የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (27)

አትበዳደሉ

“ሰዎች ሆይ፣ እናንተ ወንድማማች ናችሁ፤ ስለምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ?” (የሐዋ. 7፡26)።

ይህን ቃል የተናገረው ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። ሙሴ በሕጻንነቱ በወንዝ ዳር ተጥሎ የፈርዖን ልጅ አግኝታ በቤተ መንግሥት አሳደገችው። አልጋ ወራሽ ሆኖም የአስተዳደር ጥበብን ተማረ። ሙሴ ግን እስራኤላዊ መሆኑን ስላወቀ የግብጽ ንጉሥ ከመሆን የእስራኤል ነጻ አውጪ መሆንን ይመኝ ነበር። እስራኤልን ነጻ ማውጣት የፈለገው ግን በጉልበቱ ነበር። አንድ ቀንም አንድ ግብጻዊ እስራኤላዊውን ሲበድለው አየና ግብጻዊውን ገደለው። በማግሥቱ ያ እስራኤላዊ ከወንድሙ ጋር ሲጣላ አይቶት ለምን እርስ በርሳችሁ ትበዳደላላችሁ? ብሎ ምክር ቢያቀርብ ሰሚ አጣ።

ግብጻውያን የእስራኤልን ዘር ለማጥፋት ቀን ከሌሊት እየተጉ ነው። እስራኤልም እርስ በርሳቸው ይበዳደላሉ። በክፉ ቀን እንኳ ሊተዛዘኑ አልቻሉም። “በክረምት እባብና ጓጉንቸር አብሮ ይከርማል” ይባላል። ክረምቱ እስኪያልፍ ትንንሽ ፍጥረቶች እንኳ አይበዳደሉም። ሰው ግን ይህን ብልሃት አጥቶ ይጨካከናል። ልጅ ታሞ በሚያጣጥርበት ቤት ባልና ሚስት ይበዳደላሉ። ከእነርሱ በኋላ የመጣ ልጅ ቀድሜ ልሂድ እያለ ሲጨነቅ ልባቸው መለስ አይልም። በሚጸለይበት ሰዓት ይነታረካሉ። ወገናችን በስደት ምድር ውርደትን እንደ መጎናጸፊያ ተጎናጽፏል። በባሕር የሚሰጥመው፣ በአሸዋ የሚቀበረው እልፍ ነው። በአገር ያለነው ግን አብረን መኖርና መተዛዘን አልቻልንም። ክፉ ቀን ለእኛ ብርቃችን አይደለም። ያለፍነው ግን በመተዛዘን ነው። የአረማውያን ሰይፍ ወንድሞቻችንን ሲቀላ አይተናል፣ እኛ ግን አሁንም እንነቃቀፋለን እንጂ ወደ እግዚአብሔር መመለስን አንሻም። እየሆነ ያለው ልባችንን ሰበር ሊያደርገው አልቻለም። እጅግ ደንዳኖች ነን። የሚመሩን አላዘኑልንም ስንል እኛ ግን ለጎረቤታችን አላዘንም። ያሳለፍነውን ቀን እንኳ ረስተን እንባላለን።

እግዚአብሔር የሚለመነን እርስ በርሳችን ስንተዛዘን ነው። አንዱ ያንዱን ደሞዝ ከልክሎ እግዚአብሔርን በረከት ቢለምን እንዴት ይሆናል? አንዱ የአንዱን ስም በክሎ በሰላም መተኛት ቢሻ የት ይገኛል? አንዱ ያንዱን ልፋት ወርሶ ጤና ከየት ያገኛል? እርስ በርሳችን ካልተዛዘንን የሩቁ ባያዝን አይደንቅም። መተዛዘን ያለው ፍቅር ይስጠን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ