የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /14/


ሰላምታ ተሰጣጡ
“በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ” /1ጴጥ. 5፡14/፡፡
ሰላምታ ፍቅርን የምንለዋወጥበት ትልቁ መንገድ ነው፡፡ ሰላምታ የንግግርና የግንኙነት መክፈቻ ነው፡፡ ቀላልና ማንም ሰው እንዲያደርገው የሚጠበቅበት ነው፡፡ እንኳን ከአዋቂዎች ከሕጻናትም የምንጠብቀው ሰላምታ ነው፡፡ ሰላምታ ቀጣዩን ሰዓትና ፍቅር የሚወስን ነው፡፡ ሰላምታ በፍቅርና በብሩህ ፊት ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ለማንም ሰው የሚያስፈልግ ስጦታ ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ ማንም ሰው ሊሰጠው የሚችል ሀብትም በውስጡ አለ፡፡ እርሱም ፍቅር ነው፡፡ ሰላምታ ልምምድ ሊያስፈልገው ይችል ይሆናል፡፡ ሰላምታን ለመስጠት የሚከብዳቸውና ቢሰጡም አርኪ ያልሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ሰላምታ የፍቅር ልብና የተቀደሱ ቃላት ያስፈልጉታል፡፡ ይልቁንም በሰላምታችን እግዚአብሔር ስለሚመሰገን ሰላምታ ትልቅ የአምልኮ መንገድ ነው፡፡ ዛሬ ሰላምታም አልቆ ሰዎች በምልክት፣ ሲያልፍም ዝም ወደ መባባል ደርሰዋል፡፡ ሰላምታ ከጀመርኩ ሌላው ነገር ይቀጥላል በሚል ሂሳብ ሰዎች ዱዳ ሆነዋል፡፡ ይልቁንም በባዕድ አገር ላይ የአገር ልጆች ሰላም ለመባባል እንኳ አልታደልንም፡፡
ክርስቲያኖች ግን በፍቅር ሰላምታ መሰጣጠት ይገባቸዋል፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን አንዱ ተልእኮ ስለሆነ ነው ቅዳሴው መሐል እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ የሚባለው፡፡ ምእመናንን የሚያስተዋውቅና በፍቅር የሚያስተባብር ትልቅ ኃይል ስለሆነ ነው፡፡ በቅዳሴአችን የምናደርገው ሰላምታ ትርጉሙ በደንብ ሊብራራና ሊነገር ያስፈልገዋል፡፡ የተቀደሰ አሳሳም ማለት ትከሻ ለትከሻ መሳሳም አይደለም፡፡ የተቀደሰ አሳሳም ከዓለም አሳሳም የተለየ የፍቅር አሳሳም ነው፡፡ ዓለም መሳሳምን ለሽንገላ ታውለዋለች፡፡ ይሁዳም ጌታውን የሸጠው በመሳም ነው፡፡ የተቀደሰ አሳሳም ግን በክርስቶስ ፍቅር የሚደረግ ነው፡፡ በውስጣችን ጥላቻን፣ ቂምን ይዘን ልንሳሳም እንችላለን፡፡ ይህ ግን የበለጠ ፍቅራችንን እየጎዳው ይመጣል፡፡ በሰላምታችንም እግዚአብሔር አይከብርም፡፡ ይቅርታና ፍቅር ለሌሎች ስንል ሳይሆን ለራሳችን ሰላም የምንለማመዳቸው ጸጋዎች ናቸውና ልባችንን ንጹሕ በማድረግ ሰላምታን መስጠት ይገባናል፡፡ እውነተኛ ሰላምታችን ሌሎችን የመማረክ አቅም አለው፡፡ ይልቁንም በዓለም ጥላቻ ደንቁሮ የመጣው በሰላምታችን ፈውስ ያገኛል፡፡ ሰላምታ የትልቅ አገልግሎት መክፈቻ ነውና አክብረን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ “ሰላም ላንተ ይሁን ወንድሜ፣ ሰላም ላንቺ ይሁን እህቴ” ብለን ስንናገር ፍርሃትና ጭንቀት ይበናሉ፡፡ በእምነት ስናደርገው ፈውስን ይሰጣሉ፡፡ የዛሬ ጭንቀት መልሱ ትንሽ ነበር፡፡ በሰላምታ ከሞት የሚያመልጥ፣ የመኖር ተስፋው የሚቀጠል ስንት ሰው አለ፡፡ እውነተኛ ሰላምታን ያድለን!

ያጋሩ