የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አካባቢውን መምሰል

“ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል ።” 1ጢሞ. 1፡6-7
የኤፌሶን ሰዎች የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ የወደዱት በምን ምክንያት ነው ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። አይሁዳውያን የሆኑት የሕግ አስተማሪዎች ክርስቶስ ያለ ሙሴ ፣ ወንጌል ያለ ኦሪት ፣ ጥምቀት ያለ ግዝረት ብቻውን አያድንም እያሉ ያስተምሩ ነበር ። የትምህርታቸው ፍጻሜ ምንድነው ? ስንል ሙሴ ያልመራቸው ፣ ኦሪት ያልደረሳቸው ፣ ግዝረት ያላነጻቸው ሰዎች ክርስቲያን መሆን አይችሉም የሚል ነው ። ስለዚህ አሕዛብ ሙሴ ሊመራቸው ጊዜው አልፏል ፣ ግዝረትን ለመቀበል የአብርሃም የሥጋ ልጆች አይደሉም ።ኦሪትም የተሰጠው ለአይሁድ ነው ። የሕግ አስተማሪዎች እግዚአብሔር ላጸደቃቸው አሕዛብ ብስጩ የሆኑ ምስኪኖች ናቸው ። እግዚአብሔር ሲወድና ሲያድን የድጋፍ ፊርማ አያሰባስብም ። የሕግ አስተማሪ የሆኑት አይሁድ ሦስት ዓይነት ክፍል ሊኖራቸው ይችላል፡-
1-  ሙሴ የመጨረሻው መሪዬ ፣ ኦሪት የፍጻሜ ሕጌ ፣ ግዝረት የመጨረሻ የቃል ኪዳን ማኅተሜ ብለው ክርስቶስን ፍጹም የማያምኑ ፣ ወንጌልን የሚገፉ አሉ ።
2-  ወንጌሉን ከኦሪት ጋር ተቀብለው አሕዛብ እንደ እኛ ከተገረዙ መዳናቸው ሙሉ ይሆናል ብለው አሕዛብን የሚያደናግሩ አሉ ።
3-  እንደ ኦሪቱ ወንጌሉም የተሰጠው ለእኛ ብቻ ነው ብለው የአሕዛብን በወንጌል ማመን ፍጹም የማይቀበሉ አሉ ።
እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት ፍርጥም ብለው በቊጣ ስለሆነ ስሜታውያንን የማነቃቃትና ለግድያ የማሰለፍ አቅም ነበራቸው ። እንደ እነርሱ ስለማያስበው ሰው ልዩነቱን አክብረው የሚቀመጡ ሳይሆን መሞት አለበት ብለው የሚፈርዱ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች የሃይማኖት ሰዎች እንዳንላቸው ወንድሜ ይሙት እንጂ ይዳን አይሉም ። ፖለቲከኛ እንዳንላቸው በአሳብ ልዩነት አያምኑም ። ጀግና እንዳንላቸው በሃይማኖት አጥር ውስጥ ተደብቀዋል ። በዚህ ምክንያት ከአረማዊነት ወደ ክርስትና የመጡት የአሕዛብ ክርስቲያኖች ግራ ተጋብተው ነበር ። እንደ እነ ጳውሎስ ያሉትን ሐዋርያት ሲያስቡ ደስታ ይሰማቸዋል ። የሕግ አስተማሪዎችን ሲያስቡ ደግሞ ማመንታት ውስጥ ገብተው ነበር ። ማመንታት ውስጥ የገቡት እነ ጳውሎስም ሆኑ የሕግ አስተማሪዎች ሁለቱም አይሁዳውያንና ብሉይ ኪዳንን የሚቀበሉ በመሆናቸው ነው ። የመጀመሪያው የሐዋርያት ጉባዔ በ50 ዓ.ም. የተካሄደበት ምክንያት እነዚህ የአሕዛብ ክርስቲያኖችን ለማጽናትና የተቀላቀለ ወንጌል ይሰብኩ የነበሩትን ቢጽ ሐሳውያን ለመገሠጽ ነው ። /የሐዋ. 15./
አንዳንድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች በሕግ አስተማሪዎች ተስበው ነበር ። እነዚህ የሕግ አስተማሪዎች ለውስጣዊ ቅንነት ሳይሆን ለውጫዊ ሥርዓት የሚጠነቀቁ ፣ ከፍቅር ለውበት የሚያደሉ ፣ ከእግዚአብሔር ክብር ለሰው ሙገሳ ቅድሚያ የሚሰጡ ፣ ያመኑበትን ነገር በመሞት ሳይሆን በመግደል የሚያስከብሩ ስለሆኑ፣ ስለሚናገሩት አመክንዮ ስለሌላቸው ማሳመኛቸው ቊጣ የሞላበት ንግግር መሆኑ ፣ ጠባቸው ልክ የለውምና እስከ ትዳርና ሰፈር ወርደው የሚያምሱ በመሆናቸው አንዳንድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ወደ እነርሱ ተስበው ነበር ። ወደ እነርሱ በመሳባቸው ነቀፋ የሚቀርላቸው ፣ ጠላት የሚቀንሱ ፣ ሕዝብ የሚያተርፉ መስሎአቸው ነበር ። እነዚህ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ወዲህ ጣዖታውያን በሆኑት ዘመዶቻቸው ፣ ወዲህ በአይሁዳውያን በመነቀፋቸው ሌጣነት ተስምቷቸው ነበር ። ዘመዶቻቸው እንዴት ከአይሁድ የመጣ እምነትን ትቀበላላችሁ ? ይሏቸዋል ፤ አይሁዳውያኑ ደግሞ እንዴት እኛ በሰቀልነው ክርስቶስ ታምናላችሁ ? ይሏቸዋል ። በዚህ ምክንያት አንድ እጃቸውን ለዘመዶቻቸው ፣ አንድ እጃቸውን ለአይሁዳውያን ሰጥተው ሲጓተቱአቸው ደክመው ነበር ። ለአሕዛብ ክርስቲያኖች ጣዖታውያንና ወግ አጥባቂዎች ፤ ሥርዓት አልበኞችና ሁሉን አጥርተው የሚያዩ ፈተናዎቻቸው ነበሩ ። የንጉሡ መንገድ ግን ከመካከል ነው ።
ክርስትና በሁለት ጦር ግራና ቀኝ የተወጠረ ፣ ወደ አንዱም ምቾት የሌለው ሆኖባቸው ነበር ። በዚህም ምክንያት አንደኛ በአይሁዳውያን ወገኝነት በመሳብ ፣ ሁለተኛ የአይሁዳውያንን ትችትና ማሳደድ በመሰልቸት ወደ እነርሱ እየተሳቡ መጥተው ነበር ። ሐዋርያው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ይህን ጉዳይ ነው ።
“ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል ።”
ሐዋርያው እነዚህ መስሎ አዳሪ ለመሆን የፈለጉትን ሰዎች የሚገልጥበት ቋንቋ የሚደንቅ ነው ።
“አንዳንዶች ስተው” በደምሳሳው አልተናገረም ። አንዳንዶች ስተው በማለት ተናገረ ። ሁሉ ክፉ አይሆንም ፤ ሁሉም በስህተት መንገድ አይነጉድም ። አንዳንዶች ይስታሉ ። ሁሉን ደግ ፣ ሁሉንም ክፉ ማለት እውነተኛ መለኪያ አይደለም ። ስለዚህ ሐዋርያው አንዳንዶች አለ ። ደምሳሽ የሆነው ዘመናችን አንዳንዶች ከሚለው የሐዋርያው ቃል ቢማር መልካም ነው ። በአንድ አማኒ መላውን ሃይማኖት መፈረጅ ፣ በአንድ ሰው መላውን ጎሣና ነገድ ዋጋ የለሽ ማድረግ ልንላቀቀው የሚገባን ዘመናዊው ፈተና ነው ።
ሐዋርያው ስለ አንዳንዶችም የተናገረው በመራራት ነው ። ስተው ይላል ። መሳት መንገድ የጠፋበት ሾፌር ወይም መንገደኛ ማለት ነው ። መንገድ የጠፋበት ሾፌርን የሚሰድበው ወይም የሚወግረው ማነው ? መንገድ ለጠፋው ያዝኑለታል ። ጊዜውን ፣ ጉልበቱን ፣ ገንዘቡን ፣ ተስፋውን አባክኗልና ። ሐዋርያው እዘኑላቸው እያለ ነው ። የሳተ ሰው ስለ ማሳሳቱ ብዙ ጊዜ ያሳስበናል ። ከመሳሳቱ በላይ መሳቱ ያሳዝናል ። ካልጠፋ በቀር የሚያጠፋ የለም ።
“የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ” ይላል ።እነዚህ ሰዎች አጉል ጠበቆች ሁነው ነበር ። ስለ ሕግ አስተማሪዎች የሚናገሩት ንግግርና ጥብቅና እውነትነት የሌለው ነው ። የደጋፊዎች ፍቅር የጭፍን ፍቅር ነው ። ደጋፊዎች ያለ ምክንያት ይወዳሉ ፤ ያለ ምክንያት ይጠላሉ ። ለምን ? የማይባሉ የፈቃድ ወረቀት ያላቸው የሚመስሉ ናቸው ። ጥብቅና ስለሚቆሙለት ነገር እንኳ የማያውቁ ሰዎች ሊረቱ ይችላሉ ። ሆ ሲባል ሆ ማለትን ብቻ ገንዘብ ያደረጉ ከሰሙት ውጭ ላለመስማት ጆሮአቸውን የደፈኑ ብዙ ናቸው ።
ስለ ሕግ አስተማሪዎች አስረግጠው የሚናገሩት ባለማስተዋል ነው ። አለማስተዋል ደግሞ አለማጤን ነው ። ከላይ ከላይ መዋኘት እርሱ አለማስተዋል ነው ። ጠልቆ ለመዋኘት ልምድ ፣ ድፍረት ፣ አየር መቆጠብ ያስፈልጋል ። ለጋ አማኞች ፣ ሁሉን ነገር የሚፈሩ ድንብሮች ፣ ለሚናገሩትና ለያዙት ነገር ቁጠባ የሌላቸው ብኩኖች ጠልቆ ማየት አይችሉም ። የሕግ አስተማሪዎቹ የመጨረሻ ግባቸው አሕዛብን ከኦሪትም ከወንጌልም ማፈናቀል ነው ። አንዳንድ የአሕዛብ ክርስቲያኖች ባለማስተዋል የነገ መቀበሪያቸውን ይቆፍራሉ ። በዓላማቸው የማይጸኑ ሁሉን ይከስራሉ ።
ሐዋርያው፡- “ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል” ይላል ። የመሳት ፣ የመመሳሰል ፣ የጥብቅና ፣ ያለ ማስተዋል መንገድ መጨረሻው ከንቱ ንግግር ነው ። እግዚአብሔር ምስክሮችን እንጂ ጠበቆችን አይፈልግም ። ከንቱ ንግግር ስድብ ፣ ፌዝ ፣ ፍሬ የሌለው ገለባ ወሬ ፣ አድማ ፣ ስም ማጥፋት ፣ ሐሜት በውስጡ አለበት ። እግዚአብሔርን ብቻ ቢያዩ ክርስትናውን ይዘልቁት ነበር ። አካባቢውን ሲያዩ ግን ወደዚህ ሁሉ መክሰር ውስጥ ገብተዋል ።
በእግዚአብሔር ፊት እንደምንቀርብ ብናስብ በዙሪያችን ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን አንፈራም ። ከሰዎች ቊጣ በእግዚአብሔር እንድናለን ፣ ከእግዚአብሔር ቊጣ በማን እንድናለን ። የሚያስፈራንን መለየት መታደል ነው ።
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ፣ ያንተ በመሆናችን ብቻ ደስታህ ይብዛልን !
1ጢሞቴዎስ /11/
ኅዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ