የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አንድ ጊዜ አስበኝ

ጸሎተ ሶምሶን

ለቤተሰቤ ብርቅ ነበርሁ ፣ የኋላ ወርቅ ተብዬ የተጠራሁ ፣ “ሰማኸኝ ጌታዬ” ተብዬ ስእለት የተከፈለብኝ ፣ ሳልፀነስ የተናፈቅሁ ነኝ ፤ የመኳንንት ዘር አይደለሁም ፣ የፍቅር ጌትነት ባለበት ቤት ፣ በሚጸልይ ቤተሰብ ውስጥ የተወለድሁ ነኝ ። ጌታዬ ሆይ ! በመንፈስ ጀምሬ በሥጋ እንዳልጨርስ እባክህን አንድ ጊዜ አስበኝ ። “ነበርሁ” ብሎ መናገር ለኃጢአት እንጂ ለጽድቅ የሚዘገንን ነው ። ከቤተሰቤ በፊት አንተ አይተኸኛል ። ደም በማኅፀን ሳይረጋ የእኔን ከፍታ አብስረሃል ። የመረጥህልኝ ቤተሰቤን ብቻ ሳይሆን የምኖረውንም የኑሮ ዓይነት ነው ። ዛሬ ግን ካየህልኝ ኑሮ ወጥቻለሁና አንድ ጊዜ አስበኝ ። ያንተ ምርጫ እንደማያጸጽት ተረድቻለሁ ።

ቤተሰቤ ስለ እኔ እንዲጠነቀቅ የናዝራዊነትን ወግ አስተምረሃል ። ከማኅፀን ሳልወጣ ጭቃ ላይ እንዳላርፍ ተጨንቀህልኛል ። በማኅፀን ዓለም ብቸኛ ወዳጅ ሆነኸኛል ፤ ቤተሰቦቼም እንዳዘዝካቸው ስለ እኔ አልተሳሳቱም ። ወላጅ ራሱ ይረክስ ይሆናል ፣ በልጅ ጉዳይ ግን ፍጹም ነው ። ወላጆቼ ለእኔ የሆኑትን እኔ ለእነርሱ መሆን አልቻልኩም ፤ ውኃ ሽቅብ የመፍሰስን ያህል ተስኖኛል ። እኔ ለእኔ ደግ ከሆንሁት ቤተሰቤ ያሳየኝ ቸርነት ይበልጣል ። እኔ ፣ ለእኔ ክፉ ባልንጀራው ፣ ጨካኝ ባላንጣው ነኝ ። የሄድኩበት መንገድ ቢርቅም አንድ ጊዜ አስበኝ ። የእኔንም የአገሬንም ትንሣኤ አሳየኝ ።

በናዝራዊነት ጀምሬ በዘማዊነት ስጨርስ ፣ መጠጥን እንዳልተጸየፍሁ ዛሬ ግን ሳጣጥም ፣ ከርኵስ ነገር ስርቅ ኖሬ ዛሬ ግን ስረክስ ፣ ፍጻሜዬ አላማረምና የፍጻሜ አምላክ ፍጻሜዬን አሳምርልኝ።
በኑሮዬ ላከብርህ ጊዜ ቢያልቅ ፣ በሞቴ እንዳከብርህ አንድ ጊዜ አስበኝ ። ለንስሐ ሞት አብቃኝ እያልሁ ፣ የመዳን ቀን ዛሬ መሆኑን ዘንግቻለሁና አቤቱ አንቃኝ ።

ዓለም ደልላ ሸጠችኝ ፣ ዓለም አስብታ አረደችኝ ፣ ዓለም ስማ ነከሰችኝ ፣ ዓለም ዳብሳ ቀለደችብኝ ፣ ዓለም በጓዳ አባብላ በአደባባይ አዋረደችኝ ። የመውደቅ ዘመን በትንሣኤ እንዲለወጥ አንድ ጊዜ አስበኝ ። ሕፃን ልጅ ሲቆሽሽም የሚሮጠው ወደ አባቱ ነውና ተቀበለኝ ። አገሬን ብዬ ወጥቼ አንድ ራሴን ማዳን አቃተኝ ። በተአምራትህ ድልን እንዳላየሁ አሁን ግን በደረቅ ጣቢያ ተቀመጥሁ ። የደስታዬን ምሥጢር አንተን አሳልፌ ሰጠሁህ ። ለመኖር አቅም አጥቻለሁና ፣ ላልኖርኩለት እውነት በግርግር ለመሞት “ምነው በተደባለቀ” እላለሁና አንድ ጊዜ አስበኝ ። ጠላት ጠላትነቱን ላይረሳ ፣ ሰይፉን ወደ ኋላ ፣ ቆንጆን ወደ ፊት አድርጎ ማረከኝ ። ያ ሁሉ ዘፈን በመታወር ፣ ያ ሁሉ መፈራት በመሳለቂያነት አበቃ ። ገዳይ ደብቃ ከምታጎርስ ከዚህች ደላላ ዓለም አድነኝ ።

ዓለም ልብዋን አስቀምጣ በአፍዋ አጫወተችኝ ፣ ሃይማኖት ሃይማኖት ስል ዘመኔን እንዳባከንሁ ነገረችኝ ፣ በቤተ እግዚአብሔር ያለው ጦርነት ነው ፣ እዚህ ግን መዝናናት ነው አለችኝ ። ታስሮ እንደ ተፈታ ጥጃ ስዘልል ተሰበርኩኝ ። በስብራቴ ውስጥ ነኝና አንድ ጊዜ አስበኝ ። የምናገረው የሚያስቃት ፣ የምትናገረው የማያስቀኝ የዓለም እጮኛ ነኝና መሳቂያ የሆንሁትን ልጅህን አንድ ጊዜ አስበኝ ። ይህን የምልህ ከቤተ ክርስቲያን ቆሜ ፣ ከምእመናን መካከል ተገኝቼ አይደለም ። ፊት ለፊቴ ሰርቀው የደለቡ ባለጠጎች እየጠጡ ይታዩኛል ፣ የሴረኞች ሸንጎ በዙሪያዬ ይሰማኛል ። ከመቃብር ስፍራ እጠራሃለሁ ። እንደ አንበሳ ኖሬ እንደ ውሻ ተዋርጄአለሁ ። ያንን የልጅነት ፍቅሬን ፣ በእኔ ላይ የደከምከውን አስብና አንድ ጊዜ ድል ስጠኝ ።

የተንሸራተትኩበትም የወደቅሁበትም ቦታ ጠፍቶኛል ። እንደ ሞኝ የወንዙን ጥልቀት በሁለት እግሬ ለክቼ ሰጥሜአለሁ ። ራሴንም ቃል ኪዳኔንም አዋርጄአለሁ ። ያላንተ ከመኖር ባንተ መሞት ብፅዕና ነው ። እንደ ፈላስፋ ፣ እንደ ጀብደኛ ኖሬአለሁ ፤ እንደ አማኝ መሞትን እሻለሁ ። በእኔ ማፈርህ ይብቃና ዛሬ በእኔ ታፈር ። ድል ስጦታህ ስለሆነ አመሰግንሃለሁ ። እኔም ቀን ስለወጣልኝ አደንቅሃለሁ ። ለፍላጎቴ ሞቼ ላንተ እነሣለሁ ። አሜን ። “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ እባክህ፥ አስበኝ አምላክ ሆይ፥ ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፥ እባክህ፥ አበርታኝ ።” አሜን!!!

መነሻ መጽሐፈ መሳፍ. ምዕ. 16

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ነሐሴ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።