የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንዲት መለኮታዊ ግብር

“ክርስቶስንም ከሙታን ሲያስነሣው ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም ደግሞ ከሚጠራው ስም ሁሉ በላይ በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው በክርስቶስ ባደረገው ሥራ የብርታቱ ጉልበት ይታያል ፤ ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛለት ከሁሉ በላይም ራስ እንዲሆን ለቤተ ክርስቲያን ሰጠው ። እርስዋም አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት ።” ኤፌ. 1 ፡ 20-23 ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሞትም ፈቃዱ ፣ ለመነሣትም ሥልጣኑ የራሱ መሆኑን ተናግሯል ። ዮሐ. 2፡19 ፤ 10፡18 ። ሐዋርያውም ክርስቶስን ከሞት ያሥነሣው መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ይናገራል ። ሮሜ . 1፡4 ። በዚህ ክፍል ላይ ደግሞ አብ እንዳሥነሣው ተጽፎአል ። ኤፌ. 1፡20 ። ይህ ድንቅ የሆነ ገለጻ ነው ። መሞት የወልድ በለበሰው ሥጋ የተለየ ግብሩ ነው ። ይህን ግብር አብና መንፈስ ቅዱስ አይጋሩትም ። ወልድም ሥጋ ባይለብስ ሞት አይነገርለትም ። መነሣትም የወልድ በለበሰው ሥጋ ፣ በቀመሰው ሞት የራሱ የተለየ ግብር ነው ። ማሥነሣት ግን የሥላሴ አንዲት መለኮታዊ ግብር ነው ። ይህም በትምህርተ ሥላሴ አፍአዊ ግብር ተብሎ ይጠራል ። ሥላሴ በውሳጣዊ ግብር ሦስት ናቸው ። አብ ወላዲና አሥራጺ ፣ ወልድ ተወላዲ ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ የሚሰኙበት የግብር ሦስትነት ይህ ነው ። መፍጠር ፣ ማዳን ፣ ማሥነሣት ግን ሦስቱም አካላት በአንዲት መለኮት የሚፈጽሙት ነውና አፍአዊ ግብር አንድ ነው ። ስለዚህ ማሥነሣት አንዲት የመለኮታዊ ግብር ነውና አብም ፣ ወልድም ፣ መንፈስ ቅዱስ አሥነሡ ተብሎ ሊነገር ይችላል ። መነገሩም ድንቅ የሆነው የሥላሴን አንድነት ያሳየናል ።

ሊቃናት ወይም አለቆች ፣ ሥልጣናት ፣ ኃይላት ፣ አጋእዝት/ጌትነት የሚባሉት የመላእክት ነገዶች ናቸው ። ሊቃናት የሚባሉት ሰላታኤል የተባለ መልአክ አለቃቸው የሆነ ፣ ሥልጣናት የሚባሉት አለቃቸው ሱርያል የሆነ ፣ አጋእዝት የሚባሉት ቀድሞ ሳጥናኤል አለቃቸው የሆነ አሁን በቅዱስ ሚካኤል የሚመሩ ፣ ኃይላት አለቃቸው ቅዱስ ሚካኤል የሆነ ፣ ስመ ነገድ ነው ። ሊቃናት በአንደኛው ሰማይ ይኖራሉ ፣ ሥልጣናት በሁለተኛው ሰማይ ይኖራሉ ፣ ኃይላትና አጋእዝት በሦስተኛው ሰማይ ይኖራሉ ። ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ከመላእክት አገር በላይ በመንበረ መንግሥት ዐርጓል ። በክብርም በስፍራም ላቅ ባለ ቦታ ተቀምጧል ። በመለኮትነቱ ይህ ድንቅ አይደለም ። ቀድሞም ያልተሰጠው ያልተቀበለው የባሕርይ ገንዘቡ ነው ። ከመቃብር በታች ተፈርዶበት የነበረው የእኛ ሥጋ ከመላእክትና ከሥልጣናት በላይ መቀመጡ ይደንቃል ። መነሣት ፣ በላይ መቀመጥ ሥጋ ለለበሰ ቃል የሚነገር ነው ። ሥጋ ባይለብስ ኑሮ መለኮት ተነሣ ፣ ከፍ አለ አይባልም ። ሞት የማይስማማው ፣ ወጣ ወረደ ለመባልም የማይቻል ምሉዕ በኵለሄ ነውና ።

በዚህ ዓለም ላይ የተለያዩ የሥልጣን ደረጃዎች አሉ ። አንዱ አገርም ካንዱ አገር በሀብትና በሥርዓት ይበልጣል ። ክርስቶስ ከፍ ያለው ከዚህ ምድራዊ ክብር በላይ ነው ። የእርሱ ከፍታም የአማኞች ከፍታ ነው ። ራሱ ባለበት አካሉ ይኖራልና ። እርሱ ከፍ ያለውም በሰማይ ካለው ከመላእክት አገርና ክብር በላይ ነው ። መላእክት የሚሰግዱት አምላክ ለሆነው ትስብእትም ነው ። ለመለኮት እሰግዳለሁ ፣ ለሥጋ አልሰግድም አይባልም ። መለኮትና ሰውነት በተዋሕዶ አንዱ የአንዱን ገንዘብ አድርጓልና ። እኛም ግን ከመላእክት ጋር ለአንዱ ጌታ እንሰግዳለን ። በምድር እንዳለው ስምና ክብር በሰማይም እንዲሁ አለ ። በምድር የምናየው አብዛኛው መልካም ነገር የሰማይ ጥላ ነው ። በሰማይም በስም ከፍ ያሉ ፣ በክብርም የላቁ የመላእክት አለቆች አሉ ። ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሱባዔ ቢገባ መልኩ እንደ ፀሐይ አበራ ። ስምንት ሺህ ዓመታት ከእግዚአብሔር ፊት ያልተለዩ ቅዱሳን መላእክት ክብራቸውና ብርሃናቸው ከፍ ያለ ነው ። በየማነ አብ መቀመጥ ለወልድ ቀዳማዊ ክብሩ ነው ። ለለበሰው ሥጋ ግን በአብ ቀኝ ከተዋሕዶ በፊት ርስት አልነበረውም ። ታላላቅ መላእክት እንኳ በየማነ አብ መቀመጥ አልተሰጣቸውም ። በደረጃ ዕድገት ፣ በክብር የሚገኝ ስፍራ አይደለምና ። በአብ ቀኝ ለመቀመጥ አብን መምሰል ያስፈልጋል ። ጌታችን ተዋሕዶው ፍጹም ነውና በለበሰው ሥጋ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ። ሥጋ ይዞ አልወረደም ፣ ሲወጣ ግን የሰውን ሥጋ ይዞ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ። አንድ ክርስቶስ እንጂ ከተዋሕዶ በኋላ ሁለትነት የለውም ። ሁለትነት ካለው ሥላሴን አራተኛ አካል የሚጨምርበት ነው ። በቤተ ልሔም ሲወለድ ከሥላሴ መንበሩ ያልጎደለው ወልድ ፣ ወደ ሰማይ ዐረገ ሲባልም ከምድር አልተለየም ።

የብርታቱ ጉልበት ምንድነው ካልን ሞትን ማሸነፉ ፣ አጋንንትን መቀጥቀጡ አይደለም ። የብርታቱ ጉልበት አምላክነትን በቅጠል ለፈለገው ሰው አምላክነትን የሰጠበት ቸርነቱ ነው ። አዳም የምድር ገዥ ተብሎ በቀዳማዊ ልደት የከበረው አሁን በተዋሕዶው የሰማይም ገዥ ሆነ ። በአራዊት ላይ ሥልጣን የነበረው በአጋንንትም ላይ ሥልጣን ተቀብሎ መንፈሳዊውን ዓለም መግዛት ቻለ ።

ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት ሲል ክፉን ብቻ ሳይሆን መላእክት ሁሉ እንዲገዙለት ሆነ ። አስገዛለት ሲባል ዐምፀውበት ነበረ አያሰኝም ። ለለበሰው ሥጋ መላእክትም ተአዛዚ ሆኑ ማለት ነው ። ከሁሉ በላይ የቤተ ክርስቲያን ወይም የምእመናን ራስ ሆነ ። ራስ ተቆጣጠሪ ፣ የበላይ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያንም መሪ ክርስቶስ ነው ። እርሱ ሳያፍርብን ወንድሞቼ ብሎናልና ጌታ አብ ልጆቼ ይለናል ። ቤተ ክርስቲያንም አካሉ ናት ። አካሉን ይዞ ራስ ይከብራል ። በቤተ ክርስቲያንም መለኮታዊ ሥልጣን ይኖራል ። በቤተ ክርስቲያንም ሁሉን ይሞላል ። ማለትም ከነገድ ፣ ከቋንቋ ዋጅቶ ሁሉን ገንዘቡ ያደርጋል ። ቤተ ክርስቲያን ድንበር የለሽ ናትና ።

የኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ አንድን ፈጸምን ። ክብር ምስጋና ዕድሜ ሰጥቶ ላስፈጸመን አምላክ ይሁን ።

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ