የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እመ አምላክ – የአምላክ እናት

ብዙ እረኞች በምድር ላይ አሉ ። ነገር ግን መንጋቸውን በትጋት የሚጠብቁ ፣ ከብርዱ የተነሣ ከብቶቹ እንዳይሞቱ እሳት የሚያነድዱ እረኞች ለልደቱ ተጋበዙ ። እርሱ እረኛ ይወዳል ። እረኛውን ያዕቆብን ለሕዝብነት ፣ እረኛውን ሙሴን ለመሪነት ፣ እረኛውን ዳዊትን ለንጉሥነት የመረጠ የቤተ ልሔም እረኞችን በልደቱ ጋበዘ ። ዳዊት በትንቢት ያየውን ፣ እረኞቹ በዓይናቸው አዩ ። ንጉሥ ያልታደለውን ድሆች ተቀዳጁት ። እረኛ የእግዚአብሔር ስም ነው ። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን መግቦት እረኛ በሚል ቃል ገልጧል ። እርሱ የተናቁትን ያከብራል ። የባርያን ሥጋ የለበሰ ፣ የድሆችን መጠሪያ እረኝነትን የራሱ መጠሪያ አደረገ ። ሰውነትንም ሙያንም አከበረ ። እርሱ ትልቁን ድርሻ ለመስጠት በትንሹ ድርሻ ይፈትናል ። እርሱ ትጉሆችን ይመርጣል ። ሰነፍ እረኛ አለና እርሱ ኖላዊ ትጉህ – ትጉህ እረኛ ተባለ ። ክፉ እረኛ አለና እርሱ “መልካም እረኛ” ተባለ (ዮሐ. 10 ፡ 11)። ቤተ መቅደሱን ትቶ በበረት ተወለደ ፣ ካህናትን ትቶ ለእረኞች ምሥጢሩን ገለጠ ። እርሱ በትልቅ ቦታና በትልቅ ሰው ሳይሆን እርሱ በትሑታን ይከብራል ። ድንግል ሆይ ! የእግዚአብሔርን አሠራር ታውቂያለሽና እረኞችን ባየሽ ጊዜ ተደንቀሻል ።

እረኞች ከምድር የተገፉ ናቸውና ወደ ሰማይ ቀረቡ ። እረኞች ከሰው የተጣሉ ናቸውና በእግዚአብሔር እቅፍ ውስጥ ዐረፉ ። እረኞች በነፍሳቸው ተወራርደው መንጋውን የሚጠብቁ ናቸውና ለመሥዋዕትነት የመጣው ጌታ ልደቱን ገለጠላቸው ። መንጋ የእግዚአብሔር ሕዝብ ስም ነው ፣ እረኛም የእግዚአብሔር የመግቦቱ ስም ነው ። መንጋና እረኛ ተብለን ብንሰደብ ምስጋና እንጂ ስድብ አይደለምና ደስ ሊለን ይገባል ። እርሱ ለመንጋው ባለቤቶች ፣ ለበግ ነጋዴዎች ልደቱን አልገለጠም ። እርሱ ለእረኞች ፣ ብዙ ደክመው ጥቂት ለሚመሰገኑ ልደቱን ገለጠ ። ድንግል ሆይ የእግዚአብሔር ተግባር ላንቺ አስደናቂ ነው ። በመደነቅም ሰማየ ሰማያት ታሪጊአለሽ ። በምድር ዋጋቸውን ላላገኙ ፣ የተሻለ ሰጥተው ያነሰ ለሚቀበሉ እርሱ አምላካቸው ነው ። የበጉ ባለቤት ፣ የበጉ ነጋዴ በጥቂት ድካም ብዙ ገንዘብ ያገኛሉ ፣ በእረኛው ልፋት “ጌቶች” ይባላሉ ። ባለጠጎች ድሆች ላይ የተጣበቁ ናቸው ። በሰማይ ዋጋ የሚጠብቅ በምድር ያልተከፈለው ብቻ ነው ። ሁለት ዋጋ የለምና በምድር የምስጋናና የክብር ብዛት ሲጎርፍልን ወዮልን ! ድንግል ሆይ ልዕልቶችን ትቶ አንቺን ፣ ሮምን ትቶ ናዝሬትን እንደ መረጠ አይተሻልና በእረኞቹ ያሠራሩን አለመለወጥ አድንቀሻል ። ለአራስ ቤትሽ ፈትፍተው የሚያመጡ ወይዛዝርት አልተጋበዙም ፣ ፈትፍተው የሚያመሰግኑ እረኞች ግን ተጋበዙ ። ባለቅልጥሞቹ/ባለዝግን ወጦቹ ሳይሆኑ ባለ በገናዎቹ ተጠሩ ።

ልደቱን ለእረኛ ሳይሆን ለእረኞች ገለጠ ። እርሱ በኅብረት ላሉ እረኞች/አገልጋዮች ክብሩን ይገልጣል ። ክብር የሚሸሸው ተነጣጥለው ሲቆሙ ነው ። ቤት ከተለያየ መፍረሱ አይቀርም ። አሸዋው ከሲሚንቶ ፣ እንጨቱ ከብረት ፣ ድንጋዩ ከብሎኬት ፣ ግርፉ ከቀለም ሲለያዩ ቤት ይፈርሳል ። የተለያዩ እረኞች ባሉበትም አገልግሎት እየፈረሰ ይመጣል ። ድንግል ሆይ ! ከበጎች ጋር እንጂ ከእረኛ ጋር ኅብረት ያለው እረኛ ጠፍቷል ። አንዱ ባንዱ መመለጥ ሲስቅ ይውላል ። ለጽድቅ የመጡትን ምእመናን የተንኮል ሠራዊት ያደርጋቸዋል ። ወንጌል ፣ ወንጌል ባልገዛቸው ሰዎች ተጎድቷል ። አለማወቅ ሲነቀፍ ኖረ ፣ ዛሬ አለማመን ይነቀፋል ። ሰው ላመነው ይሞታል ፣ እኛ መኖር አቅቶናል ። ድንግል ሆይ ! የእረኞቹን ኅብረት ፣ የተጉላቸው መንጋዎችን ትተው ወደ ጌታ ሲመጡ እናጣቸዋለን የሚል ስጋት አልነበራቸውም ። መንጋውን ተወት አድርገው ለመጸለይ ፣ ለመጾም ፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለመፈለግ ሲመጡ የሚጨነቁትን አገልጋዮች እነዚህ ድሆች ገሠጹ ። የእግዚአብሔርን ፊት ስንፈልግ ጥቂት ሩጫ ፣ ብዙ ድል ይኖራል ። በሰከንድ የኤልያስ ጸሎት የ3 ዓመት ከመንፈቅ ጥያቄን መልስ አገኘ (1ነገሥ. 18 ፡ 36-37)። በጥቂት ስብከት ጴጥሮስ ሦስት ሺህ ሰው አሳመነ (የሐዋ. 2 ፡ 41)። ኤልያስ ሦስት ዓመት በጽሞና ፣ ጴጥሮስም አሥር ቀን በሱባዔ ነበሩ ።

ድንግል ሆይ ! እነዚህን እረኞች ባየሽ ጊዜ ሁሉን በፈጠረ ፣ ሁሉን በማይዘነጋው ፣ በፍጥረቱ ላይ አመሳሶ/ማበላለጥ በሌለው ልጅሽ ደስ አለሽ ። እነዚህን ድሆች ለመቀበል ቤት ፣ ለመመገብ ሌማት የለሽም ። ትልቁን ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስ ፣ ትልቁን ስቴ መድኃኒት ኢየሱስን ይዘሻልና አልተሳቀቅሽም ። አንዳንዱ የሚያልፈውን ሌላው የማያልፈውን ይጋብዛል ። ድንግል ሆይ! ለልብሰ መንግሥት የለበሰው ሄሮድስ አልመጣም ፣ ድሪቶ የለበሱት እረኞች ግን መጥተዋል ። ከሩቅ አገር ሰብአ ሰገል ሊሰግዱ መጥተዋል ። ሄሮድስ ግን በአይሁድ ጥቆማ ሊገድለው ወጥቷል ። ክርስቶስን የቅርቡ ይንቀዋል ፤ የሩቁ ያከብረዋል ። ስለዚህ ነው የሕንዱ መሪ፡- “ክርስቶስን ወደድሁት ፣ የእርሱን መንገድ ስለማይከተሉ ክርስቲያኖችን ጠላሁ” ያሉት ። ስለዚህ ነው ሰላማዊ ሰልፈኞች፡- “ክርስቶስ ሆይ ፈራጅ ልጆችህን ያዝልን” የሚል መፈክር ይዘው የወጡት ።

ድንግል ሆይ! እመ አምላክ የምንልሽ የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት ስለምንቀበል ነው ። አንቺ የአምላክ እናት ነሽ ። ጸጋ ሁሉ ቢደራረብ እዚህ ላይ አይደርስም ። መመረጥ ሁሉ ቢኖር ይህን አያህልም ። ሔዋን ከመበደልዋ ፣ አዳምም ከመሳቱ በፊት የነበረውን ሐዲስ ሥጋ ይዘሻል ። መንፈስ ቅዱስ አክብሮሻልና ንጽሐ ሥጋሽን ፣ ንጽሐ ልቡናሽን እናደንቃለን ።

ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ ፤ እግዚኦ ።

ትርጉም፡- ቅዱስ እግዚአብሔር ፣ ቅዱስ ኃያል ፤ ቅዱስ ሕያው የማይሞት ። ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ ። አቤቱ ይቅር በለን ።

አሜን !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ