የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ (4ኛ)

 ተስማሙ 
“እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ” (ሮሜ.12፡16)
 የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በገንዘብ ተጣልተው ጉዳዩ እያየለ መጥቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋ ደረሰ። እርሳቸውም መሪዎቹን፦ “እኛ ወደ እናንተ ለመምጣት ስናስብ እናንተ ወደ እኛ መጣችሁን?” እንዳሉ ይነገራል። ሰላም ያጣው ዓለም ወደ እኛ የሚመጣው እኛ ሰላም ሲኖረን ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን የዘላለም ጉዳይን እየዳኘች ለሚያልፍ ጉዳይ ፍርድ ቤት መንከራተቷ እግዚአብሔር እንዲያዝንብን አድርጓል። የዚህ ችግሩ ያለንን የከበረ መፍትሔ አለመገንዘብ ነው። ዳግመኛም የእኛን ጭቅጭቅ የዳኙ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን አይመጡም። መልካሙን ጌታ በእኛ መጠን ያዩታል። ሐዋርያው፦ “እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ” ያለው ሰላማችን ቅድስና ስለሆነ፣ ለአምልኮም አስፈላጊ ስለሆነ ነው። ቅድስና ማለት መልካም አኗኗር ነው። ቅድስና ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር በሰላም መኖር ነው። በብዙ ችግር ውስጥ ሆኖ መጸለይ ይቻላል። በትንሽ ቅሬታ ውስጥ ሆኖ መጸለይ ግን አይቻልም። “ቂም ይዞ ጸሎት ሳል ይዞ ስርቆት አይሆንም” ሰላም ማጣት ቅድስናን፣ ጸሎትን፣ ምስክርነትን ይጎዳል። በአንድ አሳብ ለመስማማት የአካልነት ስሜት ሊሰማን ያስፈልጋል። በአካል ዓለም ደስታም ሀዘንም የጋራ ነው። በአሳብ የሚለያየን የእኔነት ስሜት ነው። ለክፉ፣ ክፉ ምላሽ አለመስጠት ይህም በአንድ አሳብ ለመስማማት ወሳኝ ነው። ጦርነት ማለት የአንድ ወገን ተኩስ ሳይሆን ምላሹ ነው። የትዕቢት አሳብን ማራቅ በአንድ አሳብ ለመስማማት ይረዳል። “እርሱ ማን ነው?” ማለት ትዕቢትን ሲወልድ “እኔ ማን ነኝ?” ማለት ግን ትሕትናን ይወልዳል። ከተገለጠ ትዕቢት ይልቅ ልብ ላይ የተቀመጠ ትዕቢት በአንድ አሳብ ለመስማማት እንቅፋት ይሆናል። በአንድ አሳብ ለመስማማት እግዚአብሔር ላለው ነገር ቅድሚያ መስጠት ይገባል። እግዚአብሔር ማዕከል ያልሆነበት ማንኛውም ንግግር አያግባባም። ዛሬ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ልብስ በአደባባይ ገልጠን በሚያምንና በማያምን ፊት ስንሰዳደብ ክርስቶስን እንደገና እርቃኑን እየሰቀልነው መሆኑን አላስተዋልንም። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው በስድብ አይከብርም። በስብከታችን የሳብነውን ሕዝብ በእርስ በርስ ሽኩቻችን እንዳንበትነው መጠንቀቅ ይስፈልጋል። አገልግሎቱ አላነሰም፣ ፍቅር የሌለው ጸሎት ግን ግዳጅን አይፈጽምም፣ ምሕረትን አያወርድም። በአንድ አሳብ ለመስማማት እግዚአብሔር ይርዳን! 


እርስ በርሳችሁ (8) 
ባሪያዎች ሁኑ 
“ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ” (ገላ. 5፡13) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታ ሆኖ ሳለ በዚህ ዓለም ላይ ግን የኖረው ከባሪያ ያነሰ ሆኖ ነው። በእስራኤል ልማድ እግር ማጠብ የባሪያ ተግባር ነው። ባሪያውም እግር ከማጠቡ በፊት እራቱን ይበላል። እራቱን ሳይበላ እግር ቢያጥብ ባጠበ እጁ ለመብላት ተጸይፎ ጦሙን ማደር ይመርጥ ነበር። ጌታችን ግን የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበው ከማዕድ ላይ ተነሥቶ ነው። ካጠበ በኋላም ወደ ማዕዱ ተመልሷል(ዮሐ.13)። የተሸጠውም በባሪያ ዋጋ ነው። በዚያ ዘመን የአንድ መለስተኛ ባሪያ መሸጫ ሰላሣ ብር ነበር። ጌታችንም ጌታ ሳለ በባሪያ ዋጋ ተሽጧል። ለዚህ ነው ሐዋርያው፦ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ…” የሚለው (ፊልጵ.2፡6-8) እግር በማጠብ ትሑት እንሁን ብንል እንኳ እርሱንም ጌታ ይዞብናል። የትልቆቹ ትልቅ እንዲህ ዝቅ ካለ እኛማ እንዴት ዝቅ ማለት ይጠበቅብን ይሆን? ፍቅር ሁልጊዜም በዝቅታ እንጂ በኩራት አይገለጥም። ፍቅር የሚረካው በማገልገል እንጂ በመገልገል አይደለም። አንዳችን ለአንዳችን ባሪያ መሆን የሚገባን በፍቅር ነው። ፍቅር የሌለበት ዝቅታ ሁሉ ሐሰተኛ ነው። ያለ ፍቅር የሚደረግ ማንኛውም አገልግሎት በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የለውም። ደንቡን ለማድረስ ብለን የምናከናውነው መንፈሳዊ ተግባር የለም። የተግባራችን ቅመሙ ፍቅር ነው። እርስ በርሳችን ቁመት የምንለካካ ከሆነ ከፍቅር ጎድለናል ማለት ነው። ፍቅር ለሚወደው ባሪያ ይሆናል። “ፍቅር ኃያል ወልድን ከመንበሩ ሳበው፣ እስከ ሞትም አደረሰው” ተብሏል። ፍቅር ከመንበር በረትን፣ ከመግደል መሞትን መርጧል። የሞተውም ጠላቶቹ ለሆንን ለእኛ ነው። እግዚአብሔር ፍቅር ነው። እግዚአብሔር ተግባራዊ ፍቅር ነው። በፍቅር የሚገለጥ ማንነት ይስጠን! ዘመናችሁ ይባረክ! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ