አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም” መዝ 101፣ 27
እግዚአብሔር በህልውናው ፣ በባሕርይው ፣ በአንድነቱ፣ በሦስትነቱ፣ በመለኮታዊ ግብሩ ጽኑ ነው። በባሕርይው መለወጥ የለበትም። እርሱ ራሱ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” ብሏል ( ሚል.3፥7 )። ብዙ ሰዎችና ሁኔታዎች ደርሰን ስንመለስ፣ ቆይተን ስንመጣ፣ ተኝተን ስንነቃ ከስፍራቸው ይታጣሉ። የቦረቅንበት መንደር ፣ የሕፃንነታችን መፈንጫ ከዓመታት በኋላ እንዳልነበር ሆኗል:: ያሳደጉን ሽማግሌዎች ፣ ለእኛ መልካም ያደረጉ ደጎች ትዝታቸው እንጂ ህልውናቸው አይገኝም። እነርሱ ከቦታቸው የሉም፣ እኛም አንድ ቀን ከቦታችን እንታጣለን። በአባቶቻችን ዘመን የነበረ ፣ በልጆቻችን ዘመን የሚኖር የሁልጊዜ አዲስ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በሚያረጅ ዓለም ውስጥ የሚያጽናናው የእርሱ አዲስነት ብቻ ነው።
ዛሬ በእግር የምንጓዝባቸው፣ በመኪና የምንፈስባቸው ጎዳናዎች አንድ ዘመን የባላባቶች ሳሎን፣ የጎበዞች ማደሪያ ክፍል ነበሩ። ይህ ዓለም የሚገዛው ለለውጥ ሕግ ነው። ለዚህ የለውጥ ሕግ አእምሮአችንን ካላሰናዳን ብዙ ነገሮች ግራ ሊያጋቡን ይችላሉ። የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነው። እግዚአብሔር ግን ሰማይ ዘፋኑ፣ ምድር መከዳው (መደገፊያው) ሆኖ ለዘላለም ይኖራል። የሌለበት ቦታ የለምና የሚታጣበት ስፍራ አይኖርም።
የትላንት መልካችንን ዛሬ እናጣዋለን። ጥቁሩ ፀጉር ሽብቷል ፤ የጠራው ፊታችን ተሸብሽቧል። ለስላሳው እጃችንና ልባችን ሻክሯል። ያ ጽኑ ጉልበት ደክሟል። እንዳለ ያለ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
የነበረው እንዳልነበር ለመሆን ይቸኩላል። ሙዝየም የገቡ ቅርሶችና ዐፅሞች በአንድ ዘመን አስፈሪ ነበሩ። ዛሬ ግን መፈራታቸው ወድቆ በመስተዋት ተዘግተው ይጎበኛሉ። ዓለም ነበር ለመባል ይቸኩላል። እግዚአብሔር ግን ሕያው ነውና ነበር አይስማማውም::
የዛሬ ክፉዎች ትላንት እጃቸውን ቁርጠው የሚሰጡ ደጎች ነበሩ። የእያንዳንዱ ቀን ተግዳሮት ጠባያችንን ሊነጥቀን ይታገለናል። ቁጠኛ የነበሩ አግብተው፣ ወልደው ቀዝቃዛ ሆነዋል። እግዚአብሔር ግን ጠባዩ የማይጨምር የማይቀንስ ጽኑ ነው። የመታመኛ አምላክ የሆነውም በጠባዩ የጸና በመሆኑ ነው።
የጋራ የቃል ኪዳን አገሮችና ጦሮች ፈርሰዋል። አንድነትን አንድ ዓይነት ለማድረግ የፈለጉም ብዝኃነትን ሰርዘዋል፡፡ የራሳቸውን ቋንቋና ባሕል በኃይል ጭነዋል። እግዚአብሔር ግን በማይጨፈለቅ ሦስትነት፣ በማይበታተን አንድነት ለዘላለም ይኖራል ።
ሺህ ዓመት ንገሥ የተባለ ንጉሥም ዓመቶች ያልቁበታል። ብዙ ውጥን የነበራቸው ሊቃውንትም መቃብር ገብተዋል። እግዚአብሔር ግን ዓመቶች አያልቁበት ዘላለማዊ፣ አይለወጥ የሁልጊዜ ያው ነው። የሰዎች መለዋወጥ፣ የሁኔታዎች መደፍረስ ግራ ሲያጋባን “አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም” ብለን እንዘምር። እኛ አሮጌና አዲስ ዓመት እንላለን። እግዚአብሔር ግን በዘላለም አዲስነት ይኖራል።
ጸሎት
አንተ ያው ስለ ሆነህ የትም ዞረን ስንመጣ እናገኝሃለን። ስንለወጥ ብትለወጥ አናገኝህም ነበር። ታይቶ ለመጥፋት በሚቸኩለው ፣ ሕልም እልም በሆነው ዓለም ከመደናገር ባንተ ድነናል። ዓመቱን ባርክል። በፈሰሰው ደምህ ለዘላለሙ አሜን!
ዕለተ ብርሃን 3
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 3 ቀን 2016 ዓ.ም.