የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ እግዚአብሔር አለ

“አንድ እግዚአብሔር አለና ፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” 1ጢሞ. 2፡5
ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ላለው ጳጳስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ ይህን አንደኛ ጢሞቴዎስን የጻፈለት በአገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን ፣ የልብ ስብራት ደርሶበትም ከመንገድ እንዳይቀር ለማበረታታት ነው ። አንደኛ ጢሞቴዎስ ስድስት ምዕራፎች ያሉት ሲሆን፡-
·        ምዕራፍ አንድ ሃይማኖትን ስለ መጠበቅ ፣
·        ምዕራፍ ሁለት አምልኮተ እግዚአብሔርን በትጋት ስለ መፈጸም ፣
·        ምዕራፍ ሦስት እውነተኛ አገልጋዮችን ስለ መሾም ፣
·        ምዕራፍ አራት ስለ አገልጋይ መንፈሳዊ ቁመና ፣
·        ምዕራፍ አምስት ቤተሰብን ስለምትመስል ቤተ ክርስቲያን ፣
·        ምዕራፍ ስድስት የስብከት ዋነኛ አርእስትን ይናገራል ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ የእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ መሆኑን ተናግሯል ። ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት ምሥጢርና የሚያውቁት እውነት ምንድነው ? ብሎ የሚጠይቅ ጠያቂ ካለ ሐዋርያው፡- “አንድ እግዚአብሔር አለና ፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው” ይላል 1ጢሞ. 2፡5 ። ሐዋርያው አንድ እግዚአብሔር አለና ሲል ምሥጢረ ሥላሴን ፣ አንድ መካከለኛ አለ ሲል ደግሞ ምሥጢረ ሥጋዌን እየገለጠ ነው ። በምሥጢረ ሥጋዌ ሥርም ምሥጢረ ጥምቀት ፣ ምሥጢረ ቊርባንና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን አሉ ። ስለዚህ የጥምቀትና የቊርባን መሠረት ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ። በጥምቀትም በቊርባንም በዋናነት የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ እንመሰክራለንና ። የምሥጢረ ሥጋዌ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። ሥጋዌን ልዩ ያደረገው አምላክ ሰው መሆኑ ፣ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ፣ በተለየ አካሉ ሥጋ መልበሱ ነው ።
ሐዋርያው በአጭሩ ለመዳንና እውነቱን ለማወቅ ምሥጢረ ሥላሴንና ምሥጢረ ሥጋዌን እየተናገረ ነው ። ቤተ ክርስቲያን አምስቱ የሃይማኖት ምሰሶዎች /አምስቱ አእማደ ምሥጢር/ የምትላቸው ከመጽሐፍ የተገኙ ናቸው ።
አንድ እግዚአብሔር አለና ። የብሉይ ኪዳን ትልቁ የእምነት መግለጫ “እግዚአብሔር አንድ ነው” የሚለው ነው ። እስራኤላውያን በብዙ አማልክት በሚያመልኩ መካከል አንዱን አምላክ ማምለካቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ። የብዙ አማልክት ተከታዮች እምነትና ድፍረት የላቸውም ። አንዱ አምላክ የሚቤዥ አምላክ መሆኑን እስራኤላውያን ከግብጽ የባርነት ቤት ሲወጡ ተረድተዋል ። አንዱ አምላክ የሠራነው ሳይሆን የሠራን ፣ የምንሸከመው ሳይሆን የሚሸከመን ነው ። ለፍጥረት መገኘትን ፣ ሥርዓትንና ነዋሪነትን፣ ደግሞም ፍጻሜ የሚሰጥ ነው ። ሰማይና ምድርን የፈጠረው አንዱ አምላክ መሆኑ በፍጥረት ስምምነት ይታወቃል ። ሌሊትና ቀኑ ፣ ሰማይና ምድሩ ያለ ግጭትና ያለ ሁከት የሚኖሩት አንዱ አምላክ ስለ ሠራቸው ነው ። ሰዎች ደግሞ በሁከት የሚኖሩት ብዙ አማልክትን ስለሚከተሉ ነው ። አንዱ አምላክ በሦስት ገጻት የሚኖር ፣ በሦስት አስማትና በሦስት አካላት የተገለጠ ነው ። አንድ አካል አንድ ቢባል የሚደንቅ አይደለም ። ሦስቱ አካላት አንድ መሆናቸው ግን ይደንቃል ። በዓለም ላይ ብዙ ሦስትነቶች ቢኖሩም የሥላሴ ሦስትነት ግን የተለየ ነውና ቅድስት ሥላሴ ወይም የተለየች ሦስትነት ብለን እንጠራዋለን ።
የእግዚአብሔር አንድነት የምንለው እግዚአብሔር በፈቃድ ፣ በተግባር ፣ ሕይወትን በመስጠት ፣ በመፍረድ ፣ በማፍቀር ፣ በመስጠት ፣ በመንሣት ፣ በመግደል ፣ በማዳን ፣ ዓለማትን በማምጣት ፣ በማሳለፍ ፣ በባሕርይ ፣ በህልውና ፣ በመለኮት ፣ በአገዛዝ ፣ በረድኤት ፣ በተአምራት አንድ ነው ።
እግዚአብሔር በፈቃድ አንድ ነው ። እያንዳንዳቸው የሥላሴ አካላት የራሳቸው ልብ ፣ ቃል ፣ እስትንፋስ አላቸው ብለው የሚያስተምሩ የዘጠኝ መለኮት ትምህርት አራማጅ ናቸው ። እግዚአብሔር አንድ ልብ መሆኑ እግዚአብሔር በፈቃድ ፣ በመወሰን ፣ በምክር አንድ ነው ማለት ነው ። ፈቃዱ ከዘላለማዊነቱና ከቅዱስነቱ ይመነጫል ። ፈቃዱንም በመገለጥ ወይም በአስተርእዮ ለሰዎች ያሳውቃል ። አስተርእዮ ያስፈለገው እግዚአብሔር ራሱን ካልገለጠ ልናውቀው ስለማንችል ነው ። የአስተርእዮው መንገድ ነቢያት ፣ መጻሕፍት ፣ ተአምራት ፣ ቤዛነት ሊሆኑ ይችላሉ ። እግዚአብሔርም በራሱ ይታወቃል ፣ በአቅማችን ልክ ግን ለእኛ ተገልጧል ። እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ልወቀው ማለትና ጨርሶ ማወቅ አልፈልግም ማለት ሁለቱም ስህተት ናቸው ። እግዚአብሔር ታላላቅ ውሳኔዎችንም ወስኗል ። እነዚህም ሰውን መፍጠር ፣ ማዳንና ዳግመኛ መምጣቱ ናቸው ። ምክሩም የጸና ነው ። ከሕዝቦች ምክር ይልቅ የአንዱ እግዚአብሔር ምክር ይበረታል ። በምክራችን ላይ እርሱ ካልመከረበት ምክራችን ከንቱ ነው ። በምክሩ ግሩም የተባለም እርሱ ብቻ ነው ።
እግዚአብሔር የግብር አንድነት አለው ። በሥላሴ መንግሥት ግብር ሁለት ዓይነት ነው ። ውሳጣዊና አፍአዊ ይባላሉ ። ውሳጣዊ ግብር ሦስት ነው ። ይህም አብ ወላዲ ፣ ወልድ ተወላዲ ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ የሚባልበት ነው። ይህ ውሳጣዊ ግብር ሦስት ነው ። አፍአዊ ግብር የሚባለው ግን ለፍጥረት የሚሰጠው ቸርነትና ማዳን ነው ። በዚህ ግብር እግዚአብሔር አንድ ነው ። በወልድ ቃልነት ዓለም ቢፈጠር ቃልነቱ ለአብም ለመንፈስ ቅዱስም ነውና ሥላሴን ፈጣሪ ያሰኛቸዋል ። በወልድ ቤዛነት ዓለም ቢድንም ሥጋ መልበስ የወልድ የተለየ ግብሩ ሲሆን ማዳን ግን የመለኮት አንድ ግብር ነውና ሥላሴ አዳኝ ይባላሉ ።
ብዙ ወጣቶች ኢየሱስ ብቻ የሚል ትምህርት ሲያስተምሩ ይታያሉ ። ሰባልዮስና የዘመናችን ኢንሊ ጂሰሶች ኢየሱስ ብቻ ይላሉ ። ይህ ስህተት ነው ። ስለ አንድ መካከለኛ ወይም አዳኝ ስንናገር ስለ አንድ አምላክ መርሳት የለብንም ። መዳናችን ሥላሴያዊ ነው ። በአብ ፍቅር ፣ በወልድ ቤዛነት ፣ በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ድነናል ። ለዚህ ነው ታላቁ ባስልዮስ መዳን ሥላሴያዊ ነውና፡- “በአንድ ልጅህ በርሱ ያለ ክብርና ጽንዕ ላንተ ይገባሃል ፣ ከመንፈስ ቅዱስም ጋር ለዘላለሙ አሜን” የሚለውን ጸሎት የቀመረው ።
ሕይወት አንዲት ናት ። ሕይወትም የእግዚአብሔር ገንዘብ ናት ። ከሕያው ባሕርዩ የተነሣ ሕያዋንን ፈጥሯል ። ሥላሴ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወትነት ይኖራሉ ። ይህ ሕይወትም ለሰውና ለመላእክት ተሰጥቷል ። ሕይወት ለእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ስትሆን ለሰው ግን ስጦታ ናት ። ሕይወትም በወርቅ እንዳትገዛ ከዋጋ በላይ ናት ። ከፍጡር እንዳንከጅላት ትርፍ ሕይወት ያለው ማንም የለም ። የሕይወት ምንጭ ግን እግዚአብሔር ነው ። ጣዖታት ግዑዛን ናቸው ። ሕያዋን ሰዎች ግዑዛንን ፈጠራችሁን ብለው ከሚያመልኩ ጣዖታት ሰውን ቢያመልኩ ይሻል ነበር ። እኛ ሕያዋን ነንና ሕያው አምላክ እንደፈጠረን ህልውናችን ምስክር ነው ። እግዚአብሔር በሕይወት አንድ ነው ። አንድ እግዚአብሔር አለ ። ብዙ እግዚአብሔር ቢኖር ኖሮ ዓለም ትታወክ ነበር ። ብርሃንና ኃይል በሚያመነጩ ተቋማት አካባቢ መኖር ይረብሻል ። ትልቋ ፕላኔትና ኃይል ሰጪ ፀሐይ ግን ድምፅዋ አይሰማም ። አንድ እግዚአብሔር ስላለ ፍጥረት በጸጥታ እየተጓዘ ነው ።
1ጢሞቴዎስ /25/
ታኅሣሥ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ