ተቃራኒዎች ለዘላለም አይታረቁም ፣ አንተ ግን ማስማማት ይቻልሃል ። እውነትን የሚቃወሙ ሐሰትን ያበዛሉ ፣ አንተ ግን የመረራቸውን እውነት ልታጣፍጥላቸው ይቻልሃል ። በገዛ ነፍሳቸው እልህ የተጋቡትን መመለስ አይቻልም ፣ አንተ ግን የሰይጣንን ሽንገላ ድል ልትነሣላቸው ይቻልሃል ። ነፍሶችን መማረክ በሥጋ አቅም አይቻልም ፣ በፍቅር መሳብ ግን ላንተ ይቻልሃል ። የቤተሰብን መዝረክረክ በቍጣ ማስተካከል አይቻልም ፣ አንተ ግን ሁሉን ወደ ልቡ መመለስ ይቻልሃል። ሳይሠሩ መኖር አይቻልም ፣ አንተ ግን ዕውር አሞራን መቀለብ ይቻልሃል ።
ኃይለኞችን መቅረብ አይቻልም ፣ አንተ ግን ጨካኙን አዛኝ ማድረግ ይቻልሃል ። ባልን ትሑት ማድረግ አይቻልም ፣ አንተ ግን ሕይወትን መለወጥ ይቻልሃል ። ሚስትን ማለዘብ አይቻልም ፣ አንተ ግን በቅድስና መሸለም ይቻልሃል ። የተቆረጠን ቅርንጫፍ መግጠም አይቻልም ፣ አንተ ግን ለሞተው ሕይወት መስጠት ይቻልሃል ። ያስተማሩት ሲወቅስ መስማት አይቻልም ፣ አንተ ግን በግዑዝም በእንስሳም ማስተማር ይቻልሃል ። ከፍ ያሉት ዝቅ ያሉትን ማየት አይችሉም ፣ አንተ ግን ለከፍታው ጉልላት ፣ ለዝቅታው መሠረት መሆን ይቻልሃል ።
መሠረታዊ ፍላጎትን ፣ አብሮ አደግ ችግሮችን ማስወገድ አይቻልም ፣ አንተ ግን የታሰረውን ልትፈታ ይቻልሃል ። የተበተኑትን መሰብሰብ ፣ የፈሰሰውን ውኃ ማፈስ አይቻልም ፣ አንተ ግን ሞትን ወደ ልደት መለወጥ ይቻልሃል ። የረገጡትን መተው ለፈሪዎች አይቻላቸውም ፣ አንተ ግን ቦታ ማለዋወጥ ይቻልሃል ። የወጡ ቃላትን መመለስ አይቻልም ፣ አንተ ግን ከሰው ልብ ቂምን መሻር ይቻልሃል ። የአገር ውስጥ መጻተኛ መሆንን ፣ በወገን መገፋትን መቀበል አይቻልም ፣ አንተ ግን ሌሊቱን ቀን ማድረግ ይቻልሃል ። የሞቱን ደብዳቤ ይዞ የሚሄደውን – ሰው አማኙን ማትረፍ አይቻልም ፣ አንተ ግን ሰይፍን በሽልማት መለወጥ ይቻልሃል ። የተዘጋውን መክፈት አይቻልም ፣ የዳዊት ቁልፍ – የሥልጣን ዘንግ ያለህ አንተ ግን ይቻልሃል ። ባለጠጋን ወደ መንግሥትህ ማስገባት አይቻልም ፣ አንተ ግን ሰው የማይችለውን ትችላለህ ።
በእኔ አይቻልም ፣ ባንተ ግን ይቻላል !
በማልችለው ነገር ላይ ጌታ የሆንከው መድኃኒቴ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ በመቃብሬና በዘላለም ሞቴ ላይ ሥልጣንህን አምናለሁ ። ባንተ ከዳንን ልጆችህም ምስጋና ይገባሃል ። ለዘላለሙ አሜን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተጻፈ ጳጕሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም.