የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተ ትክክል ነህ

 “ጻድቅ ይሞታል ፥ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም ምሕረተኞችም ይወገዳሉ ፥ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም ።” ኢሳ. 57 ፡ 1 ።

መኖር የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ፣ መሞትም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። መኖር እግዚአብሔርን በምድር ለማክበር ሲሆን መሞትም በሰማይ እግዚአብሔር እኛን የሚያከብርበት ነው ። መኖር ከማኅፀን ዓለም ወጥተን ሰፊውን ዓለም የተቀላቀልንበት እንደሆነ ፣ መሞትም አስጨናቂውን ዓለም ተገላግለን የማያልፈውን ርስት የምንወርስበት ነው ። መኖር ከፍታና ዝቅታ ያለበት ሲሆን መሞት ግን በረጋው ዓለም መክበር ነው ። መኖር ድንቅና ጉድ የምናይበት ሲሆን መሞት ግን እግዚአብሔርን በክብሩ የምናይበት ነው ። መኖር በሥጋ ታስረን ግዳጃችንን የምንፈጽምበት እንደሆነ ፣ መሞት ደግሞ ተፈትተን የእግዚአብሔርን ደስታ የምንካፈልበት ነው ። መኖር ብርሃንና ጨለማን የምናፈራርቅበት እንደሆነ ፣ መሞት ግን ሙሉ ብርሃንን የምናገኝበት ነው ። መኖር እግዚአብሔርን በቤታችን የምንጋብዝበት ሲሆን ፣ መሞት ደግሞ እግዚአብሔር እኛን በእልፍኙ የሚጋብዝበት ነው ። መኖር ያከበረን ሲያዋርደን ፣ የወደደን ሲጠላን የምናይበት ነው ፣ መሞት ግን ከከበሩ ውርደት ፣ የተወደዱ መጠላት የሌለበትን የእግዚአብሔርን ግዛት መውረስ ነው ። መኖር “ብወድቅስ ?” የምንልበት የአፋፍ ላይ ጉዞ ነው ፣ መሞት ግን በጉ በሚያበራበትና እንቅፋት በሌለበት ሰማይ መሆን ነው ። መኖር ሞላ ጎደለ የሚል የቁማር ኑሮ የምንጫወትበት ነው ፣ መሞት ግን ከታላቁ እራት ከበጉ ሰርግ የምንታደምበት ነው ። መኖር ሐሰተኛ ወዳጆችና እውነተኛ ጠላቶችን የምናፈራበት ነው ፣ መሞት ግን እውነተኛ ወዳጆች የሆኑት ቅዱሳን መላእክትን የምናገኝበት ነው ። መኖር ጥላቻ በሞላበት ዓለም መቍሰል ያለበት ነው ፣ መሞት ግን ፍቅርን ከተሞላች ከብርሃን እናት ከድንግል ማርያም ጋር የምንሆንበት ነው ። 

ባንወለድ ኑሮ ይህን ዓለም እንደማናየው ፣ ካልሞትንም ያንን ዓለም አናየውም ። በምጥ እንደ ተወለድን በጣር ይህን ዓለም እንለቃለን ። በማኅፀን ዓለም አካላዊ ዝግጅት ባናደርግ በዚህ ዓለም መኖር አንችልም ነበር ፣ በዚህ ዓለምም መንፈሳዊ ዝግጅት ካላደረግን በሰማይ ደስታ አናገኝም ። መኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ መሞትም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ እየተማርን ፣ በየዕለቱ ከማናውቀው አዲስ ነገር ጋር እየተላመድን ነው ፣ ተማሪ ለራሱ ደውሎ ከትምህርት ቤት መውጣት አይችልም ፣ ሰዓቱ ሲደርስ ግን ሥልጣን ያለው አካል ሲደውልለት ይወጣል ፤ በሞት ደወልም ራሱን የሚጠራ ሰው ሊኖር አይገባም ። ሰዓቱ ሲደርስ ባለሥልጣኑ ጌታ ደውሎ ይጠራዋል ። 

ናማ ናማ ብለህ ባታቻኩለኝ ፣

እዚያ እመጣለሁ ቀሪ ቤት የለኝ ፤ 

የተባለው ለዚህ ነው ። መሰንበት እንጂ መቅረት የለም ። ለሞቱት ያለቀስነው ስለቀደሙን እንጂ ስለቀረን አይደለም ። 

ከቶ አይቀርም ሞቱ ፣

ምን ቢሰነብቱ ፤ 

እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛ ሰዎችን በሞት የሚወስደው ዓይኖቻቸውን ከእንባ ፣ እግሮቻቸውን ከጥፋት ፣ ሰውነታቸውን ከኃጢአት ሞት ለመሰወር ነው ። ደጋግ ሰዎች መሞታቸው ብዙ ጊዜ ጥያቄ ይሆንብናል ። እግዚአብሔር ግን ቀጣዩን ክፉ አይተው ልባቸው አይሰበር በማለት በሞት ይሰውራቸዋል ። ጻድቃን በሞት በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ ይሆናሉ ። ይህ እቅፍ ፣ ያቀፈውን ገፍትሮ የማያውቅ ፣ የፍቅር ሙቀት ያለበት ነው ። 

ብዙ ነገሮችን አናስተውልም ። ከማናስተውላቸው ነገሮች አንዱ ደጋግ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ ነው ። በክፉዎች መካከል ጻድቅ ነፍሳቸውን ሲያስጨንቁ የኖሩ ፣ በሚያዩት ክፉ ፣ በሚሰሙት መርዶ የሚያዝኑ ደጎች እግዚአብሔር ያርፉ ዘንድ በሞት ይጠራቸዋል ። ትላንት የሞቱት ደጋግ ሰዎች አመለጣቸው የምንለው ምን ነገር አለ ? በክብር ስለማለፋቸው ፣ በፍቅርም ስለመቀበራቸው ማመስገን ይገባናል ። ከሞትም ሞት በሚመረጥበት ፣ ሰው አውሬ ሁኖ ሰውን በበላበት ዘመን እነዚያ ያለፉ ደጋጎች እግዚአብሔር እንደሰወራቸው ማስተዋል ይገባናል ። 

ታላቁ የመከራ ዘመን የሚባለው ሦስት ዓመት ከመንፈቅ የሚፈጀው የክርስቶስ ምጽአት ዋዜማ ነው ። ይህ ታላቅ የመከራ ዘመን ያጠረው ስለተመረጡት ምርጦች ነው ። /ማቴ. 24 ፡ 22 ፤ ራእ.13 ፡ 5 ።/ እግዚአብሔር ወዳጆቹን ላለማሳዘን ለክፉዎች በሚገባቸው መጠን መዓቱን አያፈስባቸውም ። የቅዱሳን ጸሎት የእግዚአብሔርን ቍጣ ይከለክላል ። ነቢዩ ሙሴን አስታውሶ በዘመረው ዝማሬ ላይ፡- “እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ” ብሏል ። /መዝ. 105 ፡ 23 ።/ በታላቁ የመከራ ዘመንም የመከራ ጽዋ የሚፈስሰው መከራውን እንዳያዩ አማንያን ስለሚሰወሩና ምድርን በጸሎት የሚከልል ስለማይኖር ነው ። እግዚአብሔር ስለተመረጡት መከራን የሚያሳጥር በመሆኑ የተመረጡት መኖራቸው ይጠቅመናል ። ጻድቃንን መውሰዱም ለወዳጆቹ ማሰቡን ያሳያል ። ቅዱሳን ለራሳቸው ከሚኖሩት ለእኛ የሚጠቅሙት ይበልጣል ። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና ፤ ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው” ብሏል ። /ፊልጵ. 1 ፡ 23 – 24 ።/ መኖርና መሄድ ሁለቱም እኩል ፣ እኩል ሆነውበት ተጨንቋል ። እኛ እኩል ፣ እኩል የሆኑብንን ነገሮች ለመምረጥ ዕጣ እንጥላለን ። እኛ የሚያስጨንቀን መንገድ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሊሆን ይችላል ። ይህን ማንነት ይዘን ነው ቅዱሳንን መናቅ ያበዛነው ። ሐዋርያው መሄዱ ለእርሱ ጥቅም ለአማንያን ግን ጉዳት መሆኑን አልሸሸገም ። የእግዚአብሔር ሰዎች መኖራቸው ጥቅሙ ለእኛ ነው ። የሚያጽናኑን ፣ የሚያስተምሩን ፣ የሚጸልዩልን ናቸውና እጅግ ያስፈልጉናል ። 

ደጋጎች መሞታቸውን እኛ እናውቃለን ፣ ለምን እንደ ተጠሩ ግን እግዚአብሔር ያውቃል ። የወዳጆቹን ልብ ከስብራት ፣ የጻድቃንን ዓይን ከኀዘን ለመጠበቅ እግዚአብሔር እልፍ ያደርጋቸዋል ። ስለዚህ ምሥጢሩ እግዚአብሔር ጋር ነው ብለን መደሰት እንጂ ማዘን አይገባንም ። በርግጥም ስለ ደጋጎች የምናዝነው ጥቅሜ ቀረ ብለን እንጂ ቀረባቸው ብለን አይደለም ። እኛም በደግነት ይህን አጭር ዘመን እንድንፈጽመው መለመን እንጂ ላለፉት ደጎች ማዘን አይገባም ። ሐዋርያው ልሄድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ አለ ። ሞት መንገድ ነው ። መንገድ ግብ ያለው ነገር ነው ። ሞትም ከምድር ዕድርና እቁብ ተለይተን ከአእላፋት ማኅበር ፣ ከጻድቃን መንፈሶች ጋር የምንቀላቀልበት ፣ ከጽዮን ሙሽራ ከክርስቶስ ጋር የምንኖርበት ነው ። /ዕብ. 12 ፡ 22-24 ።/ ቅዱሳን ሁሉ ናፍቀው ሄዱ እንጂ ይህች ዓለም አትቅርብኝ ብለው አላለቀሱም ። 

ዛሬ እንደ አዲስ ቃል ሁኖ ማራናታ ጌታ ሆይ ቶሎ ና እንላለን ። ትንሽ ሲረጋጋ ደግሞ ቶሎ አትምጣ እንላለን ። አፋችን ቶሎ ና ይለዋል ፣ እስስት ዓለም ስትለዋወጥ ደግሞ ልባችን ባይመጣ ይመርጣል ። እርሱ ግን የሚመጣው የልባችንን ትርታ አዳምጦ ሳይሆን እመጣለሁ ያለውን ተስፋውን ለመፈጸም ነው ። እኛም ግደለኝ ከማለት ሥራዬን አስፈጽመኝ ማለት ይገባናል ። ለማንኖርበት ዓለም ብዙ እየደከምን ወደምንኖርበት ዓለም ባዶ እጃችንን እንዳንሄድ ማሰብ ያስፈልገናል ። 

የብሉይ ኪዳን በዓላት በቤተ መቅደሱና በቤታቸው እንዲከበሩ ሁነው የተዋቀሩ ናቸው ። በቤተ መቅደሱ የሚከበረው በዓል እግዚአብሔር ልጆቹን በቤቱ የሚጋብዝበት ሲሆን ፣ በቤታቸው የሚያከብሩት በዓል ደግሞ እግዚአብሔርን በቤታቸው የሚጋብዙበት ነው ። ይህ የቤተሰብ መገለጫ ነው ። ወላጆች ልጆቻቸውን በቤታቸው የሚቀበሉበት ቀን አለ ፣ ልጆችም ወላጆችን የሚቀበሉበት በዓል አለ ። መኖር እግዚአብሔርን የምንጋብዝበት ፣ መሞት ደግሞ እርሱ እኛን የሚጋብዝበት ነው ። በምድር ላይ የእኛ ደስታ አለ ፣ በሰማይ ግን የጌታ ደስታ አለ ። “አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ ፤ በጥቂቱ ታምነሃል ፥ በብዙ እሾምሃለሁ ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” የምንባልበት ነው ። /ማቴ. 25 ፡ 21 ።/

እግዚአብሔር ሆይ ስላለፉት ደጎች አንተ ትክክል ነህ ። የእኛንም ፍጻሜ አንተ አሳምረው !!!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ነሐሴ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ