ይቅር በለኝ አዳምጣለሁ ። የሰዎችን ፊት ዓይኔ አትኩሮ ያያል ። ጠንቋይ መዳፍን ሲያነብ ፣ እኔ ፊት እያነበብሁ ራሴን አሰቃያለሁ ። ዛሬ ፊታቸው ጠቆረ ፣ ምን አስበው ነው? እላለሁ ። የምታኖረኝን ትቼ የማያኖሩኝን እፈራለሁ ። መኖሬ በሰው ፍቅር ላይ የተመሠረተ ይመስለኛል ። ዓለሙ ሁሉ ቢያድም አንተ ካልፈቀድህ ማንስ ይነካኛል ? ጌታ ሆይ የሰዎችን የድምፃቸውን መጠን በጆሮዬ እለካለሁ ። ሰላምታቸው ቀዘቀዘ ደግሞ ምን ሊሉኝ ነው ? እላለሁ ። ስሜቴ ከፍና ዝቅ ይላል ። ቋሚ ባልሆኑ ሰዎች ላይ ደስታዬን መሥርቼ ስወጣና ስወርድ እውላለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። አንተ በእውነት ስትወደኝ ምንም አይመስለኝም ፣ ሰዎች በሽንገላ ሲያፈቅሩኝ ልቤ ይዘላል ። ቀድሞም ያልወደዱኝ ሲጠሉኝ ግራ ይገባኛል ። የሰው ፍቅር ከሞት አያድንም ፣ “ወዶኛልና አዳነኝ” የተባለልህን አንተን ፣ የነፍስ አብነቴን ችላ ብያለሁና ይቅር በለኝ ። የእግር ኮቴዎች ምን ይዘው መጡ ? የሚል ጥርጣሬ ፣ የስልክ ጥሪዎች ምን ሊሉኝ ነው ? የሚል ስጋት ይጥልብኛል ። ትላንት ሰላም ያሉኝ እንዲህ ብለው ነው ፣ ዛሬ ደግሞ ይህን ቃል ቀነሱ እያልሁ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በብሉይ በሐዲስ ፣ በእውነት ምስክሮች የጸናውን ፣ አንተ ለእኔ ያለህን በጎ አሳብ አቃልያለሁና ይቅር በለኝ ።
አዳምጣለሁ ይቅር በለኝ ። ስሜን ሲያቆላምጡ ደስ ይለኛል ፣ ውለታ መስሎኝ ካልከፈልሁ ያሰኘኛል ። ለስም አጠራሬ የምከፍል ብቸኛ ሰው የሆንሁ ይመስለኛል ። በሙሉ ስሜ ሲጠሩኝ ደግሞ ደስታዬ እንደ ካባ ወደ ኋላ ይወድቃል ። ሰዎች ሥራቸውን ስለ ሠሩ ከማመስገን በላይ ለእኔ ልዩ ውለታ ያደረጉልኝ መስሎ ያሳቅቀኛል ። ቁመናዬ በነፋስ ሽውታ ይነቃነቃል ፣ ቆዳዬ ትንሽ ሲነካ የሚቆስል ስስ ሆኗል ። እንኳን ችግር መጥቶ ፣ ሊመጣ ነው እያለ ይርዳል ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አንተን ሳይሆን ወደዚህ ዓለም ያላመጡኝን ፣ ከዚህ ዓለም የማይወስዱኝን ፤ እንደ እኔ ፈሪ የሆኑትን አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ሰዎች ቃላቸውን ሲያጥፉ ፣ የትላንት ንግግራቸው ከዛሬው ሲዘባረቅ አዳምጣለሁ ፣ ለምን ? ብዬ በቀጭን መርፌ ነፍሴን እወጋጋታለሁ ። አዎ አዳምጣለሁ ሰዎች ለሌላው ሰው መርዛም ዱለታ ሲዶልቱ ፣ እኔን ባይነኩኝም አዳምጣለሁ ። ሲያሙ ቆይተው ፣ ያሙት ሲመጣ አቅፈው ሲስሙት እታመማለሁ ። ወላጅ ቀብረው በሠልስቱ ስለ ውርስ ሲያወሩ አዳምጣለሁ ፣ ስለዚህ እደቅቃለሁ ።
በአካሌ ላይ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ገና ሞት እያለ መታመምን እፈራለሁ ። በመገናኛ ብዙኃኑ ስለ በሽታ ሲወራ እኔ እንደ ታመመ ሰው እንቅስቃሴ ማድረግ እጀምራለሁ ። አዎ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ትንሣኤና ሕይወት መሆንህን አምናለሁ እያልሁ በሽታን እሰጋለሁ ። ጠቢብ አልቻለም ሲባል በጆሮዬ የምሰማው እግዚአብሔር አልቻለም ብዬ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። እያንዳንዱን ቃል አጠራለሁ ፣ እንዲህ ያለው እንዲህ ለማለት ፈልጎ ነው እያልሁ አሰላስላለሁ ። እኔ እንደ ልቤ እየተናገርሁ ሰዎች ግን ችሎት ላይ ቆሞ እንደሚናገር ሰው በሰቀቀን እንዲያወሩኝ አደርጋለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። አሰቡትም አደረጉትም ፣ ተናገሩትም ዝም አሉትም ያው ነው ብዬ አረፋ መትቼ ፣ በሺህ አባዝቼ አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። በሁለት ጆሮ እየሰሙ ከሰው ጋር መኖር እንደማይቻል ባውቅም ፣ በትዕግሥት ማጣት የካብኩትን ብንድም አሁንም አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ምን ይሉኛልን ፈርቼ ሥራዬን ፣ ሐሜትን ተሳቅቄ ራእዬን ትቻለሁና ይቅር በለኝ !
ልጆቼ ስለ እኔ ያላቸውን የፍቅር ሙቀት አዳምጣለሁ ። “ብሞትስ ምን ትላላችሁ” ብዬ የቅኝት ፍተሻ አደርጋለሁ ፣ ገና ሳልሞት አላለቀሱም ብዬ ተስፋ እቆርጣለሁ ። ማዳመጥ አስክሮኝ ብሶትን እወልዳለሁ ። ከሰው ጋር በጨዋታ በሳቅ ውዬ ፣ ወደ ቤቴ ስመለስ የተናገርኩትን ሌሊት ሙሉ ከልሼ አዳምጣለሁ ። አስቀይሜ ቢሆንስ ብዬ እሰጋለሁ ፣ ደስታዬን ሳበላሽ አድራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስልክ ደውዬ በመጀመሪያው ጥሪ ካልተነሣ አዳምጣለሁ ። የመጀመሪያው ጥሪ በእኔ ትርጉም ፍቅር ነው እላለሁ ፣ ሦስተኛው ጥሪ ላይ ካልተነሣ ስላልፈለጉ ነው እላለሁ ። ደስታዬን ጨቁኜ ለራሴ አለቅሳለሁ ። ባልተጨበጠ ነገር የተጨበጠ ኀዘን ውስጥ እገባለሁ ። ሰዎቹን ሳገኛቸው ያን ጊዜ ስልክ ያላነሣሁት ታስሬ ፣ ታምሜ ነበር ሲሉኝ በራሴ አፍራለሁ ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ስብከት ስሰማ አዳምጣለሁ ፣ ሰባኪውን ካወቅሁት የእኔን ምሥጢር እያወጣ ነው ብዬ ቃልህን ለመስማት እንኳ እፈተናለሁ ። እኔን ሊናገር ፈልጎ ነው እያልኩ አደባባይህን ፣ የንስሐ ድምፅን እጋፋለሁ ። አዳምጣለሁና እባክህ ይቅር በለኝ ።
ሰዎች የትዳር ውድቀታቸውን ሲናገሩ የእኔም ጉድ ባልሰማው ነው እንጂ ይህን ይመስላል እያልሁ ቤቴን አውካለሁ ። ኑሮዬን አፈርሳለሁ ። ለእልህ ስላደረግሁት አልቆጭም ። ጉልበቴ በማይረባ ነገር ያልቃል ። ቃልህ ተተርጉሞ እንኳ አይገባኝም ፣ የሰዎችን ነጠላ ቃል ግን ተርጕሜ እጣላለሁ ። ትላንት የሰማሁት ቃልህን ረስቼዋለሁ ፣ የሃያ ዓመት ቂም ግን በውስጤ ሕያው ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ ። ደግ ቃል ቶሎ አይገባኝም ። ትምህርትም ጎበዝ አይደለሁም ። ክፉ ቃል ግን ያለ አስተማሪ ይገባኛል ፣ ፈነካክቼ – አብጠርጥሬ እጋተዋለሁ ። አቤቱ ያን ጊዜ መተንተን ይሆናል ፣ የማይጠቅም መተንተን ነው ፤ ያን ጊዜ ሁሉም ነገር ብልጭ ይልልኛል ፣ የማይጠቅም ብርሃን ነው ። ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል ፣ የማይጠቅም ልቅሶ ነው ። ማዘንስ ሰዎች ስለበደሉኝ ሳይሆን ሊያስቀይሙህ የማይገባውን አንተን በማሳዘኔ ነው ። አዳምጣለሁና ይቅር በለኝ።
ተፈጸመ
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 28 ቀን 2016 ዓ.ም.