የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ /17/


ስጦታ ተሰጣጡ
“እርስ በርሳቸውም ስጦታ የሚሰጣጡበት ቀን ያደርጉታል” /አስቴር 9፡19/፡፡
የእስራኤል ልጆች በየዓመቱ ከሚያከብሩአቸው በዓላት አንዱ ፉሪም የሚባል ነው፡፡ በሐማ ምክር በአንድ ቀን በመላው ዓለም ላይ እንዲደመሰሱ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የአዋጅን ቃል ሽሮ በሕይወት የቆሙበትን ቀን ፉሪም ብለው ያከብሩታል፡፡ ትርጉሙ ክፉ ዕጣ ወደ መልካም ዕጣ መለወጡን የሚያስታውስ ነው፡፡ ይህ በዓል ከሚከበርበት ሥነ ሥርዓት እንዱ እርስ በርስ ስጦታ መሰጣጠት ነው፡፡ ምንጫቸውን ለማድረቅ የወጣውን ጠላት እግዚአብሔር ያሳፈረበት ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠላትን ለክፋቱ ቢተወዉ ኖሮ ለየራሳቸው መኖር፣ ወንድማቸውንም ማየት ባልቻሉ ነበር፡፡ የመተያየት ዋጋ ያገኙበት ቀን ነውና በስጦታ ያከብሩ ነበር፡፡ እኛም ከእስራኤል ይልቅ ድነናል፡፡ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶብን ሳለ በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ከመቃብር በላይ ዘምረናል፣ በሲኦል ደጃፍ ላይ ተጓደናል፡፡ እርሱ መዳንን ባይፈጽም ኖሮ ቤተ ክርስቲያን ልትኖር እኛም ልንገናኝ አንችልም ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ የደሙ ፍሬ ናት፡፡ ስለዚህ የዳንበትን ምሥጢር ዕለት ዕለት ማሰብና ማክበር ይገባናል፡፡
የእስራኤል ልጆች ስጦታ የሚለዋወጡት አንዱ፣ አንዱን ስላስደሰተው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ማዳን መታሰቢያ ለማድረግ ነው፡፡ ባያድነን ኖሮ ዛሬን፣ ዛሬ ለማለት አንበቃም ነበር በማለት ስጦታ ይሰጣጡ ነበር፡፡ ስጦታ የፍቅርና የእግዚአብሔር ማዳን መግለጫ ነው፡፡ ስጦታ ትንሽም ይሁን ትልቅ ደረጃ የሚወጣለት አይደለም፡፡ ስጦታ መልእክቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ስጦታ ብድር አይደለም፡፡ ስጦታ በጸጋው ለባረከን ጌታ መታሰቢያ እንዲሆን በቸርነት የሚሰጥ ነው፡፡ ስጦታ በድንገት የምናደርገው አሊያም የምንተወው ሳይሆን ስጦታ አገልግሎት ነው፡፡ ስጦታችን የዚያን ሰው የፍቅር ሸለቆ ይሞላል፡፡ ለራሱ ዋጋ እንዲሰጥ ያደርገዋል፡፡ ስጦታ ወደ ሌላ ጎጆ የምንልከው አምባሳደር ነው፡፡ ከፍ ብለን እንድንታሰብ ያደርገናል፡፡ ስጦታችን በራሱ ከፍ ያለ ቦታ ተቀምጦ ይታያል፡፡ ሰዎች እርሱን ባዩ ቁጥር ለካ ወዳጅ አለኝ ብለው ይጽናናሉ፡፡
እርስ በርሳችሁ የፍቅር ስጦታን ተለዋወጡ፡፡ እግዚአብሔር ይባርካችሁ!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ