የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(33)

በአድማ አትያዙ

“እርስ በርሳቸውም፦ ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ” (ዘኁ. 14፡4)።

የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ በምድረ በዳ ላይ ሳሉ አሥራ ሁለት ሰላዮችን ወደ ከነዓን ላኩ። የስለላው ዓላማ የምድሪቱን መልካምነት አይተው ለሕዝቡ እንዲናገሩ፣ የሕዝቡም ልብ ለጉዞ እንዲበረታ ነው። አሥራ ሁለቱ ሰላዮች ግን ሲመለሱ ሁሉም ምድሪቱ መልካም ናት አሉ። አሥሩ ግን በውስጧ ኃያላን ሰዎች አሉና አንችላቸውም ብለው ጠላቶቻቸውን አተልቀው ተናገሩ። ኢያሱና ካሌብ ግን እግዚአብሔርን አተልቀው ጠላቶቻቸውን አሳንሰው በእምነት ተናገሩ። ሕዝቡ ግን የአሥሩን ቃል ሰምቶ በፍርሃት ተናጠ። አለቀሰ። በሙሴና በአሮን ላይ አጉረመረመ። በዚህ ጊዜ፦ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ተባባሉ።

በርግጥም ወደ ኋላ የሚል ሕዝብ መሪ ሳይሆን አለቃ የሚሾም ነው። መሪ ያስከትላል፣ አለቃ ግን ይነዳል። መሪ ሠርቶ ያሳያል፣ አለቃ ግን ያዛል። መሪ መሥዋዕት ይሆናል፣ አለቃ ግን ሙቱልኝ ይላል። ወደኋላ ቢመለሱ ቀይ ባሕር አይከፈልም። እግዚአብሔር ተአምር የሚያደርገው ወደፊት ለሚሄድ እንጂ ወደ ኋላ ለሚል ሕዝብ አይደለም። ከግብፅ የወጡት የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰምተው ነው። አሁን ግን በአገልጋዮቻቸው ላይ አንጎራጎሩ። ላለማመናቸው ተጠያቂ አደረጓቸው። በድንቅና በተአምራት ያወጣቸው እግዚአብሔር ነው። አሁን ግን ከጠላቶቻቸው አሳነሱት።

የእግዚአብሔር ቤት ያገናኛል። የትም የማይገናኙ ሰዎች በቤቱ ይገናኛሉ። እርስ በርሳቸው የእምነትን ነገር መነጋገር ካልቻሉ ግን አለቃ ሾመን ወደ ኋላ እንመለስ ይላሉ። አንዳንድ ሆነው መጥተው በቡድን ይወጣሉ። መሪ አያስፈልገንም ብለው አለቃ ይሾማሉ። የአድማውም ድምፅ መንፈሳዊ ይመስላል። ብዙ አድማዎች የሚጠነሰሱት የጸሎት ፕሮግራም ላይ ነው። “አባቶችን የሚሠሩትን አሳውቅልን፣ አገልጋዮችን ከመሸቃቀጥ አውጣልን” ተብሎ ሲጸለይ አሜን የሚለው የዋህ ለካ አባቶች የሚሠሩትን አያውቁም፣ አገልጋዮችም እያታለሉን ነው ብሎ ማሰብ ይጀምራል። ምንም በሌለበት አይዟችሁ መቻል ነው በሚል ቃላት ይመለመላሉ። በዚህ ጊዜ አለቃ ሾመን እንመለስ ይመጣል። አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ ያሉት እስራኤል ግብፅም አልተመለሱም፣ ከነዓንም አልገቡም። ወደ ኋላ የሚሉ ከሁሉም ሳይሆኑ ይቀራሉ። አሳቾችም ያስደነበሩትን ሕዝብ ሜዳ ላይ ጥለው ይሰወራሉ።

እኛም ያለነው በምድረ በዳው ዓለም ላይ ነው። ምድረ በዳ የሚታይ፣ የሚሰማ እንደሌለው ዓለሙም በጎ የማይሰማበት፣ መልካም የማይታይበት ሆኗል። እግዚአብሔር ግን ለምድረ በዳው ድምፅ፣ ለጥማቱም እርካታ አለው። ፈተናና ትግሎች አስፈርተዋችሁ ከዚህ ሁሉ ወደ መጣሁበት ዓለም ብመለስስ አትበሉ። ዓለም የምታመጣው ሞት ዘላለማዊ ነው። የዛሬ መከራና እርካሽ መሆን ግን ኃላፊ ነው። የእስራኤል ልጆች የሚበልጠውን አይተው በሚያንሰው ተጠራጠሩ። እኛም ብዙ አይተናል። ሞትን በነበር ለመናገር በቅተናል። በሚያንስ ነገር ልንዝል አይገባንም። የጠራንን እያየን ጉዞአችንን ወደፊት ልናደርግ ይገባናል። ኅብረት ማለት ወደፊት መጓዝ ነው። የማፈግፈግ ምክር አድማ ነው። ከዚህ መለየት ይገባናል። እግዚአብሔር እስከ መጨረሻው ያጽናን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ