የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንተ ግን ያው አንተ ነህ

“አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም ከቶ አያልቁም።” መዝ. 101፡27 ።
ስላደረግህልን ምስጋና እናቀርብልሃለን ፤ ግን ያላደረግህልን ምን አለ ? ሰለሰጠኸን ነገር ሁሉ ተመስገን እንላለን ፣ ግን ያልሰጠኸን ምን አለ ? ይህች ሰዓት ፣ በእጃችን ያለችው ጥቂት ነገርም ያንተ ናት ። አሁን እንኳ ስምህን ለመጥራት አንደበታችንን ስለፈታኸው ፣ ለምስጋና ለመቆምም ዕድሜአችንን ስለቀጠልኸው ነው ። የማይገባንን ሰጥተህ ደስ የምታሰኘን ፣ ዳርቻ ሳይርቅህ ካለንበት የምትጎበኘን ፣ መጋረጃ ሳይከልልህ ኑሮአችንን የምታይልን ፣ ቁልፍ ሳያሻህ የልባችንን ምሥጢር የምታውቅልን ጌታ እናመሰግንሃለን ። ክረምትን በጋ ይተካዋል ፣ እርጥበቱ ለትኩሳት ፣ ረግረጉ ለደረቅ ተላልፎ ይሰጣል ፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ። ሌሊቱን ቀን ፣ ቀኑንም ሌሊት ስታደርገው አይቸግርህም ። ማታው ሲያልፍ የተደበቀው ይወጣል ፣ ቀኑ ሲያልፍም የሚፋንነው ይገባል ። አንተ ግን በአንዲት ብርሃን ደምቀህ ትኖራለህ እንጂ አትለዋወጥም ። ፈርዖን በኤርትራ ባሕር ሰጥሟል ፣ ናቡከደነፆርም እንደ በሬ ሣር ግጧል ። አንተ ግን በማይጎድል ክብር ትኖራለህ ። ዓመታትና ዘመናትን ሲለወጡ ብቻቸውን አይለወጡም ፣ እኛን ይዘው ይለወጣሉ ። ይፈርዱ የነበሩ ይፈረድባቸዋል ፣ ያዝዙ የነበሩ በሚያዝዙት ይታዘዛሉ ፤ አንተ ግን ወራቶች ሳይጫኑህ ለዘላለም ትኖራለህ ።
ሕልሙ እውን ፣ እውኑም ሕልም ይሆናል ። ሕልሙ እውን ሲሆን ደስታ ፣ እውኑ ሕልም ሲሆንም ድንጋጤ ይሆናል ። አንተ ግን በጸናው ዙፋንህ ትኖራለህ ። ደርሰን ስንመለስ ብዙ ነገር ተለዋውጦ ፣ ቦታውን ስቷል ። አንተ ግን በማይፈርስ መቅደስ ለዘላለም ትኖራህ ። የጸናኸው ካላጸናኸን ፣ ያለኸው ካላኖርኸን ፣ የምትኖረው ተስፋ ካልሰጠኸን እንደ እኛ የሚበላሽ ፍጥረት የለም ። ከሌሎች ፍጡራን ይልቅ እኛ ያለ አንተ መኖር አንችልም ። አዎ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ። እኛ የወደድነውን ስንጠላ ፣ የሾምነውን ስንሽር ፣ የካብነውን ስንንድ ፣ ያጎረስነውን ስንነክስ አንተ ግን በጸና ፍቅር ትኖራለህ ። ከእኛ ጋር ሁነህ የወደድነውን መውደድ የጠላነውን መጥላት አይሆንልህም ፤ የራስህ ሚዛን ያለህ አምላክ ነህ ። እኛ ከሞት ተርፈንም ለሥጋ እንኖራለን ፣በሚታሰር ምላስም ሰውን እንጎዳለን ። አንተ ግን በጸና እውነት ትኖራለህ ።
ጊዜ የጠቆረውን ሲያቀላ ፣ የቀላውን ያጠቁራል ፤ የወፈረው ሲከሳ የከሳውም ይወፍራል ፤ የሰጠው ሲቀበል ፣ የሚቀበለውም ይሰጣል ። አንተ ግን ያው አንተ ነህና በዘላለም ቸርነት ትኖራለህ ። ደክሞህ እርዳታ ፣ አጥተህ ስጦታ አትሻም ። እንደ ጠባይህ ሀብትህም ፍጹም ነው ። በማይጎድለው በረከትህ ባርከን ። ሰው ሲሰጥ ካለው ላይ አጉድሎ ነው ። ያንተ ሀብት ግን ፍጹም ነውና ጉድለት የለበትም ። ተርፎ ከሚጣለው ዕድሜ አትንሣን ። በማይለወጠው ማንነትህ የሚለዋወጠውን የዓለም ሁኔታ ድል ንሣልን ። አንተ የምትከብርበት ዘመን ጨምርልን ። አልፋ ዖሜጋ በተባለው ስምህ አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ