የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

አፄ ቴዎድሮስና የመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅራቸው

                                                               ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 12 2004

ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚታወቀው የታሪክ ዘመን ኢትዮጵያ ሀገራችን የነበራት የግዛት አንድነት ተሸርሽሮ፣ በመኳንትና በመሳፍንት ተከፋፍላ አንዱ አንዱን አሸንፎና አስገብሮ የበላይ ለመሆን እጅግ ደም አፍሳሽ የሆኑ በርካታ ጦርነቶች የተካሄዱበት የጨለማው ዘመናችን አንድ የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ በታሪክ ገናና የሆነችውን፣ በጥንት ሥልጣኔዋ ቀደምትና አንቱታን ያተረፈችውን ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንዲህ በግዛት ተበጣጥሳና ተከፋፍላ መኖሯ እጅግ እንቅልፍ የነሳቸው አፄ ቴዎድሮስ ገናናዋንና ታላቂቷን ኢትዮጵያን እንደገና በዓለም መድረክ ከፍ ብላ ትታይ ዘንድ ትልቅ ራእይ አንግበው የተነሡ ሰው ነበሩ፡፡ ሀገራቸውን በአውሮፓዊው ዘመናዊነት ለማዘመንና ከኢትዮጵያ አልፈው ኢየሩሳሌምን ነፃ ለማውጣት እቅድ የነበራቸው አፄ ቴዎድሮስ ወደ ንግሥና በመጡበት ማግሥት ያደረጉት ዋነኛ ነገር ቢኖር፡-

ወታደሮቻቸው፣ ተከታዮቻቸው እና ህዝባቸው በሥርዓት እንዲኖር እግዚአብሔርን የሚፈራ ለሕግና ለሥርዓት ተገዢ እንዲሆን በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የታነጸና ቆራቢ እንዲሆን ጭምር ጥብቅ የሆነ ትእዛዝ ማስተላለፋቸው ነው፤ ይኼም በዘመኑ አማካሪያቸው የነበሩት እንግሊዛውያኑ ጸሐፍትና ሚስዮናውያን በመጻሕፍቶቻቸው ገልጸውታል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ይህን ትእዛዝ ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ጭምር ምሳሌ በመሆን በተግባር ያሳዩ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በሥርዓተ ንግሥናቸው ጊዜ ከሚስታቸው ከወ/ሮ ተዋበች ጋር ቆርበው ሠራዊታቸውንም ያልቆረብህ እጣልሃለሁ ብለው አዋጅ ቢነግሩ፡- ‹‹ከሠራዊታቸውም ከመኳንንቱም እግዚአብሔር የመረጣቸው እየተገኙ ቆረቡ፣ የመንግሥትም ሥርዓት በየሀገሩ ተነገረ፡፡ ለቤተ ክህነት ኃላፊዎችና ለተከታዮቻቸው መቁረብ ለምን እንዳስፈለጋቸው በእግዚአብሔር ሥርዓት መኖር የእሱን ይቅርታ፣ ማለትም ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ያስገኛል›› በማለት ይህን አዋጅ ማስተላለፋቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንጋፋ የታሪክ ተመራማሪና መምህር የነበሩት ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ Kasa and Kasa: Papers on the Lives, Times and Images of Tewodros and Yohannes (1855-1889) በሚል ርእስ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባሳተመው የጥናት መጽሔት ላይ ‹‹የቴዎድሮስ ዓላማዎች ከየት እንደመነጩ›› በሚለው ጥናታዊ ጹሑፋቸው ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር መርዕድ በዚሁ ጥናታዊ ጹሁፋቸው እንደገለጹት አፄ ቴዎድሮስ በ1862 ዓ.ም ለእንግሊዟ ንግሥት ለቪክቶሪያ በፃፉት ደብዳቤያቸውም፡-
‹‹ኢትዮጵያ በውስጥ ችግር የታወከችውና በውጭ ጠላቶች ተደፈረችው የእግዚአብሔርን ሥርዓት ባለመከተላችን ነበር ብለው ገልጸዋል፡፡›› ይህን የአፄ ቴዎድሮስን እምነት በመከተል ይመስላል ጸሐፊ ትእዛዛቸው አለቃ ዘነብ የቴዎድሮስ መነሣት በዘመኑ እጅግ ተንሠራፍቶ የነበረውን የሞራል ውድቀት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፍኖ የነበረውን ምስቅልቅል፣ አስመሳይነትንና አድርባይነትን ለማስወገድ በእግዚአብሔር ተመርጠው የተላኩ መሆናቸውን በማመን እንዲህ የገለጹት፡-
‹‹…ይህንን ክፋት ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በሃበሻ ላይ ንጉሥ ቴዎድሮስን አስነሣ ምንዝር የማይወድ፡፡ ገንዘብ ሐሰት ስርቆት የማይወድ፡፡ ሸፍጥም ሁሉ የማይወድ፡፡ እግዚአብሔርን የፈራ፡፡ እጅግ የሚሰጥ፡፡ እንግዳን የሚወድ ለታመመ የሚያዝን በአንዲት ሴት የቆረበ…፡፡››
አፄ ቴዎድሮስን ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ በሰዎች ተወዳጅነትን ካፈሩላቸው ጠባዮቻቸው መካከል ሐቀኝነታቸውና ታማኝነታቸው ነበሩ፣ በተጨማሪም እጅግ ሃይማኖተኛና ለተዋህዶ እምነታቸው ቀናኢ እንደነበሩ የውጭ ሀገራትም ሆኑ የሀገራችን ጸሐፊዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፤ አፄ ቴዎድሮስ በእጅጉ መጻሕፍትን መመርመር የሚወዱ አንባቢና አስተዋይ ንጉሥም ነበሩ፡፡ በቤተ መንግሥታቸው አቅራቢያም የሃይማኖት፣ የታሪክ፣ የጥበብና የፍልስፍና መጻሕፍትን እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሀገራት መንግሥታትና ግለሰቦች ጋር የተፃፃፏቸውን ደብዳቤዎችና ታሪካዊ ሰነዶችን በማደራጀት ያስቀምጡ እንደነበረና በወቅቱ እነዚህን ውድና ብርቅዬ በርካታ የታሪክ መዛግብት፣ የሃይማኖት መፃሕፍትና ቅርሶች በመቅደላው ጦርነት በእንግሊዝ ወታደሮች ሲዘረፉና ሲቃጠሉ የታዘቡ የውጭ ሀገራት ጸሐፍት በጉዞ ማስታወሻቸው ላይ ጽፈውልን አልፈዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አፄ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ቅዱስንና ለሌሎች መንፈሳዊ ጹሑፎችን የሚተረጉሙ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጸሐፍትን ያበረታቱ ነበር፡፡ ለአብነትም፡-
እ.ኤ.አ በ1856 ዓ.ም ማርቲን ፍላድ የተባለው እንግሊዛዊው ሚስዮናዊ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 300 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ በመምጣቱ አፄ ቴዎድሮስ ደስታቸውን በመግለጽ፣ ‹‹ጠመንጃ የሚሠራ ሰው ለምን አላመጣችሁም›› እንዳሉና ከመጡትም መጻሕፍት ውስጥ በግእዝ ቋንቋም የታተሙ ስለነበሩባቸው፣ ‹‹ይህን ማንም የማይገባውን ለምን አመጣችሁ፣ ምን ጥቅም አለው ብላችሁ ነው፤ የተተረጎመው በጣም ጥሩ ነው፡፡›› በማለት ድጋፋቸውንና ቅሬታቸውን አሰምተው እንደነበር T.L Kane የተባለ አውሮፓዊ ጸሐፊ “Ethiopian Literature in Amharic” በተባለ መጽሐፉ ዘግቦታል፡፡
መጻሕፍት ቅዱሳት ወደ አማርኛ እየተተረጎሙ በሀገር ውስጥ መሰራጨታቸውን በማድነቅ አፄ ቴዎድሮስ፡-‹‹በእግዚአብሔር ኃይል እና ጸጋ መጽሐፍ ቅዱስን የሰጡንንና ጥንት ጥቂት ብቻ ሲኖሩን አሁን መንደሩ ሁሉ ባለመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሆን ያደረጉትን እንግሊዞችን እንዴት እንረሳልን›› በማለት መናገራቸውን ይኽው T.L Kane ጸሐፊ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ ገልፆታል፡፡
በአንድ ወቅት ሚስዮናዊው ማርቲን ፍላድ ‹‹የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ›› በሚል አርእስት አንድ መጽሐፍ በአማርኛ አዘጋጅቶ ለማሳተም ማሰቡን ንጉሡ አፄ ቴዎድሮስ ሰምተው መጽሐፉን እንዲያመጣላቸው አድርገው ካነበቡት በኋላ፤ ‹‹ይህን መጽሐፍ የፃፍኽው አንተ ነህን ብለው ጠየቁ፡፡›› ቄስ ፍላድም፡- ‹‹አዎን እኔ ነኝ የፃፍሁት›› ብለው መለሱላቸው፡፡ ‹‹የጻኽፈው ስለምንድን ነው?›› ብለው አፄ ቴዎድሮስ ቢጠይቋቸው ቄስ ፍላድ እንዲህ ብለው መለሱ፡- ‹‹ያገርዎ ሕዝብ በጎ ነገር እንዲማሩ ብዬ ወደ ሀገሬ ወደ አውሮጳ ሰድጄ ለማሳተም አስባለሁ፤ ከታተመም በኋላ ብዙ መጻሕፍት ወደዚህ አስመጣለሁ፡፡›› በማለት ሲመልስ፣ ንጉሡም መልሰው፡- ‹‹ይህ መጽሐፍ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ብመልስልህ ትወዳለህ›› ብለው ቢጠይቁ መምህር ፍላድ፡- ‹‹አዎን! እንዳሳትመው ቢመልሱልኝ በወደድሁ ነበር አሉ፡፡›› ንጉሡም ጥቂት ዝም ብለው ቆይተው እንዲህ አሉ፡- ‹‹እኔ ይህን አስቀራለሁ፣ አንተ ግን ሌላ ጻፍ፡፡›› በማለት ልመናዊ የሆነ ትእዛዝ አስተላለፉለት፡፡ ቄስ ማረቲን ፍላድም እንደገና በብዙ ድካም ሁለተኛ መጽሐፍ ጽፈው ወደ አውሮፓ ልከው አሳትመው አያሌ ሺህ መጻሕፍት ወደ ኢትዮጵያ አስመጡ፡፡
በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ብዙ የአማርኛ መጻሕፍት ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ከገቡም በኋላ ንጉሡ በየአብያተ ክርስቲያናቱ እንዲነበቡ እንዲደረጉ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጸሐፍት ዘግበዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1864 ዓ.ም 10000 ሐዲስ ኪዳን የአማርኛ መጻሕፍት በሀገር ውስጥ እንደተሰራጩና ሌሎች 14000  ግልባጮች በመታተም ላይ እንደነበሩ እንዲሁም አፄ ቴዎድሮስ በመጀመሪያ የመንግሥትነት ዘመናቸው ከሚስዮናውያን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርተው እንደነበርና መጽሐፍ ቅዱስ በአማርኛ በሀገራቸው ውስጥ እንዲሰራጭ ድጋፍ ይሰጡ እንደነበር ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪና ምሑር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፡- The Foundation of Education, Printing, Newspaper, Book Production, Libraries and Literacy in Ethiopia በሚል ጥናታዊ ጹሑፋቸው ገልጸዋል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ለሺህ ዘመናት የሰውን ሥጋ፣ ነፍስ እና መንፈስ የገዛ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣  ሕፃን፣ ትንሽ፣ ትልቅ፣ ወታደር፣ ጭፍራ፣ ሠራዊት፣ ንጉሥ፣ ልዕልት…ወዘተ. ሳይል የብዙዎችን ልብ የማረከ ዘመናትን የተሻገረ ድንቅ የሆነ የእግዚአብሔር የዘላለም እቅድ፣ ፈቃዱና ለሰው ልጆች ያለው መልካምና በጎ ፈቃዱ ዘላለማዊው ቃል ኪዳኑ የተገለጸበት ሕያው መጽሐፍ እንደሆነ በብዙዎች የተመሰከረለት ነው፡፡ ይሄ ድንቅ የሆነ የእግዚእብሔር እስትንፋስ የሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ብርቱ፣ ጨካኝ፣ አንበሳ ልበ- ጀግና የተባሉትን የአፄ ቴዎድሮስን ልብ እንኳ ለመግዛት/ማቅለጥ የቻለ ብቸኛ መጽሐፍ ነበር፡፡ ስለዚህ ድንቅና ሕያው መጽሐፍ ብዙዎች ተግዘዋል፣ እስከ ሞት ድረስም ተደብድበዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ ክቡር ሕይወታቸውን ጭምር ሳይሳሱ መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፡፡ ይህ ድንቅና ብርቅዬ መጽሐፍ ዛሬ እንዲህ በጓዳችን እንደ ልብ እንዲገኝ ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል፣ ይሄ ደግሞ ለከንቱ አይደለም! እጅግ ለከበረው፣ የእግዚአብሔር ኃይሉ፣ ክንዱ፣ ጥበቡ የሆነው፣ የተሰወረ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው!!!
ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው የዘላለም ፍቅሩና ምሕረቱ የተገለጠበት፣ በአንድያ ልጁ በጌታችን እና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክስርስቶስ ቅድስት እና ክብርት ለሆነችው ለሙሽራይቱ ለቤተ ክርስቲያን ክቡር ነፍሱን አሳልፎ የሰጠበት የመስቀሉ የፍቅር ገድል የተተረከበት ድንቅዬ መጽሐፍ ነው፡፡ ንጉሥ ቴዎድሮስ ይህ መጽሐፍ ለእሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያንና ለሕዝባቸው ማስተዋልንና ዕውቀትን የሚሰጥ ድንቅዬና ብርቅዬ መጽሐፍ መሆኑን በመገንዘባቸው ነበር በብዛት ተተርጉሞ ለሁሉ እንዲዳረስ ብርቱ ጥረት ያደርጉ የነበሩት፤ በዚህ በእኛ ዘመን ስንቶቹ ባለሥልጣኖቻችን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና አባቶቻችን፣ እኛስ ከዚህ መጽሐፍ ጋር ያለን ወዳጅነት ምን ይመስል ይሆን? ለመልሱ ሩቅ መሄድ የሚያስፈልገን አይመስለኝም፣ ያለንበት መንፈሳዊ እና ሥጋዊ ጉስቁልና የሚያሳየን ሐቅ ቢኖር ምን ያህል ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሆነው ጥበብ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ከሚያገናኘን ከዚህ ቅዱስ መጽሐፍ እንደተቆራረጥን ነው፡፡  

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።