ዕዳ አይኑርባችሁ
“እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ” (ሮሜ. 13፡8)
ዕዳ በትከሻ ላይ ያለ ሸክም ሳይሆን በኅሊና ላይ ያለ ሸክም ነው። ዕዳ አያስተኛም። ጣር ላይ ያሉ ሰዎች የእገሌ ዕዳ አለብኝ ይላሉ፣ ዕዳ ሰላማዊ ሞትን ይከለክላል። ዕዳውን ያልከፈለ ሞቶ እንኳ ይከሰሳል፣ ቤተሰቡ ይወቀሳል። ሐዋርያው ዕዳ ያለው የገንዘብን ሳይሆን የፍቅርን ዕዳ ነው። መወደድ ቢያስደስትም ቢያስመካም፣ መወደድ ግን ብቻውን ዕዳ ነው። ሌሎች እየወደዱን መውደድ አለመቻል ያስጨንቃል፣ ራስን እንድንጠይቅ ያደርጋል። ዕዳ ነውና አያስተኛም። ምን ያህል ክፉ ሰው ነኝ እንድንል ያደርጋል። ፍቅር ከሚቀበሉት ይልቅ ሲሰጡት ያስደስታል። ሰው ለሚሆነው አይሆንም። ወዳጁንም ቸለል ይላል። ሰው የሚከተለው የሚወደውን ሳይሆን የጠላው የመሰለውን ነው። እርሱም እልህ ስለሚይዘው ነው። ፍቅር መተላለፍ ካለው ሕመም እንጂ ደስታ አይሆንም። የብዙ ሰው ፍቅር ፈረቃ ነው፣ የአንዱ ሲጨርስ የአንዱ ይጀምራል። የፍቅር ደስታ ያለው በመዋደድ ውስጥ ነው። የሚወዱን ሰዎችም ፍቅራቸውን ካላወቅንላቸው ታማሚ ናቸው። ጌታችን የሕማም ሰው የተባለው የሚወዳቸው ፍቅሩን ስላላወቁለት ነው። የእርሱ ሕመም ዓርብ ዕለት ብቻ አልነበረም። እርሱ ዘመኑን በሙሉ የሕማም ሰው ነበር። እኛም የፍቅሩ ዕዳ አለብን። ፍቅር ካለ ሕግጋት ቀላል ናቸው። ፍቅር የመታዘዝ ጉልበት ነው። የፍቅር ዕዳ እንዳይኖርብን፣ የሚወዱንን እንድንለይ እግዚአብሔር ይርዳን!
እርስ በርሳችሁ
ተቀባበሉ “ስለዚህ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እንደ ተቀበላችሁ እንዲሁ እርስ በርሳችሁ ተቀባበሉ” (ሮሜ. 15፡7) መቀበል የአንድ ወገን ድርሻ ነው። መቀባበል ግን የሁለት ወገን ግዴታ ነው። እንግዶችን መቀበል፣ ለድሆች ቸርነትን ማድረግ መቀበል ወይም ማስተናገድ ነው። ክርስቶስ የተቀበለን የእኛን መቀበል ሳይጠብቅ ነው። እርሱ እኛን ከነማንነታችን እንደተቀበለን እኛም ሌሎችን መቀበል አለብን። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ውስጣዊ ችግሮችን ከሚያስነሡ ነገሮች አንዱ አለመቀባበል ነው። ሁሉም ራሱን ይቀበላል፣ ወንድሙን ግን መቀበል ያቅተዋል። ለራሱ ይቅርታን ይሰጣል፣ ለወንድሙ ግን ፍርድን ይሻል። ለራሱ ቀስ ብሎ ማደግን ይመድባል፣ በሌሎች ማዝገም ግን ተስፋ ይቆርጣል። የሮሜ ቤተ ክርስቲያን ባለመቀባበል ምክንያት ታውካ እንደነበር ምዕራፍ 14 ይነግረናል። አለመቀባበል አንዱን ጌታ የሚያመልኩ ሁለት ጎራዎችን ወለደ። የሚመለከው አንዱ ጌታ ከሆነ ማኅበሩም አንድ ሊሆን ይገባው ነበር። ጠባቸውን ደግሞ መንፈሳዊ ሊያደርጉት ፈለጉ። አንዱ እኔ የገባኝ ነኝ ብሎ ፍቅርን ጣለ። ሌላው እኔ ለእግዚአብሔር እቀናለሁ ብሎ ፈራጅና ሌላውን ኮናኝ ሆነ። ራሱን የእግዚአብሔር የቅርብ ረዳት፣ መጋረጃ ገላጭ አድርጎ ቆጠረ። ስለዚህ ባለመቀባበል በቤተ ክርስቲያን ንቀትና ፍርድ በዛ። በጌታ የከበረው ምእመን ሌላውን ናቂ ከሆነ፣ በምሕረት የሚኖረው ሰው በሌላው ፈራጅ ከሆነ እግዚአብሔር ያዝናል! አውቃለሁ የሚለው እውቀቱን በፍቅር መግለጥ አለበት። ክርስቶስን እንጂ ነጻነቱን እንዳያመልክ መጠንቀቅ አለበት። እውነት የገባው ስል አእምሮ ስላለው ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ ስላገዘው ነው። ዛሬ የሚያከብረውን እውነት ትላንት ይቃወመው እንደነበር ማሰብ አለበት። እግዚአብሔር እርሱን አስገብቶ የምሕረት በሩን እንዳልዘጋ ማሰብ ያስፈልገዋል። እግዚአብሔር በደካማው ወገን ላይም ዓላማ እንዳለው፣ እርሱ የሁሉ አባት መሆኑን ማሰብ አለበት። ፈራጁና ሌላውን ጥላሸት ቀቢውም እንደ ራሱ ትእዛዝ አድርጎ መናደድ አይገባውም፣ ወገኔን ጥዬ እንዴት ብቻዬን እገባለሁ በሚል ፍቅር ሌላውን መሳብ አለበት። ፍቅር የሌለው ክርስትና በድን እንደሆነ ማሰብ አለበት። ያለፍቅር የሚደረግ አገልግሎት ሁሉ እግዚአብሔርን አያከብርም። ክርስቶስ መፍረድ ቢሻ ኖሮ በዙፋኑ ይበይን ነበር፣ በረት የተወለደው ማዳን ስለሚሻ ነው። እርስ በርስ መቀባበል ይገባል። አንዱ የአንዱን አሳብ በቅንነት ተረድቶ ለሁላችንም መለወጥ የመንፈስ ቅዱስን ክንድ መፈለግ ይገባናል። እባክህ ጌታ መቀባበል ስጠን። ለራሳችንና ለምንወዳቸው መንግሥተ ሰማያትን ተካፍለናል። ለምንጠላቸውና አይገባቸውም ለምንላቸው ገሀነመ እሳትን መድበናል። በቅጡ ሰው ሳንሆን የአምላክን ዙፋን ነጥቀናል። ጌታ ሆይ መቀባበልን ስጠን!