የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (11)

ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ
“እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” (ኤፌ. 4፡32)።

ቸርነት የተለቀቀ የስጦታ ልብና እጅ ነው። ርኅራኄም አዘኔታ ነው። ይቅርታም ተጨማሪ ዕድል መስጠት ነው። እነዚህ ሦስት ነገሮች የእግዚአብሔር ጠባያት ናቸው። እርስ በርሳችን ቸሮች መሆን ይገባናል። ከቁሳቁስ ፍቅር የወገን ፍቅር ሊበልጥብን ይገባል። ፍቅራችን ስሌታዊ እንዳይሆን በነጻ መዋደድ ይገባናል። ምን እቀበላለሁ ሳይሆን ምን እሰጣለሁ? ማለትን መለማመድ ያስፈልጋል። ገደብና ፍርሃት ያለው ፍቅር እውነተኛ አይደለም። ለወገናችን ስናደርግ መደሰት ደግሞም እኛ ጋ የተቀመጠ መብቱን እንዳደረግን ሊሰማን ይገባል። ሰዎች በአገርና በወንዝ ልጅነት በሚረዳዱበት ዓለም ክርስቶስ ትልቁ መገናኛችን መሆኑን ማሰብ አለብን። የሰጠነውን ፍጹም እየረሳን ወገናችንን ብቻ ማሰብ ያስፈልጋል። እግዚአብሔር በሰጠን ልክ ቸርነትን አልተለማመድንም። ካለቀቅን አይለቀቅልንም። መስጠት የመቀበል መንገድ ነው።

እርስ በርስ መተዛዘን ይገባል። እውነተኛ ፍቅር ወገኔ አለው ሳይሆን ላይኖረው ይችላል፣ ምናልባት እርቦትም ሊሆን ይችላል የሚል አስተሳሰብ አለው። አያጣም፣ ምን ይሆናል የሚል አስተሳሰብ ፍቅር የተራቆተው ራስ ወዳድነት ነው። ልንዋደድ እንችላለን። ዕድሜ የሚኖረው ግን የሚተዛዘን ፍቅር ነው። ፍቅር እኔ ምን እሆናለሁ ሳይሆን እነርሱ ምን ይሆናሉ? ይላል።
ቸርነትና ርኅራኄ በሰላም ዘመን ነው። ሰላም ሲናጋ ግንኙነት ሲደፈርስ ይቅርታ የደፈረሰውን የማጥራት፣ የታወከውን ወደ ፀጥታ ወደብ የመውሰድ አቅም አለው። እግዚአብሔር ይቅር ያለን በክርስቶስ ነው። እኛም ይቅር ለመባባል ክርስቶስን ማየት አለብን። ያለ በደሉ የሰውን ክፋት በሙሉ ሳይከፋ የተቀበለውን ጌታ ማሰብ ይገባል። እኛስ የተራ ጉዳይ እንጂ ትንሽ ቢዘገዩ ያደረጉብንን እናደርግባቸው ነበር። እርሱ ግን በፈጠረው ዓለም ስደተኛ፣ በወደደው በሰው እጅ ሟች ሆኗል። ይቅር ለማለት ትልቁ አንቀጽ ክርስቶስ ነው። አብ እንኳ ይቅር ያለን ልጁን አይቶ ነው። እርስ በርሳችን ይቅር መባባል ይገባል። ተጣጥለን መሄድ እንችላለን። የምንሄድበትም ሰው ይቅር የምንለው እንጂ ፍጹም ሰው አይደለም።

ቸርነት እየጠፋ እንደሆነ ብልጣብልጥነት እየተፈታተነን እንደሆነ እናያለን። የጥርስ እንጂ የቸርነት ግብዣ እየጠፋ ነው። አደረግሁ የሚል ድምፅም ይሰማል። ማድረግ አስመክቶ ራስን እንደ ትልቅ ካዩበት ቸርነት ንግድ ሆነ ማለት ነው። ብዙ ፍቅሮች መተዛዘን የላቸውም። ሀዘኔታ ከሌለ ፍቅር እልህና መጠባበቅ ይሆናል። ያለሁት፣ ያለኋት እኔ ነኝ በሚል ስሜት መተዛዘን ለብዙ ጭንቀቶች መልስ ይሆናል። ይቅርታም የተሰበረውን ድልድይ ይገጥማል። ክርስቲያኖችን ከማስታረቅ ዓለማውያንን ማስታረቅ እየቀለለ መጥቷል። ዓለማውያን ቢራ አውርደው ይታረቃሉ፣ እኛ ግን ጌታ ቢወርድም አልታረቅም እንላለን። ይልቁንም ምክንያት የሌላቸው ጠቦች እየበዙ ናቸው። የማናውቃቸውን ሰዎች እንሳደባለን፣ በስማ በለው ጠብ እናባዛለን። ክርስቲያን ግን ለፍቅር የሚበጅ ነገር ያደርጋል እንጂ ጠብን አይዘራም።

እርስ በርሳችን ቸር፣ ርኅሩኅና ይቅር የምንባባል ያድርገን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ