በአጉል ፍቅር አትዋደዱ
“እርስ በርሳቸውም፦ ኑ፥ ጡብ እንሥራ፥ በእሳትም እንተኩሰው ተባባሉ” (ዘፍ. 11፡3)።
በምድር ላይ አንድ ቋንቋ አንድ ንግግር ነበረ። የሰው ልጆችም ሰማይ ጠቀስ ግንብ ለመሥራት ፈለጉ። የግንቡ ዓላማ የመጀመሪያው ስማቸውን ለማስጠራት ነው። ይህ ትዕቢት የወለደው ነው። ሥራችን ከተናገረ መልካም ነው። ያሁኑን ትውልድ እየበደልን ግን ለነገ ታሪክ ላስቀምጥ ማለት ጭካኔ ነው። የግንቡ ሁለተኛው ዓላማ በዙሪያቸው ሰማይ ጠቀስ ግንብ ገንብተው ራሳቸው ላይ ለመዝጋት ነው። በጊዜያዊ መግባባታቸው ተደስተው ያለመለያየት ወሰኑ። አሳቡ መልካም ይመስላል። ነገር ግን ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት ያለውን የእግዚአብሔር አሳብ ይቃረናል። ዓለምን ፈጥሮላቸው ሳለ መንደርን ዓለም አድርገው መቀመጥ ፈለጉ።
ትዕቢት የእግዚአብሔርን ዙፋን መቃወም ነው። ፍቅርም እውነተኛ የሚሆነው የእግዚአብሔር አሳብ ሲከብርበት ብቻ ነው። እግዚአብሔር የማይከብርበት ፍቅር ፍጻሜው አያምርም። እርስ በርስ መዋደድ የሚገባን ሕግን እያከበርን እንጂ ሕግን እያፈረስን አይደለም። ያንን ሰማይ ጠቀስ ግንብ ቢሠሩና ራሳቸው ላይ ቢዘጉ ኖሮ እየበዙ በመጡ ቁጥር ተጨንቀው ይጎዱ ነበር።
እግዚአብሔርም ይህን ጅምር አየ አልተደሰተም። ስለዚህ ቋንቋቸውን ደባለቀውና በምድር ላይ በተናቸው። ከዚህ ተግባር በኋላ አብርሃምን ሲጠራ እናያለን። ይህ ተግባሩ ፍርድም ምሕረትም ነው። የዚያም ስፍራ ስም ባቢሎን ተባለ። ድብልቅልቅ ማለት ነው። የሰው ጠብ ብቻ ሳይሆን በፍቅሩም ውስጥ እንከን አለበት። የሰው ጥበብ በራስ ላይ ከማጠር አያልፍም። ዛሬ ዓለም እየፈራ ያለው በገዛ እጁ እንዳይጠፋ ነው። የኒውክለር ስጋት ዓለም በገዛ እጁ ላለመጥፋት የሚያሰማው ጥሪ ነው። ከንቱ ፍቅር እግዚአብሔር የማይከብርበት ወዳጅነት አለ። ከአንዳንድ ኅብረት መለየት በረከት ነው። እግዚአብሔር በጅምር ስለሚያስቆመን ግንቦች ምስጋና ማቅረብ አለብን። ቢያልቁ ዘላለማዊ እስር ቤት ይሆኑብን ነበር። እግዚአብሔር ሲባርክ እየሰጠ ብቻ ሳይሆን እየነሣም ነው። ዓለም ሰፊ ነው። በራሳችን ላይ ሰማይ ጠቀስ ግንብ ገንብተን ልንጨነቅ አይገባም። እዚህ ባይሳካ እዚያ ይሳካል። እዚህ ጋ ብንጠላ እዚያ እንወደዳለን። ዮሴፍ በወንድሞቹ በነጻ ሲሸጥ በግብጾች ደግሞ በዋጋ ተገዝቷል። መላው ዓለም ቢወደን የምንኖረው ከሁለት ሰው ጋር ነው። መላው ዓለም ቢጠላንም የምንኖረው ከሁለት ሰው ጋር ነው። የምንጨነቀው በከንቱ ነው።
በከንቱ ፍቅር ውስጥ ስስት፣ መጣላት፣ መቀያየም የለም። ቢጣሉም አንድ ቢራ ከወረደ ይታረቃሉ። እኛ ነን እግዜር ቢወርድም አንታረቅም የምንል። ይህ ወዳጅነት ተባብሮ መሞት እንጂ ተባብሮ መኖር ያለበት አይደለም። መተዛዘን፣ ምሥጢር መጠበቅ ያለ ቢመስልም ዕድሜ የሚያሳጥር ኅብረት ነው። ወዳጅነቱ ለእውነት ዋጋ የሚከፍል ሳይሆን እውነትን የሠዋ ነው። በዚህ ኅብረት ውስጥ ሰዎች በራሳቸውና በትውልዳቸው ላይ ግንብ ይገነባሉ። ሰው ያሰረው ለመውጣት በር ይፈልጋል። ራሱን ያሰረ ግን በሩን አይፈልግም። በኅብረት የሆኑ ስህተቶች አንዱ ሲወስን አንዱ እያስፈረሰ ለማቆም ይቸገራሉ። እግዚአብሔር የሚያወጣቸው ቋንቋቸውን በመደባለቅ ነው።
ፍቅር በሚመስሉ አድማዎች ላይ እግዚአብሔር ቋንቋን ሲደባልቅ ይድናሉ። ሲበተኑ የተሻለ ወዳጅ ያገኛሉ። የሚሠሩትን ስህተት ይገነዘባሉ። መርዝ የቀመሱ ሰዎች ከተስማማቸው ይሞታሉ፣ ከተጣላቸው ይድናሉ። ክፉ ኅብረትም ሲደባለቅ ለመዳን ነው። ፍቅራችን መሠረቱ ፍቅር ብቻ ነው? የአንዳንድ ፍቅር መሠረት የጋራ ጠላት መኖሩ ነው። ሌላ ጊዜም ሱስ ነው። እግዚአብሔር ክፉ ኅብረትን በመበተን ምሕረቱን ይገልጣል።
እግዚአብሔር የማይከብርበት ፍቅር ፍጻሜው መደባለቅ ነው። ኅብረታችንን እንድንቀድስ አምላክ ያግዘን!