የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ/21/


ትዕግሥት አድርጉ
“እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” /ቆላ. 3፡13/፡፡
ትዕግሥት መቻል ብቻ አይደለም፡፡ የትዕግሥት ዋነኛ ፍችው ተስፋ ማድረግ ነው፡፡ አንድን ሰው ለመቻል ልባችን ሰፊ የሚሆነው በመለወጡ ተስፋ ስናደርግ ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቀን የመለወጥ ዕድል ነው፡፡ ማንም ሰው እንደ ትላንቱ አይደለም፡፡ ትላንት የፈጸመውን ስህተት እንደ ትላንቱ፣ ዛሬ ልበ ሙሉ ሆኖ አያስበውም፡፡ ላለመሸነፍ ቢለፈልፍም ውስጡ ግን ይከዳዋል፡፡ ውስጡና የእግዚአብሔር ቃል ከድተውትም የሰው ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ከውስጥና ከቃሉ የበለጠ ሰዎች ሊደግፉት አይችሉም፡፡ ከውስጡም በላይ ቃሉ ከደገፈው ይበቃዋል፡፡ ቃሉ በዚህ ዓለም ካሉት ሐቆች በላይ ነው፡፡
ትዕግሥት እያረሩ መሳቅ፣ እያለቁ መኖር፣ እየተጎዱ ዝም ማለት፣ ሰባራ ቀን መጠበቅ አይደለም፡፡ ሕይወት በለውጥ ሕግ ውስጥ ናት፡፡ ትዕግሥትም ይህን ተረድቶ ዝም ማለት፣ እስከ ጊዜው ዘወር ማለት ነው፡፡ ክፉዎች ወይ በንስሐ ይመለሳሉ፣ ወይ በተግሣጽ ይቆማሉ፡፡ ትዕግሥትም ይህን የእግዚአብሔር ዕድል ይጠብቃል፡፡ ትዕግሥት የእግዚአብሔርን ቀን መጠበቅ ነው፡፡ ዘወር ማለት ችግሩ ከሚያስከፍለን ወለድ መዳን ነው፡፡ ችግር አይከብድም፣ ወለዱ ግን ይከብዳል፡፡ ወለዱ የእኛ ጭንቀት፣ የሰዎች ትንታኔ፣ ሥጋዊ የሆኑ መልሶቻችን ናቸው፡፡ ዝምታ አያጸጽትም፡፡ ዘወር ማለትም ብዙ ነገሮችን ያተርፋል፡፡ ጌታ እንኳ ዘወር ይል ነበር፡፡ ምንም እንኳ ለመሞት ቢመጣም ያለ ጊዜው ላለመሞት ይጠነቀቅ ነበር፡፡ ሄሮድስ በሕጻንነቱ ሊገድለው ሲል ወደ ግብጽ መሸሹ፣ አይሁድ በድንጋይ ሊወግሩት ሲሉ መሰወሩ፣ ሰይጣን በፈተና ሰዓት ራስህን ወርውር ሲለው እምቢ ማለቱ ያለ ጊዜው ላለ መሞት ያደረገው ጥንቃቄ ነው፡፡ በጊዜው ግን በአዋጅ ወደ ኢየሩሳሌም ገብቶ ስለ እኛ ሞቷል፡፡ ዘወር ማለት ፍርሃት አይደለም፡፡ ምናልባት ዛሬ መገናኛ ዘዴዎቻችንን ማጥፋትም ዘወር ማለት ነው፡፡ የሚያልፍ ቀን እንዲጎዳን መፍቀድ የለብንም፡፡
ለእርስ በርስ ግንኙነት ትዕግሥት ወሳኝ ነው፡፡ ውስጣችን በሰዎች ላይ ሲቆጣ እስካሁን የምንዋደደው በስሜት እንደ ሆነ አሁን ተግባራዊ ፍቅር እንደ መጣ ማወቅ አለብን፡፡ ተግባራዊ ፍቅር ይቅር ይባባላል፡፡ ፍቅር የሚለካው በስሜት አይደለም፡፡ አብሮን ላለው ሰው የድሮ ስሜታችን የለንም ማለት መለያየት አለብን ማለት አይደለም፡፡ ፍቅር ጠገግ ሲል ስሜቱ ይቀርና ተግባር ይሆናል፡፡ እናት ልጇን ትወዳለች፡፡ ልጇን ስለመውደዷ ግን ተናግራ አሊያም ስሜታዊ መግለጫ አድርጋ አታውቅም፡፡ ፍቅሯ ተግባራዊ ነው፡፡ ፍቅር ተግባራዊ የሚሆነው አንዱ በትዕግሥት ነው፡፡ የማንታገሠው ሰው የለም፡፡ እዚህ ጋ ያለውን ሰው ትቶ፣ እዚያ መሄድ ይቻላል፡፡ እዚያም ቤት ችግር አለ፡፡ በሁሉ ቦታ የሚያኖረን የመኖሪያ ፈቃድ ትዕግሥት ብቻ ነው፡፡
 “ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ” ይላል፡፡ ያለነው ይቅር ተብለን ነው፡፡ ሌላውም ሰው ይቅርታ የሚያስፈልገው ሰው መሆኑን ማመን አለብን፡፡ እኛ የማይበደለውን ጌታ በድለን እርሱ ይቅር ካለን ልንሳሳት የምንችለውን እኛን የበደለውን ይቅር ማለት አለብን፡፡ ይቅርታ እግዚአብሔር እኛን በምሕረቱ እንደ ተቀበለ የምንመሰክርበት አዋጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ትዕግሥትን ያድለን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ