የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተ አንተ ነህ !

ያህዌ እኔ ፣ እኔ ነኝ በል ። አንተ ብቻ አንተ ነህና ። ሰውማ ፣ እርሱ እርሱ አይደለም ። ቀን ለሌሊት ሰውና አውሬ ሁኖ ይለዋወጣል ። የበጀን አለመተዋወቃችን ፣ ጠብን ያዘገየው ተሸፍነን መኖራችን ነው ። በተላጥን ቍጥር ብዙ ክፍል ያለን ሽንኩርት ነን ። ዕርቃንህን ተሰቅለህ የምታምር ኢየሱስ ሆይ አንተ ብቻ ነህ ። ካባ ለብሰን ፣ በሐር ደምቀን የምናስቀይም እኛ ነን ። አዎ እኔ ፣ እኔ ነኝ በል ። እርግጠኛ ነገር ባጣንበት ዓለም ላይ እርግጥ ሁንልን ። የብሱ እንደ ባሕር ፣ ቀኑ እንደ ሌሊት እንዳይሆንብን እኔ ነኝ በለን ። የሚያስፈራው እንዳስፈራን እንዳይቀር ፣ ቍስል ወደ ጥዝጣዜ ፣ ደሙም ወደ መመርቀዝ ፣ ሰንኮፉም ወደ ነቀርሳ እንዳይሄድብን እኔ ነኝ በለን ። እኛ እኛ ባንሆንም ፣ አንተ አንተ ነህና እንጽናናለን ። ሁላችን ስናብድ ታረጋጋናለህ ። እኔ ነኝ ባይነትህን ፣ ከሺህ ዘመን በፊት የተናገርህበት የድምፅህ ያውነት ይማርከናል ። ሸምግለህ የምትጦረን ፣ በዘመን አርጅተህ የምታድሰን አንተ ብቻ ነህ ። አዎ እኔ ነኝ በለንና ቃላባዮችን እንርሳቸው ። ፎክረው አለሁ ብለውን ፣ ምለው ሲክዱን በጸናው ጽናትህ አቁመን ።

“መንፈስን ሁሉ አትመኑ” ተብለናል ። አንድ መንፈስ የምናምንህ አንተ ነህ ። ጊዜ አይገድብህም ፣ መነሻ የለህምና ። ስፍራ አይወስንህም ፤ ሰማያት ባንተ ውስጥ ናቸውና ። ከስፋትህ የሰፋ ፣ ተርፎ የወጣ ማንም የለም ። ብርሃን ፣ ነፋስና ሙቀት ሁሉም ዓለምን ቢሞሉም አይገፋፉም ። ፍጹማን የሦስትነት አካላትህም ዓለምን ሞልተዋል ፣ መገፋፋት የለባቸውም ። አንተ አንተ ነህ ። ዕጣ አውጥተው ልብስህን የተካፈሉህ ፣ ዕጣ ሳታወጣ ግን ሁሉንም የወደድካቸው አንተ እንደ ራስህ ነህ ። የተደረገለት ያመሰግንሃል ። ትኩስ እንጀራ ከቆረስክላቸው የድሀ ልጆች ወገን ላንተ ምስጋና ይገባሃል ። ባለማወቅ ለጠፋው ዓለም ብርሃን ይሆኑ ዘንድ ሰባክያንን የላክህ እንዴት ድንቅ ነህ ! አንተ አንተ ነህ ፤ ለሚገድሉህም ምሕረት ትሰጣለህ ። ሞት አይለውጥህምና ሞትን ትቋቋማለህ ። እጆቻችን ሲያጥሩ እጅህ በሚያፈስሰው በረከት እንጠግባለን ።

አንተ ፣ አንተ ነህ ። እኛን ደስ ለማሰኘት ያለቀስህ ። ያስለቀስከው ምስኪን የሌለ ገዥ አንተ ብቻ ነህ ። የጠፋውን አዳም ወደ ቤቱ ልትመልሰው ቤት አልባ ሁነህ ኖርህ ። እኛ ቸግሮን እንቸገራለን ፣ አንተ ወደህ ፈቅደህ የባርያን መልክ ያዝህ ። እንደ ሰው መኖርና መሞት ብቻ አይደለም ፣ ላንተ ሰው መሆን በራሱ ድህነት ነው ። አንተ ካልወረድህ ወደ ላይ አንወጣምና ስለ እኛ ዝቅ አልህ ። መሪዎች ካልወረዱ ሕዝብን ከፍ አያደርጉትምና ፣ ዝቅ ብለው ድሀን ካላዳመጡ ዕንባ አይቆምምና ልታስተምራቸው ትሑት ሆንህ ። አዎ አንተ ፣ አንተ ስለ ሆንህ ዳንን ። ዋጋ እንዳትሰጠን ምን አለን ብለህ ነው ! ዋጋ የሆንከን እኛ እናመሰግንሃለን ። ማነው ጥፋተኛ እያልን የምንኰንነውን ተርበን እናስሳለን ። ጋዜጣው ፣ መርማሪው ፣ ዳኛው ፣ ሕዝቡ ጥፋተኛን ያነፈንፋሉ ። እገሌ በደለኛ ነው ካላሉ እንቅልፍ አያገኙም ። ቍስል ያለበት የሌላውን ቍስል ሲያይ ይደሰታል ። አንተ ግን አንተ ነህ ። አንተ ብቻ ቅዱስ ነህ ። የምቀድሰው ማነው እያልህ በር ታንኳኳለህ ። አዎ አንተ አንተ ነህ ቀን ሳያደክምህ ፣ ምሕረት ሳያልቅብህ ትኖራለህ ! ፍንጭ ፍለጋ የመጣውን ምንጭ ታወርሰዋለህ !

አንተ ፣ አንተ ነህ ። በሰው ቍስል ላይ እንጨት አትሰድድም ። ያሰቃየን ሕሊና አንተ ስትናገር ዐረፈ ። የተማጸኑንን የጨከነባቸው ያ ልብ ዛሬ በጎዳናው ሲያልፍ መራራት ጀመረ ። የልብ ፈዋሽ ሆይ ፈጥነህ አዳንከን ። አንተ አንተ ነህ ። የጋበዙህን እነ ማርታን ሙት ቀስቅሰህ ታስደስታለህ ። ያሳሰበን እኛ እኛ ስለሆንን ነው ። አንተ አንተ ነህና የሚያሳስበን ጭንቅ የለም ። የተሰቀልከው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ ወላዴ አእላፍ ፣ ኃጥአንን ያጸደቅህ በግድ ሰማይና ምድር ይገዙልሃል ፣ እኛ በፈቃዳችን እንወድሃለን ። ልዕልናህን የሚያስጥል መንፈስ ከእኛ ይራቅ ። ቅርበትህን የሚንቅ ልቡና ከእኛ ይወገድ ። ለዘላለሙ አሜን ! የእኔ ዘመን እርሱ ነው የሚል እልልታ ይሠዋልህ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም.

 

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ