የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተን አንተን ያሉ

በአካል ሦስት ፣ በመለኮት አንድ መባል ገንዘብህ የሆነ ፤ አንድነትህ ሦስትነትህን ያልጠቀለለው ፣ ሦስትነትህ አንድነትህን ያልከፈለው በዘላለም ክብር ውዳሴ ያለኸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ጌታዬ ፣ በእቅፍህ ለዘላለም በፍቅርህ እስከ ወዲያኛው ባሪያህን ሰውረው ። አላመሰገኑኝም ብለህ የማትከፋ ፤ ባለማመስገናችን ግን የኀዘን ጥላ የሚያጠላብን ፣ ራሳችንን በመጥላት የምንሞገት እኛው ነን ። ተፈላጊ ነኝ ብለህም ራስህን ገሸሽ አላደረግህም ። ብዙ ሠራዊት አለኝ ብለህም አትመካም ። ሠራዊትህንም የምትጠብቀው ንጉሥ አንተ ነህ ። ለክብርህ ፍጥረታትን ፈጠርህ እንጂ ክብር ለማግኘት ያበጀኸው አንድም ፍጡር የለም ። የሰገዱልህ ሲያምፁብን ፣ ያመፁብህ ይሰግዱልሃል ። በቃልህ የተማሩ በሰላም ሲመጡ ፣ በመከራ የተማሩም እያለቀሱ ይመጡብሃል ። አንድም ቀን የምሽት ወዳጅ ነኝ ወይ ? ብለህ በርህን ዘግተህ አታውቅም ። የመሸበት አሳዳሪ ፣ ከራሱ ለወጣም ራስህን የምትሰጥ አንተ ነህ ። ከስፍራችን ስንናወጥ መልሰን የምናገኝህ ከስፍራህ ስለማትናወጥ ነው ። በምስኪኑ ቤት ስታድር ክብሬ ይጎድላል አትልም ፣ ድሀውን ስትወዳጅ የልብሱ መቀደድ አያሳስብህም ። አንዱን በመስጠት ሌላውን በመንሣት ትባርከዋለህ ። ሁሉን እንደ አመሉ ታሳድረዋለህ ። የሌለህበት ጊዜና ቦታ የለም ። የሌለሁበት ጊዜና ቦታ ግን እኔ አለኝ ። ውስኑ ማንነቴ ጽንፍ አልባ ለሆነው ጌትነትህ ይገዛል ። ለመቅረብ ለሚያስፈራው ግርማህ ምስጋና ፣ ሊርቁት ለሚያሳሳው ሞገስህ ውዳሴ ይሁን ። የቆለፍከውን የሚከፍት ለሌለ ፣ የከፍትከውን የሚዘጋ ለሌለ ቅዳሴ ይሁን ። በኋለኛው ቀን አገኘዋለሁ የምለው ዘመድ የለም ፣ ከሞት በኋላ የማገኝህ ዘመዴ አንተ ነህ ። ጥቂት ደቂቃ ለማመስገን ጊዜ እያጣሁ ለዘላለም ለማመስገን ገነትን እናፍቃለሁ ። ወገንነቴ ካንተ ጋር ነው ። ሌላውን የወገኑ አፍረዋል ፣ አንተ ያሉ ድነዋል ። ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና /2/
የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ያጋሩ