የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አትዋሹ ሀብታም ናችሁ

 አንድ ድሀ ወደ አንድ ገዳም ሄዶ በዚያ ያገኛቸውን መነኩሴ አባት፡- “አባቴ ለምን በጣም ደሀ ሆንኩ ?” ብሎ ጠየቃቸው ። እርሳቸውም፡- “የምትሰጠው ብዙ አለህ እኮ ግን አላወቅከውምን ?” ብለው በጥያቄ መለሱለት ። ድሀውም፡- “የምሰጠው ምንም ነገር የለኝም” አላቸው ። እኒህ አባትም እንዲህ አሉት፡- ከማንም የማያንስ የምትሰጠው ብዙ ነገር አለህ ተመልከት፦

ፊትህ፦ ይስቃል ፥ ይደሰታል ፣ ለኀዘነተኞች ፈገግታህን ያካፍላል !

አንደበትህ፦ ውብ የሆኑ ቃላትን ትናገርበታለህ ፥ ታመሰግንበታለህ ፥ ሰዎችን ታበረታታበታለህ ፥ ትመክርበታለህ ፥ ታጽናናበታለህ !!

ልብህ፦ ለመልካምነት ፥ ለእውነትና ለትሕትናን ክፍት ነው !

ዓይንህ፦ ጎስቋሎችንና ችግረኞችን በፍቅርና በደግነት ትመለከታለች !! በኀዘን ለተዋጠው እንባን ትሰጣለች !

እጆችህ፦ አቅመ ደካሞችን ያግዛሉ ።

ተመልከት ይህን ሁሉ መስጠት ከቻልህ አንተ ደሀ አይደለህም !!

በዚህ ዓለም ላይ ከሌላቸው ሰዎች ይልቅ ያላቸውን ያላወቁ ሰዎች ይበዛሉ ። ያለንን ካላወቅነው ያው ድሀ ነን ። ድህነት ያለው እጅ ላይ ሳይሆን አእምሮ ላይ ነው ። ሁሉም ነገር ያላቸውና ምንም ነገር የሌላቸው ሰዎች በዓለም ላይ የሉም ። ጉድለቱን ያው ባለቤቱ ብቻ ያውቀዋል ፣ ሙላቱንም ሰዎች ብቻ ያውቁታል ። የጎደልንን እኛ ስናውቀው ፣ ያለንን ግን ሌሎች ያውቁታል ። ላወቀበት ፈገግታም ሀብት ነው ። አንድ ትልቅ ባለጠጋ ናቸው ፣ ስማቸውን ብጠራ ታውቋቸዋላችሁ ። ግን ስም አይጠሬ ናቸው ። በጣም ደስተኛና ሳቂታ የሆነ ወጣት ሁልጊዜ ማኪያቶ ይሠራላቸዋል ። አንድ ቀንም  ከመቀመጫቸው ተነሥተው ወደዚህ ወጣት ሄዱና፡- “ልጄ ሁልጊዜ ሳይህ ፈገግታ ሞልቶብሃል ። ያንተን ደስታ እኔ ለአንድ ቀን አግኝቼው አላውቅም ፤ እንደ ተደሰትክ ፣ እንደ ሳቅህ ኑር” ብለው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ ። አዎ ፈገግታ ሀብትና ከሀብትም በላይ መሆኑን እኒህ ቢሊየነር መስክረዋል ። 

ዝነኛ የነበሩት ፖፕ ዮሐንስ ዳግማዊ፡-። “አንድ ሰው የመጨረሻ ድሀ ቢሆንም እንኳ ለሌላው ሊሰጥ የሚችለው ነገር አለው ፤ እንዲሁም ሌላውም በጣም የተረፈው ሀብታም ቢሆንም ከሌላ ሰው መቀበል የሚያስፈልገው ነገር አለ” ብለዋል ። ይህ ዓለም ሙሉ ድሀ ነኝ ፣ ሙሉ ባለጠጋ ነኝ የማይባልበት ዓለም ነው ። እንዳንሳቀቅ የምንሰጠው አለን ፣ እንዳንኮራ የምንቀበለው አለን ። እግዚአብሔር ቅዱስ ሙላትን ፣ እንዲሁም ቅዱስ ጉድለትን በእኛ ውስጥ በማስቀመጡ ሕይወትን ውብ አድርጓታል ። 

በዓለም ላይ ፈግታን የመሰለ ሀብትና ምግብ የለም ። ፈገግ ያሉልን ሰዎች ፀሐይ እንዳበሩልን ናቸው ። ፀሐይ በርቶም የጨለመባቸው ፈገግታን ሲያዩ ይደሰታሉ ። ልባቸው ኀዘን አርግዞ የሚኖሩ ፈገግታ ሲያዩ ይፈወሳሉ ። ዋጋ የለኝም የሚሉ ፈገግታ ሲያዩ ለካ አስደሳች ሰው ነኝ ብለው በራሳቸው ይኮራሉ ። ፈገግታ ከማንኛውም ስጦታ በፊት ከቀደመ ስጦታውን አስደሳች ያደርገዋል ። እውነተኛ ፈገግታ ያሳዩን ሰዎች በዘመናችን ሁሉ አንረሳቸውም ። በፈገግታ እንኳን ሰው እንስሳትም ይፈነድቃሉ ። በፈገግታ ውኃና ዛፍ ሳይቀር ይስቃሉ ። ፈገግ ስንል ቤቱ ይበራል ። የሥራው ቦታ ተወዳጅ ይሆናል ። ፈገግ ስንል ሰዎች ፈገግ ይላሉ ። የዘራነውን ወዲያው የምናጭደው በፈገግታ ብቻ ነው ። በፈገግታ ጠላትን መማረክ ይቻላል ። ላለመደሰት የቆረጠውን ኪዳኑን እንዲያፈርስ ማድረግ ቀላል ነው ። ፈገግታ መንፈሳዊነትን የሚነካ አይደለም ። መኮማተርና መኮሳተር መንፈሳዊነት ከመሰለን ተሳስተናል ። አዎ ምንም ድሀ ብንሆን ፈገግታን መስጠት እንችላለን ። በፈገግታችን የምንቀጥለው ዕድሜ አለና አበርትተን እንያዘው

። 

ብዙ ኀዘን ፣ የልብም ስብራት ያለብን ፣ ቀንበር እንደ ተሸከመ የጎበጥነው ሰዎች ክፉ ተናገሩኝ ብለን ነው ። አንደበት ኃይል አለውና ይጎዳል ። ለመልካም ከተጠቀምንበት በአንደበታችን ማስደሰት ፣ መጠገንና ሰዎችን ነጻ ማውጣት እንችላለን ። በአንደበታችን እግዚአብሔርን ስናመሰግን አካባቢውን መለወጥ እንችላለን ። እኛ ስናመሰግን ሰዎች ራሳቸውን ማየት ይጀምራሉ ። ስናደንቃቸው ኃይልን ይሞላሉ ። ጥሩ ፣ ጥሩ ስንናገርላቸው በደስታ ይሰክራሉ ። በዓለም ላይ በበጎ ጎኑ ያልተጠቀምንበት ነገር ቢኖር አንደበት ነው ። አንደበት የኒውክለርን ያህል ጎጂ ነው ። አንደበት ከተጠቀሙበት ነቢይና ሐዋርያ ፣ ሰማዕት የሚያሰኝ ነው ። በአንደበታችን መልካም መናገር ተገቢ ነው ። ቀድሞ የሚዘጋው እርሱ ነውና ። ዘግይቶ ተከፍቶ ቀድሞ የሚዘጋ አንደበት ነውና መልካም ልንናገርበት ይገባል ። ምንም የምሰጠው የለኝም ማለት ስንፍና ነው ። መልካም ቃል የወርቅ ሳንቲም ነው ። 

ምስኪኖችን በሙሉ ዓይናችን ስናያቸው ችግሬን አወቀልኝ ብለው ይደሰታሉ 

። በአንድ የሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ስጎበኝ፡- “ሕፃናቱ ምን ያስፈልጋቸዋል?” ስል፡- “የሚፈልጉት የሚያያቸውና የሚያቅፋቸው ሰው ነው ። ምግብ እዚህ ይሟላል ፣ የእናት ፍቅር ግን ልንሰጣቸው አልቻልንም ። እባካችሁ መጥታችሁ እቀፏቸው” አሉኝ ። እስካሁን ይህ ድምፅ ውስጤን ያጠቀጥቀዋል ። ለማቀፍ ባለጠጋ መሆን አያስፈልግም ። ሰውን በፍቅር ዓይን ስናየው ይበረታታል ። ዓይንም ፍቅርን ያሳብቃል ። ዓይንም ይናገራል ። በዓለም ላይ በቃላት የሚገለጡ ነገሮች ጥቂት ናቸው ። ቃላት የማይችሉትን ዓይን ይገልጠዋል ። ዓይን ከተጎዱት ጋር አብራ ስታለቅስ የተጎዳው ሰው ኀዘኑን ይተዋል ። መቼም ላይረሳን በልቡ ይጽፈናል ። ከሚያዝኑት ጋር ማዘን ትልቅ ዋጋ አለው ። ለዚህ ባለጠጋ መሆን አያስፈልግም ። 

በጉልበት የምናግዛቸው ብዙ ደካሞች አሉ ። መንገድ የምናሻግራቸው ዓይነ ሥውራን ፣ ገላቸውን የምናጥባቸው የአእምሮ ሕሙማን ፣ ቤታቸውን የምናጸዳላቸው ባልቴት አረጋውያን ብዙ ናቸው ። ገንዘብ መስጠት ባንችል ጉልበት ገንዘብ ነውና ያንን መስጠት እንችላለን ። ለመስጠት ፈቃዱ ካለን መስጠት እንችላለን ። እግዚአብሔር ተቀባይ ብቻ አድርጎ አልፈጠረንም ፣ መስጠት የምንችል አድርጎም ፈጥሮናል ። እባካችሁ ስጡ ። 

ቀኑን ዕለተ ወርቅ ያድርግላችሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጳጕሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም.

https://t.me/Nolawii

እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ