የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (10)

ተዋደዱ
“እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፥ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ”
(ዮሐ. 13፡34-35)።

ፍቅር ባንፈጽመው እንኳ ሁልጊዜ ሲነገር ደስ ያሰኛል። ፍቅር ሲኖሩት ደግሞ የበለጠ ያረካል። በዓለም ላይ የምናያቸው ኃጢአቶች በሙሉ የደግነት ወይም የርኅራኄ ችግር አይደሉም። ሁሉም ስህተቶች ግን የፍቅር እጦት የወለዳቸው ናቸው። ፍቅር የመልካም ተግባራት መነሻ ነው። የመልካም ተግባራት ማጣፈጫውም ፍቅር ነው። ያለ ፍቅር የሚደረግ ማንኛውም ደግነትና መሥዋዕትነት ቁጥሩ ከክፉ ነው። ፍቅር ብዙ ደንዳኖችን የሚያቀልጥ ኃይል ያላት ስትሆን ወደ ሞት የሚሄዱትን የምንታደግባት ምሥጢር ናት። ለማንኛውም ሰው የምንሰጠው ሀብት የለንም። ፍቅር ግን ለሁሉም ሰው የምንሰጠው ሀብት ናት። ሀብት ባነሡለት ቁጥር ይቀንሳል፣ ፍቅር ግን በሰጠን ቁጥር ትበዛለች። የእኛን ስጦታ የማይሹ ባለጠጎች አሉ። ፍቅርን ግን ሁሉም የሚሻት ለሁሉ የምታስፈልግ ናት። ሰዎች ፍቅርን ከሰው ቢያጡ ከውሻ የሚፈልጉት ያለቅድመ ሁኔታ የሚወዳቸው ስለሚፈልጉ ነው። ፍቅር የሰው ዘር ፍላጎት ነው። የዘመናችንን ጭንቀት የወለደው ራስ ወዳድነት፣ ፍቅር የሌለበት የኑሮ ዘዴ ነው።
ቤተ ክርስቲያንን ከኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ከሽርክናና ከዕድር ልዩ የሚያደርጋት ስብስቧ ፍቅር ስለሆነ ነው። ለፍቅር አምላክ እየዘመርን መጠላላት ትልቅ ውሸት ነው። ሰምተን መዘመር ይቻላል፣ ተሰምቶን አለመዘመር ግን በጌታ እንደ መዘበት ነው። ጌታ ሊያይ የሚፈልገው የልጆቹን ፍቅርና ኅብረት ነው። ጌታ ፍቅርን አዲስ ትእዛዝ አላት። ፍቅር ግን በኦሪትም ታዟል። አዎ ኦሪት “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ትላለች።  ጌታ ግን እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ ይላል። ጌታ የወደደን ነፍሱን እስከ መስጠት ነው። እኛም ነፍሳችንን እስክንሰጣጥ መዋደድ ይገባናል(ዮሐ.15፡13)። ትንንሽ ነገር በመስጠታችን ልንረካ አይገባም፣ ራስን መስጠትም ይገባል።

ጌታ ፍቅርን ሰንደቅ ዓላማ አድርጎ ሰጥቶናል። ባንዲራውን በሩቅ በማየት የእገሌ አገር ነው እንላለን። ሰዎችም በሩቅ አይተው የጌታ ደቀ መዛሙርት ናቸው የሚሉን ፍቅር ሲኖረን ነው። ጌታ የሰጠን ምልክት መዘመር፣ ነጠላ መልበስ፣ ሌላም አይደለም። ምልክታችን ፍቅር ነው። ልብ አድርጉ ብዙ ነገሮች እንደ ጎደሉን እንናገራለን። የጎደለን ግን ፍቅር ነው። ፍቅር ቢኖረን ሙግታችን ወደ መግባባት፣ መጣላታችን ወደ መስማማት፣ መተማማታችን ወደ መሸፋፈን፣ ምሬታችን ወደ መደናነቅ፣ መነካከሳችን ወደ መሳሳም፣ መነቃቀፋችን ዋጋ ወደ መሰጣጠት፣ ለጥፋት ማደማችን ለሥራ ወደ መተባበር ይለወጣል። እባክህን የነጻነት ባንዲራችንን ጥለናልና ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርን እንደ ገና አልብሰን!

ያጋሩ