የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(37)

አታንጎራጉሩ
“እርስ በርሳችሁ አታንጎራጉሩ” (ዮሐ. 6፡43)

ይህን ቃል የተናገረው የምስጋናው ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ብሎ ሲናገር አይሁድ ይህ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው የዮሴፍ ልጅ አይደለም ወይ? ብለው አንጎራጎሩ። በዚህ ጊዜ ጌታችን፦ “እርስ በርሳችሁ አታንጎራጉሩ” አላቸው። ጌታችን ራሱን የገለጠበት ቃላት ለእኛ እንዲገባን እንጂ የሆነው ልክ አይደለም። እርሱ ከቃላት አስረጂነት በላይ በክብር የሚኖር ነው። ራሱን መንፈሳዊና ዘላለማዊ እንጀራ አድርጎ ጠራ። እንጀራ ዕለታዊ ፍላጎት እንደሆነ ጌታም የቀኑ መሪ ነው። እንጀራ ቅርጹ ለማንም ያላደላ ክብ እንደሆነ ጌታም ሁሉን ይወዳል። እንጀራ በኅብረት የሚቆረስ ማዕድ እንደሆነ ጌታም አንድ ያደርጋል። ይህ አስደሳች ቃል ለአይሁድ መርዶ ሆነባቸው። በእርሱ ላይ የተሳሳተና ያልተሟላ እውቀታቸው አሰናከላቸው። የዮሴፍ ልጅ ነው ማለታቸው ስህተት ነው። የድንግል ልጅ ብቻ ነው ማለታቸው ደግሞ ያልተሟላ እውቀት ነው። እርሱ ሰማያዊ ልደት ያለው የአብ ልጅም ነው።

ማንጎራጎር ድምፅን ዝቅ አድርጎ ማዘን ነው። ማንጎራጎርን ለመተው አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ዜማ አለው። ማንም ሰው ድምፁን ዝቅ አድርጎ ሲያዜም ድምፁ ጥሩ ይመስለዋል። ስለዚህ የሚያንጎራጉር የገዛ ድምፁን እየሰማ የሚያለቅስ ነው። ማንጎራጎር ጊዜአዊ ስሜት አይደለም፣ ሕይወት ነው። እናቶቻችን የማይጨውን ዘመቻ፣ የትሣሡን ግርግር እያነሡ በየጠዋቱ ካላለቀሱ ቀለል አይላቸውም። ሰይጣን የሀዘን ማቅ ያስታጥቃል።

ማንጎራጎር እውነትን እንዲሁ መቀበል አለመቻል አንድ ነገር ካልተናገርሁ የሚል ሱሰኛነት ነው። ሊቅነት ተቺነት የሚመስላቸው በእያንዳንዱ ነገር ላይ አሳብ ካልሰጡ ያልኖሩ የሚመስላቸው ምስኪን ዜመኞች አሉ። ዜማ እንደማይቋረጥ እንዲሁ ያለማቋረጥ የሚያለቅሱ፣ ስለ ብልሽት፣ ስለጥፋት የሚያወሩ ቀኑን አጨልመው የሚያሳዩ አሉ። ሌላውን እያሸበሩ እነርሱ ይተኛሉ። ጊዜ ሲገልጣቸው ግን ብቸኛ ይሆናሉ። ዘመነኛ ርእስ እየፈለጉ ማስጮህ የትም አያደርስም። ዘላለማዊው ርእስ ክርስቶስ የት ሄዶ!?

“ያልተማረ ቄስ ሁሉን ያረክስ፣ የተማረ ቄስ ሁሉን ይቀድስ” እንዲሉ ሁሉን ርኩስ፣ ሁሉን መንፈስ የሚሉ አሉ። ዳር ቆመው ስብከትን፣ ዝማሬን እንደ ሜልኮል የሚተቹ ፍቅርን የመከኑ አሉ። ራሳቸውን እንደ እግዜር ፖሊስ ቆጥረው ሰው በአምልኮ እየጠገበ እነርሱ የሚራቡ ብዙ ናቸው። እኔ ይህ ነገር አይመቸኝም፣ እኔ፣ እኔ የሚሉ እኔነታቸው ግን ወድቆባቸው፣ እኔነታቸውን ጣኦት ያደረጉ የተሰበረ ዳጎን የሚያመልኩ አያሌ ናቸው።

ማንጎራጎር የእርስ በርስ ግንኙነትን ይጎዳል። ማንም ሰው ምንም ከማይጥመው ሰው ጋር መኖር አይፈልግም። ደግሞ  ዛሬ ምን ይል ይሆን? ከሚባል ሰው ጋር ለማለት እንጂ ለመሥራት ካልታደለ ጋር መኖር ይከብደዋል። በአሽሟጣጮች ፊት እግር እንኳ ይደናቀፋል። መተቸት ሕይወታቸው ከሆነ ስመኞች ጋር መቀመጥ ብዙ ሰው ይከብደዋል። ማንጎራጎር ጠባያችን ከሆነ ቶሎ መጣል አለብን። ከዚህ ተመጻዳቂነት፣ እውነትን ላርም ከሚል አቅምን አለማወቅ መዳን አለብን። በሁለት ዓይን እየታየ ከሰው ጋር አይኖርም፣ አንዱ ሲያይ አንዱ መጨፈን አለበት። በሁለት ጆሮ እየተሰማም ከማንም ጋር መኖር አይቻልም። አንዱ ሲሰማ አንዱ ማፍሰስ አለበት። እግዚአብሔር የተደሰተ ልብ ይስጠን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ