የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አትበል

እኔ የትልቅ ቤተሰብ ልጅ ነኝ አትበል። በምድር ላይ እግዚአብሔር ትንሽ ሰው አላስቀመጠም። ትልቅና ትንሽን ያመጣ መጨረሻው የማያምር ሥልጣን፣ አትብሉ የሚለው ምቀኛው  ሀብት ነው። አባቴ ደጃዝማች ፊታውራሪ ነበሩ እያልህ በጉራ ቀንህን አትጨርስ። ሁሉም ጥርኝ አፈር ሆነዋል። ላይመለሱ ሄደዋል። እንዳለ ያለ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የማይሞተው አባት እያለ በሚሞት አባት አትመካ። ይዞ መገኘት እንጂ በነበር መንጠራራት ጥቅም የለውም። ሥልጣን አደራ ነውና ለባለቤቱም አያኮራም። የድሮ ተረት ሲሾም ያልሠራ… የሚል ነበር፣ ዛሬ ግን ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚል ትውልድ  መጣ።  የማይሻረውን ንጉሥ ትተህ በሚሻር ንጉሥ  አትመካ ።

የዐፄ ቴዎድሮስ ልጅ በስደት ሞቷል። የዳግማዊ ምኒልክ የልጅ ልጅ የሆነው ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን ወርዶ 20 ዓመታት በስቃይ ታስሮ ደብዛው ጠፍቷል። የዐፄ ኃይለ ሥላሴ ልጆች አንዳቸውም ከአባታቸው በኋላ አልደላቸውም። የደርጉ መሪ ተሰደዋል። የደመቁ ሁሉ ላይበሩ ጠፍተዋል። እንኳን በሌሉ ባሉ ሹሞችም አትመካ።

ራሴን እጠብቃለሁ አሞኝ አያውቅም አትበል። ሰው የሚሞተው በጥሪ እንጂ በበሽታ አይደለም። ሁልጊዜ የሚታመም ዕድሜው ረጅም ነው፣ ተላምዷልና። ታሞ የማያውቅ ግን አንድ ጊዜ ዕዳውን ሊከፍል ይችላል። የእገሌ መቃብር ሰመጠ አትበል። እግዚአብሔር እንደ ዳታንና እንደ አቤሮን በቁም ሲኦል ማውረድ ይችላል። ዘመኑ ግን የምሕረት ነውና ይታገሠናል። የቆመውን ጨርሰህ የሞተን ማማት ነውር ነው። ሙት አይወቀስም ድንጋይ አይነከስም ። የሞቱት ምስክር የማይሻው ዳኛ፣ ይግባኝ የማይጠየቅበት ፈራጅ ጋ ሄደዋልና አሁን እንኳ ፍርድን ለእርሱ ተውለት።

ትልቅን መሳደብ ትልቅ ያደርጋል ብለህ አታስብ። ስድብ ያንተን ትንሽነት ፣ የጠባይ ድንክነት እንጂ የዚያን ሰው ውርደት አያመለክትም። በኃጢአት ተፈትኜ አላውቅም አትበል።  እግዚአብሔር አጥር ባይሆንልህ የማይደፍርህ ብልግና  አይኖርም ነበር። ቅን ስለ ሆነሁ ሁሉም ነገር ይሳካልኛል አትበል፤ ካንተ ቅንነት የጌታ ቸርነት ይበልጣል። ሰው ሁሉ ይወደኛል አትበል ፣ ሰው ሁሉ የሚወደው ጅልን እንጂ ባለ ራእይን አይደለም ። የሳቀልህ ሁሉ ወዳጅህ፣ ያቆላመጠህ  ሁሉ አፍቃሪህ አይደለም።

እውቀት ሁሉ ይያዝልኛል፣ እኔ እገሌ ግን ማወቅ የተሳናቸው መሃይም ናቸው አትበል። የጥበብና የእውቀት መንፈስ ስላገዘህ እንጂ በራስህ ብቻ ያገኘኸሁ አይደለም። አእምሮን ከነ እውቀቱ የሰጠህን ጌታ አመስግን። ሰው ሁሉ  ንጹሕ አይደለም አትበል፤ ያንድ ቀን ውኃ ብታጣ አንተ ከእነርሱ ትብሳለህ። ደግሞም ሬሳችን ቶሎ የሚበላሽ ፣ ለመጥፋት የምንቸኩል ነን ። እገሌ ተከራይ እኛ ነዋሪ ነን አትበል። ባታውቀው ነው እንጂ ዓለሙ የኪራ፣ ሁላችንም ተከራዮች ነን። ተከራይ እንኳ ሲለቅ ንብረቱን ይዞ ነው፣ አንተ ይህን ምድር ስትለቅ ባዶ እጅህን ትሄዳለህ ።

ያለህን ነገር በምስጋና እንጂ በትዕቢት አትያዘው። የንብረትን ከንቱነት ለማሳወቅ የእግዚአብሔር እጅ በብርቱ ወጥታለች። አዎ ዕራቁቱን የመጣ በካባ፣ ዕራቁቱን የሚሄድ በሀብት ሊመካ አይገባውም።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ