የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እርስ በርሳችሁ(9)

በፍቅር ታገሡ

” በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ. 4፡2-3)።

ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ትልቁ አቅም ትዕግሥት ነው። ትዕግሥት አለመጣላት ብቻ አይደለም። በልብ መተከዝን ማራቅም ነው። የማይጣሉ ውስጣቸው ግን የተሰበረ ሰዎች አሉ። ይህም ትዕግሥት ማጣት ነው። ትዕግሥት ክፉ አለመናገር ብቻ አይደለም፣ እየታመሙ በጎ መናገርን ማራቅም ነው። እሺ፣ ይሁን እያሉ የሚናገሩ ነገር ግን ውስጣቸው የሚያቃስትባቸው ሰዎች አሉ። ይህም ትዕግሥት ማጣት ነው። እውነተኛ ትዕግሥት ሥልጣን የእግዚአብሔር ነው ብሎ ተማምኖ መኖር፣ ይህም ያልፋል ብሎ በአሳላፊው ጌታ መደላደል፣ ሰዎች ነገ ይለወጣሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ፣ ለሁሉም ነገር እኔ መመለስ አለብኝ ብሎ አለማሰብ ነው።

ሰዎች በተለያየ መንገድ ሊታገሡ ይችላሉ። አንድ ጊዜ የጀመርኩትን ልጨርስ ብለው የሚታገሡ፣ “ቀን እስኪያልፍ የአባቴ ገበሬ ያግባኝ” በሚል ብሂል የሚያደፍጡ፣ ምን ይመጣል እንደ አመጣጡ እንመልሰዋለን ብለው የሚታገሡ፣ …ሊኖሩ ይችላሉ። ሐዋርያው ግን በፍቅር ታገሡ ይላል። ከፍቅር ውጭ ያለው ትዕግሥት አንድ ቀን ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ የሚተው፣ የሚፈርስ ዓላማን ተሸክሞ የሚጓዝ፣ ዕድሜ ማራዘሚያ ነው። ከፍቅር ውጭ ያለው ትዕግሥት ዛሬ የሚረገጥ ቀን ሲለወጥ የሚረግጥ ነው። ይህ ትዕግሥት ቆይ እያለ ባልተቀበልነው ነገር ገና በምኞት እንድንበድል የሚያደርግ ነው። ከፍቅር ውጭ ያለው ትዕግሥት በትረ መስቀል እንደ ያዙ ጎበዞች በሰላም የመጣውን እባርካለሁ፣ በክፉ የመጣውን እወጋለሁ የሚያሰኝ ነው። ይህ ጊዜያዊ ጨዋነት እንጂ መንፈሳዊነት አይደለም። በፍቅር የሆነ ትዕግሥት ግን ተስፋ የሚያደርግ ነው።
የዛሬ ኑሮ በልብ ፉከራ የበዛበት ቆይ ብቻ የሚባልበት የፉከራ ሆኗል። ሁሉም ሰው ማስፈራራት ይፈልጋል። ማስፈራራት ከበዛ ፈሪ በዝቷል ማለት ነው። መረጃ አለኝ የሚል ከበዛም ወንጀል አለበት ማለት ነው። ተግባራችን የልባችን አደባባይ ወይም ማሳያ ነው። አዎ በፍቅር ለመታገሥ ትሕትና መልካም ነው። ትሕትና ክብሬ ጌታዬ ነው ብሎ መኖር፣ ለፍቅር እንጂ ለመብት አለመኖር ነው። የዋህነትም አስፈላጊ ነው። የዋህነት አውቆ ለሌሎች መቆረስ፣ እንደ ሞኝ እየተቆጠሩም ደግ መሆን ነው። ከትዕግሥት የሚያፈናቅለን ሰዎች ገደባቸውን ማለፋቸው፣ ደግነታችንን እንደ ሞኝነት መቁጠራቸው ነው። የሚያስፈልጋቸውን ሞፈር ከደጃችን እየቆረጡ ” ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል” ብለው ሲተርቱብንም በመልካምነት መቀጠል እርሱ በፍቅር መታገሥ ነው።

በኑሮአችንና በሕይወታችን የፍቅር ትዕግሥትን ያድለን! እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ! እግዚአብሔር ይርዳን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ