የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እምነ – እናታችን

በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ወዳንቺ ተላከ ። ከስድስት ወር በፊት የዮሐንስን መወለድ ሊያበሥር ወደ ዘካርያስ ሂዶ ነበር ። ንጉሥ በሚያልፍበት ጎዳና ከመንፈቅ በፊት መልእክተኛ ይሄዳል ። የጠመመውን እያቀና ፣ የጎበጠውን እያስተኛ ፣ የጎደለውን እየሞላ ፣ የሻከረውን እያለሰለሰ የንጉሡን መንገድ ያቀናል ። ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅም በሥጋ ልደት ልጅሽን ስድስት ወር ይበልጣል ። እርሱ ለመልእክተኛነት ብቻ ተወልዷል ። ጧሪ ፣ ቀባሪ ለመሆን ፣ ባለትዳር ባለሀብት ለመሆን አልተወለደም ። እርሱ መንገድ ጠራጊ ነው ። የሰውን ልብ ማቅናት ጎዳና ከማቅናት ይበልጣል ። ሰው ሲሞሉት የሚጎድል ፣ ሲያለሰልሱት የሚሻክር ፣ ሲያቅፉት የሚገፈትር ፣ አበባ ሲሰጡት አፈር የሚበትን ነው ። ስለ ወዳጅ እሬት ይላሳልና ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ከባዱን ጉዞ ተጋጠመው ። እርሱ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለኤዶማውያን ለሄሮድስ ቤተሰብ ቅድስና የሚጨነቅ ፣ የነገሥታትን መንፈሳዊ ውበት የሚናፍቅ ነበር ። እርሱ እንደሚሰብከው ቃል ሰይፍ ነው ። ለመያዝ አይመችም ። ስለ አሕዛብ መሞትም የሚጨነቅ ፣ በግፍ ስለሞተው ሹም ሲከራከር በግፍ የሞተ ነው ። እርሱ በአጥቢያ የማያለቅስ የሁሉን ሕመም የራሱ ለማድረግ መንፈሳዊ ስፋት የተሰጠው ነው ።

እርሱ የሚወረስ ሀብት ፣ የሚጠፋ ስም የለውምና ስለ እውነት ከማንም መጣላትን አልፈራም ። ለእውነት ዋጋ እየከፈለ እንጂ እውነትን እየሠዋ ማንንም መወዳጀት አልፈለገም ። እምነ እናታችን ማርያም ሆይ እርሱም የአክስትሽ ልጅ ወንድምሽ ነው ። ልጅሽ አምላክ ፣ አክስትሽ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፣ የአክስትሽ ባል ሊቀ ካህናት ፣ የአክስትሽ ልጅ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ መንፈሳዊ ዘመድ የበዛልሽ እናታችን ነሽ ።

ስለ ሰው መዳን መልአኩ አንቺን ደስ ይበልሽ አለሽ ። ስለ ግል ጥቅም እንጂ ስለመላው ዓለም በረከት የሚደሰት ጥቂት ነው ። አንቺ ግን የሰው መዳን ይናፍቅሻልና መዳንም በአንዱ በእግዚአብሔር ነውና ደስ ይበልሽ ተባልሽ ። የአንቺ ደስታ ዓለም በእርሱ እንዲድን ፣ ዓለምም በልጅሽ እንዲያምን ነው ። ስለ ፀሐይ የማናመሰግነው ፣ ስለሚነፍሰው አየር ስብሐት ለእግዚአብሔር የማንለው የግል ስላልሆኑ ነው ። እናታችን ሆይ ስለ ጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ ደስ ይበልሽ ተባልሽ ። የግል ኑሮ የሌለሽ ሕይወትሽን ለእግዚአብሔር የሰጠሸ ነሽና ። የምናከብርሽ ክርስቶስን ንቀን ፣ የምንወድሽ አማኑኤልን ጠልተን አይደለም ። እርሱን ስለምናከብር እናከብርሻለን ፣ እርሱን ስለምንወድ እንወድሻን ። ሁሉ በክርስቶስ ይወደዳሉ ፣ እርሱ ግን ስለ ራሱ ይወደዳል ። ነቢያትን ብንወድ ስለ እርሱ ትንቢት ተናገሩ ብለን ነው ፣ ሐዋርያትን ብንወድ ስለ እርሱ ሰበኩ ብለን ነው ። ሰማዕታትን ብንወድ ስለ እርሱ ሞቱ ብለን ነው ፣ ደናግላንን ብንወድ ስለ እርሱ ኖሩ ብለን ነው ። አንቺን ብንወድሽ እውነተኛውን የጽድቅ መብል ፣ እውተኛውን የጽድቅ መጠጥ ወለድሽ ብለን ነው ። “ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን ።”

እምነ መንገዱ ረጅም ቢሆንም ደስታን ይዞ ማደር ፣ የምሥራችን ሰምቶ መቀዝቀዝ አይገባምና ወደ ተራራማው አገር ገሰገስሽ ። ቅዱስ ገብርኤል ከስድስት ወር በፊት በይሁዳ ኢየሩሳሌም ተላከ ፣ አሁን ደግሞ በገሊላ ናዝሬት ተገኘ ። የጸሎት መልስ በጸሎት ማማው ላይ ይመጣል ። ዘካርያስ በመቅደሱ ፣ አንቺም በትጋት ስፍራሽ የምሥራች መጣላችሁ ። ሔዋን ከስፍራዋ ብትታጣ ስፍራዋን አጣች ። ስለ ኤልሳቤጥ መፅነስ ብትሰሚ “ካረጁ ልጅ ምን ሊሠራ ነው?” አላልሽም ። የአብርሃም አምላክ ዛሬም በሥራ ላይ ነው ብለሽ ገሰገስሽ ። ትልቁ እግዚአብሔር ታናናሾችን አይንቅም ብለሽ ለማወደስ ተነሣሽ ። ደስታ ኃይል ይሆናልና በመቶ ኪሎ ሜትሮች ተጓዝሽ ። እግዚአብሔርን የያዘ አይፈራምና ያንን አስጊ መንገድ ብቻሽን አቋረጥሽ ። ባንቺም የሆነውን ፣ በኤልሳቤጥም የሆነውን የሰው አስረጂነት አይገልጠውምና በጊዜው ይገለጥለት ብለሽ አገልጋይሽ ዮሴፍን ዝም አልሽው ። እንደ ሰው ልማድ እጮኛ ተብሎ ቢጠራም አንቺ ግን አብ ለልጁ ማደሪያነት አጭቶሻል ። ባንቺ የሆነውን ሥጋውያን አይረዱትምና ዮሴፍ መጋረጃ ሁኖ ተሹሟል።

ተራራማውን አገር እንዴት ወጣሽ ? በሰው ደስታ ለመደሰት ይህ ሁሉ ፍጥነት የፍቅር እናት መሆን ነው ። ሴቶች ለሐሜት ሳይሆን ነገረ እግዚአብሔርን ለመነጋገር እንደሚገናኙ አንቺ ምስክር ነሽ ! አንቺም የፀነስሽው የዓለም ቤዛ ፣ ኤልሳቤጥም የፀነሰችው የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው ። ስለ ዓለም ጥቅም መደሰት መንፈሳዊነት ነው ። ልጅን ለግል ጥቅም ሳይሆን ለዓለም በረከት እንዲሆን መመኘት ትልቅነት ነው ። ባንቺ የሆነውን ተአምር በጥቂት መረዳት የምትችል ኤልሳቤጥ ናት ። ተአምርን ተአምር ከሆነላቸው ጋር ማውራት ዋጋ አለው ። ዕንቈን እሪያ ፊት ቢጥሉት ይረግጠዋል ፣ ይጫወትበታል እንጂ አያጌጥበትም ፤ ዋጋውን አያውቀውምና ። ዋጋን ከሚያውቁ ጋር ተአምራትን ማውራት ደስታ ይሰጣል ። እምነ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ሰው አጠገብሽ አለመኖሩ አላስጨነቀሽም ። የአማኑኤል እናቱ ለእኔ እኅቴ ልትሆኚ አይቻልም ። ለዮሐንስ ወንጌላዊ እነኋት እናትህ በማለት ልጅሽ ልጅ ሰጥቶሻል ። እኔም እምነ ጽዮን እልሻለሁ ። ትውልድ ነኝና ብፅዕት ነሽ እላለሁ ። ኃጢአት ያደከመን ፣ የደሙን ዋጋ ያላወቅን ልጆችሽ ከባለ ቅኔው ጋር እንዲህ እንልሻለን፡-

“እመቤቴ ማርያም ጠጅ እያማረሽ ፣
ማር አትይውም ወይ ? ሲቆርጥ ልጅሽ።”

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ