የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አዝምቶ መመለስ

“ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣም” ይባላል ። በአገራችን የትልቅ ማኅበራዊ ኑሮ መገለጫ የሆነው ዕድር ነው ። በዕድር ውስጥ ካሉ ነገሮች አንዱ ጡሩንባ ነፊ ነው። ጡሩንባ ነፊው ብዙ ጊዜ ምስኪን ድሃ ነው ። በብዙ ክፍለ አገር እንዳየሁትም መጠጥ የሚያበዛ ነው ። ታዲያ በሰላሙ ቀን በመንደሩ አለፍ ሲል እናቶች ይጠሩትና፡- “ለእኔ ጊዜ በደንብ አድርገህ ጡሩንባውን እንድትነፋ” በማለት ለማያዩት ቀን ቃል ያስገቡታል ። በርግጥም ሰው ዋና ፣ ዋና ቀኑን አያየውም ። ሲወለድ እንዴት እንደነበረ አላየም አላወቀም ። ሲሞትም እንዴት እንደሆነና ማን እንደሚገኝ አያውቅም ። ባለ ማወቅ የተሞላ ሕይወት ውስጥ የሚኖር ነውና ሰው ሁልጊዜ ራሱን ለእግዚአብሔር መስጠት አለበት ። ታዲያ ያ ጡሩንባ ነፊ አንዳንዴ በመንደር ሰዎች ይሰደባል ። ለሞታቸው ቀን እቅድ የሚያወጡ እናቶች ከገጠሙት ደግሞ ጥሩ ምሳ ይበላል ። ጡሩንባ ነፊ የሚፈለግበት ሰዓት ምሽት እቤቱ እንደገባ ሊሆን ይችላል ። አሊያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ሊሆን ይችላል ። በአንዱ ቤት ልቅሶ በአንዱ ቤት እንቅልፍ ነውና ጡሩንባ ነፊው ጣልቃ ይገባና ይዳኛል ። አቶ እገሌ ወይም ወይዘሮ እገሌ አርፈዋልና ቀብር በዚህ ሰዓት ነው ይላል ። አቶ እገሌ መታመማቸውን የሰማ “አረፉ ?” ይላል ። ያልሰማ መኝታው ላይ ከሚጣፍጠው የንጋት እንቅልፍ ላይ ይሰማል ። ለነገሩ ንጋት ላይ ትልልቅ ሰዎች አይተኙም ። ዕድሜ በገፋ ቊጥር እንቅልፍ ይቀንሳልና ለአራትና አምስት ሰዓት ከተኙ በኋላ ይነቃሉ ። ያንን ልቅሶ ሲሰሙ በቀን አራት ጊዜ ይሄዳሉ ። የመጀመሪያው እርማቸውን ለማውጣት ፣ ሁለተኛው ሥራ ለመሥራት ፣ ሦስተኛ ቀብር ለመሄድ ፣ አራተኛ ከቀብር መልስ በረታችሁ ወይ ? ለማለት ይመለሳሉ ።
ታዲያ ጡሩንባ ነፊው ጨለማና ብርሃን ፍልሚያ ሳይገጥሙ በሌሊት ይነሣል። በዚያ ጭር ባለው ሌሊት ፣ ፍጥረት አሸልቦ የጣመ እንቅልፍ በሚልጥበት ፣ ሌባ ለመስረቅ በሚወጣበት ፣ አእዋፋት ለመዘመር በሚዘጋጁበት ሌሊት ከጨለማው ጋር ተመሳስሎ ፣ ከአራዊት ጋር ተጋፍጦ ጡሩንባ ነፊው ያደበላልቀዋል ። ጡሩንባውን መጀመሪያ አራት ጊዜ በአራቱ አቅጣጫ ይልከዋል ። ተልከስካሹ ሁሉ ይገሰጻል ፣ ፀጥታው ጓደኛ ያገኛል ። ብርሃን ለመውጣት ይዳዳል ፣ ወፎች ዝማሬ ያሰማሉ ። በየቤቱ የተኛው የዛሬ ልቅሶ ሰሚ የነገ ሟች ፣ ጆሮውን ይገትራል ። ገና በስመ አብ ሳይል የወዳጁን ወይም የዕድርተኛውን ልቅሶ ይሰማል ። የጠላቱንም ልቅሶ ሲሰማ እንኳን ሞተ አይልም ። “አይ ለማይቀረው ዓለም እንዲያ ስንባላ አረፈው ?” ይላል ። “ሙት አይከሰስ ድንጋይ አይነከስ” “ሙት መውቀስ ድንጋይ መንከስ ነው” ይላሉ ። ሃይማኖት የነበረው የአገራችን ሰው ። ዛሬ ከሞቱ መቶዎች ዓመታት የሆናቸውን እንወቅሳለን ።
ቀልድ ይሁን እውነት ካዛንቺስ ላይ የሚነገር አንድ ነገር አለ ። በደርግ ዘመን የካዛንቺስ ጡሩንባ ነፊ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ ይመጣሉ ተብሎ ሰው ሁሉ ወጥቶ እንዲቀበል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ጡሩንባ ለመንፋት ወጣ ። ፊደል ካስትሮ ለማለት ተቸግሮ ፡- “አቶ ፍየል ታስሮ ወደ አገራችን ስለሚመጡ ሁላችሁም ወጥታችሁ ተቀበሉ ተብሏል ። የቀራችሁ ከሆነ እኔ የለሁትም ቱ ብያለሁ” እያለ ምራቁን ይተፋ ነበር ። ይህን የሰሙ ሽማግሌ ነግረውኛል ።
  
ጡሩንባ ነፊው ለመላው ቀበሌ ፣ ለሺህ ዕድርተኛ ይነፋል ። ታሞ ሳለ ለመጠየቅ ጊዜ ያጣው የቊርጡ ቀን ግን ጊዜ አያጣም ። ዛሬ ከተመቸው ያኔም ይመቸው ነበር ። ታዲያ የዕድሩን ጡሩንባ የሰሙ እናቶችና አባቶች “ለካ ውሻው ሲያላዝን የከረመው ለዚህ ነበር ?” ይላሉ ። ውሻ ሲያላዝን “ሰው ሊሞት ነው” ይባላል ። “እኔ ልሞት ነው” የሚል ግን የለም ። ራሳችንን ከሰው ክልል ውጭ አውጥተን መኖራችን የሚታወቀው የሚሞቱትን እያየን እሞታለሁ ብለን በጎ አለማድረጋችን ነው ። ሰው እሞታለሁ ብሎ ሞቱን አምኖ ዕድር ይገባል ። እሞታለሁ ብሎ ግን ለምን ንስሐ አይገባም ? ብዙዎች “ሞቼ የት እቀበራለሁ ?” የሚለው ያሳስባቸዋል ። “ሞቼ በነፍሴ የት እገባለሁ ?” የሚለው ግን አያሳስባቸውም ። ይህ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ማክበር አይደለምን ?
ጡሩንባ ነፊው እንደ ዘመድ ቀድሞ የሚነገረው ፣ ልቅሶ ካለ ብቻ የሚታወስ ከዚያ ውጭ እንዳለ እንኳ የማይታሰብ በቁሙ የተረሳ ሰው ነው ። ታዲያ ድንኳኑ ሲተካከል ዳር ቁሞ አየት ፣ አየት ያደርጋል ። እርሱ የሌሊት ወዳጅ ነውና ማለዳ የመጡት ላይ በትዝብት ይንጎማለላል ። ሬሳው ከቤት ሊወጣ ሲል አንድ ጊዜ ጡሩንባውን ያጮህና በቀጥታ ወደ መጠጥ ቤት ይሄዳል ። አዳሜ እያለቀሰ ፣ እንባውን እያፈሰሰ ወደ ቀብር ቦታ ሲሄድ እርሱ ደግሞ ጠጁን ፈሰስ ለማድረግ ስያሜ ወደ ተሰጣቸው ጠጅ ቤቶች ወደ “ውሻ ገደል” ፣ “ወደ ጥርሰ በረዶ” ፣ ወደ “ዝጉበት” ይሄዳል ። እነዚህ ሁሉ የጠጅ ቤት ስሞች ናቸው ። ጠጅ ቤት ከስያሜው ጀምሮ አቀማመጡ ስልታዊ ነው ። ዳገት ላይ አይሆንም ፣ ሰክሮ የወጣው ሰው ባናቱ ይተከላል ። ገደል ውስጥ የሆነ እንደሆነ ቧጥጦ ይወጣል ። በጣም ካቃተው ገደሉን ደግፈው የሚያወጡ ነገር ግን ከአንድ ብር እስከ አምስት ብር የሚያስከፍሉ ወጣቶች አሉ ።
ሬሳው ከቤት ከወጣ በኋላ ጥሩንባ ነፊው ሌላ ሟች እስኪመጣ ፍጹም ይረሳል። የሰበሰበው ፣ የሟችን መሞት ለዓለም ያወጀው ፣ ጥንታዊው የሬዲዮ ጣቢያ ፣ ጥንታዊው ፌስቡክ ፣ አካላዊው ወዳጅ ያ ጡሩንባ ነፊ ይረሳል ።
ታዲያ ከቀብር ሲመለሱ እርሱ በቢጫ ሰረገላው ላይ ሁኖ እያየ ይስቃል ። አለቃ ገብረ ሃና ከቤታቸው አጠገብ በጣም ድሃና በቊስል የተወረረ ሰው ነበረ። በድህነቱ ሁሉ ርቆት ይኖራል ። ጠዋት ወጥተው የነበሩት አለቃ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ሰፈሩ በግርግር ደምቋል ። ምንድነው ? ብለው ሲጠይቁ ከቤታቸው አጠገብ የነበረው ድሃ መሞቱን ሰሙ ። እርሳቸው ግን “ተኖረና ተሞተ” አሉ ይባላል ። ጡሩንባ ነፊውም ተርቦ ለሞተው ድሃ ቀብሩ ላይ በሬ ሲጣልለት ብዙ ጊዜ አይቷል ። ያ ችግረኛ ሞተ ተብሎ ሲለቀስም “ተኖረና ተሞተ” ማለቱ አይቀርም ። በጣም የምንንቃቸው ሰዎች በጣም ያውቁናል ። ምክንያቱም በእነርሱ ዘንድ ስለማንጠነቀቅ የእኛ ምሥጢር ያለው እነርሱ ጋ ነው ። መንግሥታት እንኳ ሰላይ የሚቀጥሩት ከእነዚህ ሰዎች ነው ።በአገራችን የቤት ሠራተኞችን ብዙ ለማክበር አልታደልንም ። እነርሱ መከበር ይጨንቃቸዋል ። ታዲያ ሴትዬዋ “ንስሐ አባት ይዘዋል ወይ ?” ቢባሉ “የቤት ሠራተኞቼ እያሉ ንስሐ አባት አያስፈልገኝም” አሉ ይባላል ። ንስሐዬ እነርሱ ጋ አለ ማለታቸው ነው ። ጡሩንባ ነፊውም ይንቁት ይሆናል ፣ እርሱም ይንቃቸዋል ። በጣም የሚያስፈልገንን ሥራ የሚሠሩልን የምንንቃቸው ሰዎች መሆናቸው ይገርማል ። የቤታችንን ቆሻሻ የሚያነሡት ፣ ሬሳችንን የሚሸከሙት ፣ መቃብራችንን የሚቆፍሩት ባናከብራቸውም እንደ እነርሱ የሚረዳን የለም ።
“ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣም” ይባላል ። እርሱ በጠዋቱ ግዴታውን ስለተወጣ ስለመቅበር አይጨነቅም ። ባለመቅበሩም የሚቀየመው የለም ። ከሰው ሁሉ በፊት ሰምቶ ከሰው ሁሉ ኋላ ይቀራል ። ሞቱን አርድቶ እርሱ ግን ማልቀስ ይቸገራል ። ለቀስተኞቹ አልነጋ ብሏቸው ልቅሶአቸውን አፍነው ሳለ እርሱ ለዓለም ያውጃል ። ይህን ሁሉ አድርጎ ግን ቀብር አይወጣም ። ይህ ቃል ትዝ ያለኝ ዛሬ በሌሊት ስልክ አነቃኝና አናገርሁ ። አንድ ወዳጄ ከውጭ አገር መጥቶ ገና ከአውሮፕላን መውረዱ ነው ። “በዚሁ ለሱባዔ ልሄድ ነው ፣ መግባቴን እወቀው ብዬ ነው” አለ ። ከአገር ከወጣ ብዙ ጊዜው ነው ። ቤተሰብ ቤተ ዘመድ ይጠብቀዋል ። ግን ከእግዚአብሔር ጋር ጉዳይ አለኝ ፣ እርሱን ሳልጨርስ ሰው አላገኝም ያለ ይመስላል ። ስለ ጽሞና ፣ በእግዚአብሔር ፊት ስለ መሆን ብዙ ጊዜ አስተምረናል ። ይህም ወጣት የዚህ ትምህርት ተካፋይ ነው ። እርሱ ተግባራዊ ለማድረግ ከሩቅ ሲመጣ እኔ ግን በመኝታዬ ሆኜ ገና ለመጸለይ እንኳ አልተሰናዳሁም ። ራሴን ወቀስኩ ። “ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣም” ብዬ ማንነቴን ዘለፍኩት ።
እኛ ያስተማርናቸውን ስናፈርስ ያለ ይሉኝታ የሚገስጹን እነማን ናቸው ? አባቶች ናቸው ? ወዳጆች ናቸው ? አይደሉም ። ሕጻናት ናቸው ። ሕጻናት እየኖሩት እኛ ግን ማድረግ አቅቶናል ። ምክንያቱም ጡሩንባ ነፊ ቀብር አይወጣማ ! ዛሬ መንፈሳዊ ሳይሆን ዘመናዊ ልጅ ለማሳደግ ነው ጥረታችን ። “ሶሪ” በል እያልን ስለ ይቅርታ እናስተምረዋለን ። እኛ ግን ይቅር አንልም ። ወይም ሶሪ አናውቅም ። ለነገሩ ልጆቹም የአማርኛውን “ይቅርታ” አይሉም ። ትንሽ የእንግሊዝኛው ይቀላቸዋል ። የሰው ተፈጥሮ “ይቅርታ” ለማለት ይቸገራል። በብዙ ነገር ወደ ኋላ ቀርተናልና ለእኛ ለአገልጋዮች ብርታት ይስጠን ።
በመካከለኛው ምሥራቅ እረኛው ከፊት እየሄደ ፣ ድምፁን ሲያሰማ በጎቹ ከኋላው ይከተሉታል ። ከፊት ስለሚሄድ ጠላታቸውን ከሩቅ ያየዋል ። እርሱ ለሞት ደረቱን ሰጥቶ በጎቹን ጋርዶ ይከተላል ። በእስራኤል አገር ይህን እረኝነት አይቻለሁ ። በአገራችን ደግሞ በጎች ከፊት እረኛው ከኋላ ነው ። ስለዚህ ይነዳቸዋል እንጂ አይመራቸውም ። እረኞች ዘመኑንና ትውልዱን መቅደም ካልቻሉ ማዳን አይችሉም ። መቅደም ታዲያ ፌስቡክ መጠቀም እየመሰላቸው ብዙዎች ይታለላሉ ። እርሱ ጥሩ ነው ። መቅደም በመንፈሳዊነት ፣ በእውቀትና የሌሎችን ድካም በርኅራኄ በማየት መሆን ይገባዋል ።
ጌታ ሆይ እባክህን በጠዋት ተነሥተን ፣ ሌሎችን ለልቅሶ ቀስቅሰን እኛ ግን የሳቅ ኮክቴል እንዳያምረን እርዳን ። ጸልዩ እያልን እኛ ግን ፊልም ላይ እንዳንጣድ ፣ መጽውቱ እያልን እኛ ግን ገንዘብ እንዳናሯሩጥ ጌታ ሆይ አንተ የመረጥከው አገልጋይ ዓይነት አድርገህ ሥራን ። አዝምቶ መመለስ ከእኛ ይራቅ ።
ታማኙ እግዚአብሔር ነፍሳችሁን ከመባዘን ይጠብቅ !!
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሰኞ ሚያዝያ 22/2010 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ