የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ኢካቦድ/ክብር ከእስራኤል ለቀቀ/

ቤተ ጳውሎስ፤ ማክሰኞ ግንቦት 7 2004 ዓ.ም.
ዘመኑ ዘመነ መሳፍንት ነው፡፡ ሁሉም ሰው ከፊት ለፊቱ የገጠመውን የሚያነሣበት፣ ለአሁን መልካም መስሎ የታየውን የሚያደርግበት፣ የሚያስደስተው ከሆነ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚሽርበት፣ ሥጋው ከተመቸው ኅሊናን ወግድ የሚልበት፣ ሁሉም አንድ ሆኖ ካህኑና ምእመኑ ለዝሙት የሚቃጠሩበት፣ መሪና ተመሪ ተቀጣጥረው የሚሳከሩበት፣ የልጅ ምክር አገር የሚገዛበት፣ ተው የሚል ገላጋይ ጠፍቶ ሁሉም የራሱን አረር የሚተኲስበት፣ አዋቂዎች ጨቅጫቆች ጠቢባን ዕብዶች የተባሉበት፣ ሽማግሌ የጠፋበት የዕድሜ ባለጠጎች የምግባር ድሆች የሆኑበት፣ ነቢያት ለሀብታሞች ትንቢት የሚናገሩበት፣ ሰባክያን እንደ ቃሉ ሳይሆን እንደ ዘመኑ የሚሰብኩበት፣ ቁም ነገር ዋጋ ያጣበት፣ ድሆች የተገፉበት፣ የሙት ልጆች ሰብሳቢ ባልቴቶች ጧሪ ያላገኙበት፣ ቤተ መንግሥትና ቤተ ክህነት በሐሰት ፍቅር ያበዱበት፣ አንዱ አንዱን እንዳይገስጽ መስፍኑና ካህኑ በምግባር የወደቁበት፣ ከቤተ እግዚአብሔር መልካምነት ጠፍቶ ያለቦታው ከዓለም የሚፈለግበት፣ እግዚአብሔር ትልቅ ሰው አጥቶ ከ3 ዓመት ሕጻን ጋር የሚነጋገርበት፣ አገሩ ክፍት ቤተ መቅደሱ ጎዳና የሆነበት፣ ወደ ቤተ መቅደስ የመጡ ደናግላን የሚደፈሩበት፣ የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተቃለለበት፣ የመባ ሳጥን የሚሰበርበት፣ የእግዚአብሔር ተግሣጽ የሚናቅበት፣ አለቃ ከሎሌዎች ጋር ጉቦ የሚቀባበልበት፣ የድሃይቱን ጩኸት የሚሰማ የጠፋበት፣ በጥቂቶች ጥጋብ የምስኪኗ ረሀብ የተረሳበት፣ ከእኛ በላይ ነፋስ እንጂ እግዚአብሔር የለም የተባለበት ዘመን ነበር፡፡
የተረፈም የለ፡፡ ንጹሕ ነኝ ብሎ በአደባባይ የሚታጠብ ጲላጦስ ከመሆን አያመልጥም ነበር፡፡ መንፈሳዊነት ቀርቶ ሰብአዊነትም የጠፋበት፣ ሽማግሌና ሕጻን ሁሉም በ“በለው” ምክር አንድ የሆኑበት ዘመን ነበር፡፡ ቤተ መንግሥቱ ቤተ ክህነቱ ጠፍቷል፡፡ አካላዊ ህልውናው ይታያል፣ የንጉሥነትና የካህንነት መገለጫው ግን ጠፍቷል፡፡ በወቅቱ የነበረው ሊቀ ካህን ዔሊ ነበር፡፡ ሊቀ ካህኑ ዔሊ፡-
1.     ያሻውን የሚናገር
2.    ልጆቹን የማይመክር
3.    ክፉ ቀን የሚመጣ የማይመስለው
4.    ክፉ የመጣ ቀን ጭንቅ የሚገድለው ነበር፡፡
ሊቀ ካህኑ ዔሊ ዕንባ ለሚያፈስሱ እናቶች የሚያዝን ልብ አልነበረውም፡፡ ዕንባው የሀዘን ጭማቂ ሳይሆን የስካር ውጤት መስሎ ይታየው ነበር፡፡ ሐና ልቧ ተሰብሮ፣ ንቀትንና ውርደትን መሸከም አቅቷት በእግዚአብሔር ፊት ስታለቅስ፡- “ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅን ከአንቺ አርቂው” ያላት ነው (1ሳሙ. 1÷14)፡፡ ስካርንና ሀዘንን የማይለይ፣ ዕንባ የማያስደነግጠው ነበር፡፡ ሊቀ ካህኑ ዔሊ የማያስተውል የተናገረውን ብቻ የሚያዳምጥ በመንፈስ የደነዘዘ ነበር፡፡

የሊቀ ካህኑ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፍንሐስ ቤተ መቅደስን የሚዘርፉ፣ ለጸሎት ከመጡት ደናግላን ጋር በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚተኙ ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ልጆችህን ምከር ቢለው ልጆቼ ከሚቀየሙኝ እግዚአብሔር ይቀየም ብሎ በልጅ ስስት የወደቀ ሰው ነበር፡፡ ለእውነት የሳሳንላቸው ልጆች ግን ለጥፋትና ለሞት ለአገርም ውርደት ምክንያት እንደሚሆኑ በካህኑ በዔሊ ከደረሰው እንማራለን፡፡
ሊቀ ካህኑ ዔሊ ክፉ ቀን የሚመጣ አይመስለውም ነበር፡፡ እኛ ብንሳሳት ማን ያርመናል? በሚል ስሜት የተቀመጠ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መዓት ሊወርድ የዳመነ ቢሆንም ሥልጣኑ ከመዓቱ የሚያድነው መስሎታል፡፡ መገሰጽን እንደ መደፈር ቆጥሮት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም “ያከበሩኝን አከብራለሁና የናቁኝም ይናቃሉና” ቢለውም ምንም አልመሰለውም (1ሳሙ. 2÷3ዐ)፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሽማግሌ ከቤቱ እንደሚታጣ ተነገረው፡፡ ሽማግሌ ማጣት ከእግዚአብሔር ቅጣት አንዱ ነው (1ሳሙ. 2÷31)፡፡ ካህኑ ዔሊ ግን የወደደውን ያድርግ ብሎ እግዚአብሔርን ናቀ፡፡
ሊቀ ካህኑ ዔሊ የማይመጣ መስሎት የደፈረው መከራ በመጣ ጊዜ ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ የልጆቹን ሞት በሰማ ጊዜ፣ ታቦቱም መማረኩን በተረዳ ጊዜ ከመቀመጫው ወድቆ ሞተ (1ሳሙ.4÷12-18)፡፡ ዔሊ እንደ ስሙ ዔሊ ሆኖ በማዝገም ለእስራኤል ውርደትን አመጣ፡፡ የመሪነቱ ትልቅ ድካም የእኔ መውደቅ የእኔ ብቻ ነው የሚል አሳብ ነበረው፡፡ የሚመራው ሕዝብ እንዳለ ዘንግቷል፡፡
ካህናት የነበሩት አፍኒንና ፊንሐስ ትልቅ ነውረኞች ነበሩ፡፡ ነውራቸውም፡-
1.     የእግዚአብሔር የሆነውን ለራሳቸው ያውሉ ነበር
2.    ደናግላኑን ያስነውሩ ነበር፡፡
አፍኒንና ፊንሐስ ቢመከሩም እያባበለ በሚመክራቸው አባት ሌቦችና ቀማኞች፣ በነውር የሚወዳደሩ ሆነው ነበር፡፡ ምእመኑ ልጆቹን ወደ ቤተ መቅደስ መላክ እስኪፈራ ካህናቱ ነውረኞች ቤተ እግዚአብሔርም የጨካኞች ዋሻ ሆና ነበር፡፡
ኃጢአት ስለበዛ ፍልስጤማውያን ሊዋጉአቸው ቀረቡ፡፡ ሕዝቡም ሊዋጋ ቢወጣ ተሸነፈ፡፡ አራት ሺህ ሰው አለቀ፡፡ በዚህ ጊዜ የቃል ኪዳኑ ታቦት ይምጣ አሉ፡፡ አፍኒንና ፍንሐስም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው መጡ፡፡ እግዚአብሔር እንደተለያቸው አላወቁምና እልል አሉ፡፡ ነገር ግን በዚያ ቀን ጦርነት 3ዐ ሺህ ሠራዊት ረገፈ፡፡ ታቦቱ ተማረከ፡፡ አፍኒንና ፍንስሐም በጦር ሜዳ ሞቱ (1ሳሙ. 4÷1-11)፡፡
ከሁለቱ ካህናት አንዱ የሆነው የፊንሐስ ሚስት ድርስ እርጉዝ ነበረች፡፡ ታቦቱ እንደ ተማረከ ካህናቱም እንደ ሞቱ በሰማች ጊዜ ምጥ ደርሶባት ነበርና ተንበርክካ ወለደች፡፡ እርስዋም ከደስታ ይልቅ ሀዘን ውጧት ነበርና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ ስትል የሕጻኑን ስም ኢካቦድ ብላ ጠራችው (1ሳሙ. 4÷19-22)፡፡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ተማርኳልና ክብር ከእስራኤል ለቀቀ አለች። ታቦቱ መመሪያ የያዘ የቃል ኪዳን ሰነዱ ማኅደር ነበር። መመሪያው ከተወሰደ መድረሻው ገደል ነውና ኢካቦድ ብላ በልደት ቀን አለቀሰች።
ይህ ዘመን በሁለንተናው ዘመነ መሳፍንትን ይመስላል፡፡ ዳኛ የሚሰርቅበት፣ ወንጀለኛ በኩራት የሚሄድበት፣ የሕፃናት ምክር የሰለጠነበት፣ ሽማግሌ በአገር በመንደሩ የታጣበት፣ አገልጋዮች ምእመናንን የሚያስነውሩበት፣ … ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን የሚያደርግበት ዘመን ነው፡፡ ሕዝቡ መካሪ ካህን፣ ካህኑ ተቆጪ ሊቀ ካህን ያጣበት፣ አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያዋን እንደ ጣለች መርከብ በወቅቱ ነፋስ የሚነዳበት፣ የበላዮች ነውርን ነውር ብለው ያላወገዙበት፣ የበታች አገልጋዮች በገንዘብና በዝሙት የረከሱበት የአፍኒንና የፊንሐስ ዘመን ነው፡፡
አገራችንና ቤተ ክርስቲያናችን የክብር ደጃፍ፣ የክብር እልፍኝ፣ በክብር ቃላት ያሸበረቁ ነበሩ፡፡ ታናሽ ወንድም ታላቅ ወንድሙን አንቱ የሚልበት ንጉሥ የሚፈራበት፣ ጳጳስ የሚታፈርበት አገር እንዲህ ገመና የመገላለጫ አገር መሆኑ ኢካቦድ ክብር ከኢትዮጵያ ለቀቀ ያሰኛል፡፡ የበላዩ ለበታቹ የማያዝንበት የበታቹ ለበላይ የማይገዛበት አለቃና ጭፍራ የጠፋበት፣ ሁሉ ተናጋሪ ሆኖ ሰሚ፣ ሁሉ ከሳሽ ሆኖ ዳኛ የጠፋበት፣ ትውልዳችን በነውር ያለቀበት ኢካቦድ የእኛ ዘመን ነው፡፡
አባቶች እንደ ልጆች የሚያስቡበት፣ ልጆች ሽበት እየላጩ የሚሳደቡበት፣ ቤት ፈርሶ ሁሉም ነገር አደባባይ የሆነበት፣ በእግዚአብሔር ምሕረት የሚደነቅ ጠፍቶ ሰው በሰው ኃጢአት የሚደነቅበት፣ ተኰናኙ ሰው ኰናኝ የሆነበት፣ ሰው ስለ ሰው እያወቀ ስለ ራሱ የረሳበት፣ ቅዱስ መባል እየተፈለገ ቅዱስ መሆን የተናቀበት፣ አማኝ ጠፍቶ ቡድንተኝነት የደራበት፣ ትውልዳችን በነውር አገልጋይ በጭካኔ የሚወዳደርበት፣ የአገር ክብር፣ የቤተ ክርስቲያን ፍቅር፣ የአባቶች ምክር፣ የልጆች ወዝ የጠፋበት ዘመን ነው፡፡ ምእመኑ እልል ይላል። አገልጋዩም እልል ማሰኘት ቀላል የስብከት ዘዴ ሆኖለታል። እልልታው ግን የድል ነው ወይስ የሽንፈት ብለን መመርመር አለብን። ጦጣ ታስራ ትዘፍናለች እንዲሉ መታሰራችንን ረስተን መዝለሉ ለንስሐ ጊዜ አለመውሰዱ መጪውን ያከብደዋል። አባቶችም ምእመናንም ለንስሐ መዘጋጀት ግድ ይላቸዋል።
ይህ ሰዓት የመጨረሻው መጨረሻ ነው፡፡ ፈጥነን ንስሐ ካልገባን የፍልስጤማውያን ሰይፍ እየተሳለ የእግር ኮቴአቸው እየተሰማ ነውና ኃጢአታችን አሳልፎ እንዳይሰጠን ዛሬ ልናውቅበት ይገባል። ዛሬ የሸኘነው ክብር ነገ በልመናም ላይመጣ ይችላል፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦት ዛሬም ተማርኳል። የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ጠፍቶ ሁሉም የተንኮል አሰልጣኙን በጓዳ ሸሽጎ ይታኮሳል። የእግዚአብሔር ቤት የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ርቆት የልጅ ምክር ከሰለጠነበት ፍጻሜው የከፋ ነው።
                       እግዚአብሔር ለሁላችንም አስተዋይ ልቡና ያድለን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ