የእናንተ ቤተ ክርስቲያን እኮ ጥንታዊት እናት ቤተ ክርስቲያን ናት ፣ ስለ እርስዋ ብዙ እያጠናን ነው ይሉናል ። የሄዱት እየተመለሱ እኛ ጉዞ ያምረናል ። ለካ የሰው አባት ፣ አባት አይሆንም ? ለካ እኛ የተሰጠን የበለጠው ነው ። የናቅነው የእኛ ስለሆነ ነው ። የቅርብ ጠበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል ። ዳክረን ግን ተመልሰን መምጣታችን አይቀርም ። ተመልሰን የምንመጣው እዚህ ጋ ከሆነ ዛሬ ባንርቅ የተሻለ ነው ።
በሥጋ የወለዱን ወላጆቻችን የእኛ ፊት እንዲያበራ የእነርሱ ፊት በማድያት በልዟል ። ወላጆቻችን ከአገር ያልወጡ ፣ ፊደል ያልቆጠሩ ይሆናሉ ። እነርሱ ግን የእኛ ጀግና ናቸው ። እኛን ለማሳደግ 14ቱን ክፍለ አገር የረገጡ ፣ የቃል ኪዳን ቀለበታቸውን ሸጠው ለዚህ ያደረሱንን መርሳት ተገቢ አይደለም። ብዙ ወንዶች ቅሌታቸው ዛሬም ያባራ አይመስልም ። ሲያገቡ “እማዬ” የሚሉት የሚስታቸውን እናት ነው ። እናታቸውን ፍጹም ይጥላሉ ። አባታቸውን ፍጹም ይክዳሉ ። ትዳራችሁ ወላጆቻችሁን ያስረሳ እንዳይሆን ደግማችሁ አስቡ ። “የእናት ርግማን አጥንት ይሰብራል ፣ የአባት ርግማን መሠረት ያስለቅቃል” የሚባለውን አትርሱ ። ትክክል ነው ።
አዎ አብርሃም ይስሐቅን ፣ ይስሐቅ ያዕቆብን ባረከ ። በረከት ከአባት ይገኛል። ሐረጉን ካልጠበቀ በረከት አይወርድም ። እኛስ በሥጋና በሃይማኖት የወለዱን መርቀውን ይሆን ?
ዘመኑ የወለዱንን የምናከብርበት ዘመን ይሁንልን ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሐሙስ ሚያዝያ 25/2010 ዓ.ም.