የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እስከ መጨረሻ መውደድ

 “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው ።” ዮሐ. 13፡1
“በተቀየረብህ ሰው ምክንያት የኀዘን ኑሮ አትግፋ ፣ ይህ ሰው ማስመሰሉ ደክሞት ወደ እውነተኛ ማንነቱ ተመልሷልና” የሚል አንድ አባባል ሰምቻለሁ ። የከዱን የሚመስሉን ሰዎች አብረውን የነበረ ቀን ነው የከዱን ፣ አሁን ግን ጊዜያችሁን አላባክንም ብለው ሄደዋልና ታማኝ የሆኑት ዛሬ ነው ። ብዙ ዘመን ከእኛ ጋር የኖሩት በጭምብል ተሸሽገው ነው ፣ አሁን ግን መሸፈኛውን አውልቀው ገስግሰዋል ። እስከ ዛሬ ሕመም አልባ በሽታ ነበሩ ፣ ዛሬ የሚጠዘጥዝ በሽታ ሆነዋል ። እስከ ዛሬ ሌሎችን እያባረሩ እነርሱ ብቻ አጠገባችን ነበሩ ፣ አሁን ግን ራሳቸውንና መሰላቸውን ይዘው ሄደዋል ። እስከ ዛሬ ድረስ አብረውን የሌሉትን አሉ እያልን እንታለል ነበር ፣ አሁን ሄደዋልና የሌለንን ነገር በትክክል አውቀናል ። አስመሳዮች ከአጠገባችን የሄዱ ቀን ዳግም እንደ ተወለደ ሰው ዓይናችን ተገልጦአል ። እያየን የማናይ ነበርና አሁን ግን አጥርተን አይተናል ። በሌለን ሺህ ከመዝለል ፣ በሌለን ምንም መጸለይ ይሻላል ። አሉ ብለን ከአምልኮ ያራቁን ሲሄዱ የለኝም ብለን እንድንጸልይ ያደርጉናል ። አስመሳዮች ከአጠገባችን የሄዱ ቀን ጠባያቸው ተገለጠ እንጂ ያን ቀን ማስመሰል ጀመሩ ማለት አይደለም ። አጠገባችን ሳሉ አናያቸውም ፣ በሩቅ ያሉ ግን አልሰሜን ግባ በለው እያሉ ለእኛ ያዝኑልን ነበር ፤ ሲርቁን ግን ትክክለኛ ማንነታቸውን አየን ። ሰዎች የከዱን ቀን መዘመር ፣ አስመሳዮች የሄዱ ቀን መሸለም ይገባናል ። ለሐሰተኛ ማንነታቸው ስንመጸውት ኑረን ለእውነተኛ ማንነታቸው መናደድ አይገባንም ። የሰጡን ማደንዘዣ እስከ ነገ እንደሚበቃ እያወቁ ዛሬ በመሄዳቸው ጊዜያችን አትርፈዋል ፣ የዓይናችንን ብዥታ አሳውቀውናልና ልናመሰግናቸው ይገባል ። አንድ ሰው፡- “ብዙዎች መጥተው ብዙዎች ሄደዋል ፣ አንድ ግን ቀርቷል” ብሏል ። እናንተስ  የቀረላችሁ አንድ ማን ይሆን ?

ሰዎች በሰላም መንገዳቸውን እየሄዱ ተባራሪ ጥይት ይገድላቸዋል ። የተተኮሰበት ድኖ እነርሱ ያለ ዓላማቸው ይሞታሉ ። አንዳንዶች የሚደባደቡ ሰዎችን ሲያዩ በስሜት ዘለው ሲገላግሉ ይሞታሉ ፣ ሁለቱም ጠበኞች ያልተጣሉት ሰው ፊታቸው ሲወድቅ ያዩታል ። የተጣላው ቀርቶ ገላጋይ ይሞታል ። ይህ ሟች ስሜቱ እምቢ ብሎት ገብቶ ትንሽ መንገዱን አቋርጦ ትልቅ የሞት መንገድ ይጀምራል ። ፋኖ ፋኖ እየተባለ ሲዘፈንም የመለከት ድምፅ መቋቋም አቅቶት ዘሎ ጦር ሜዳ የሚገባ ፣ ቦምብ በደረቴ አመክናለሁ ብሎ እንዲሁ የሚቀር አለ ። እደሰታለሁ ብሎ አስቦ ከዝሙት ሞትን ያጨደ ሰው አለ ። እገሌ ከሌለ እኔም አልኖርም በማለት በኀዘን ራሱን ሰርስሮ ያነቀና የገደለ ብዙ ነው ። መኖር እየፈለገ የተፈጥሮ ግዳጅ ሆኖበት የሚሞት እልፍ ነው ። መኖር ሰልችቶት የመቀበሪያ ሳጥኑን ገዝቶ የሚጠብቅ ፣ የመቀበሪያ ፉካውን አሳምሮ የሚኖር አያሌ ነው ። ብዙ ዓይነት ሟቾች ቢኖሩም ሞት ግን አንድ ነው ። ሞት ሞት ቢሆንም ትርጉም የሚሰጠው አኗኗሩና አሟሟቱ ነው ። የሌላውን ሞት ቤዛ ላይሆን የወሰደ ፣ አድናለሁ ብሎ የሞተ ፣ በወኔ ያሸለበ ፣ በሞኝነት የወደቀ ፣ በግድ ያለፈ ፣ በቃኝ ብሎ ያንቀላፋ አለ ። የክርስቶስ ሞት ግን ከዚህ ልዩ ነው ። ወድዶ ፈቅዶ ሙቷልና በተባራሪ ከሞተው ልዩ ነው ። በስሜት ሳይሆን በዓላማ የሞተ ነው ። በወኔ ሳይሆን በፍቅር የታረደ ነው ። በሞኝነት ሳይሆን በዘላለም ጥበብ የተሠዋ ነው ። በግድ ሳይሆን ሊሞትልን በሥጋ የመጣ ነው ። መኖርን ሰልችቶ ሳይሆን የሚያሳሳ ዕድሜውን ለሰው የሰጠ ነው ።
ዓለም በበሽታ ፍርሃት ተውጧል ። እሞታለሁ ብሎ ተሸብሯል ። በካንሰርና በመኪና አደጋ በየቀኑ ብዙ ሕዝብ ይሞታል ። እሞታለሁ እያሉ መሞት ግን ከባድ ነው ። ሞትን ሺህ ጊዜ ማየት ብርቱ ነው ። በዚህ ሰዓት ለፍቅር ቦታ ላይኖረን ፣ ከሞት ድምፅ በላይ የፍቅርን ቅላፄ ሰምተን ሌሎችን ለመውደድ እንቸገራለን ። ጌታችን ግን ስለ እኛ ሊሞት በተቃረበበት ሰዓት የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው ። ከፋሲካው በዓል በፊት ከምሳሌውም ከአማናዊውም ፋሲካ በፊት ደቀ መዛሙርቱን ወደዳቸው ። ከመሥዋዕትነት በፊት ፍቅር ይቀድማል ፣ ብሉይና ሐዲስን ከማመስጠር በፊትም መውደድ ይቀድማል ። ለማንወደው ወገን ብንሞት እንኳ እያፌዝን ነው ። ፍቅር የሌለበት መሥዋዕትነት አያርግም ። በጌታችን ፍቅር ውስጥ ሦስት ነገሮችን ማውጣት እንችላለን፡-
1-  አስቀድሞ የወደደ ፤
2-  ዛሬም የወደደ ፤
3-  ለዘላለም የሚወድ ፤
ዛሬ በጣም የምንወዳቸው ሰዎች ትላንት በጣም እንጠላቸው ነበር ። ትላንት በጣም የምንወዳቸውን ሰዎች ደግሞ ዛሬ ጠልተናቸዋል ። የእኛ ፍቅር ትላንት ቢኖር ዛሬ ትዝታ ፣ ዛሬ ቢኖር ነገ ላይ ታሪክ ነው ። እርሱ ግን አስቀድሞ የወደደ ነው ። የሚወዳቸውን የወደደ ሳይሆን የወደዳቸውን የወደደ ነው ። ዛሬ የምንወዳቸው ሰዎችን አእምሮአችንን አስቀምጠን ልናውቃቸው አንፈቅድም ፣ ፈቃዳችንን አስቀምጠን ልንወስን አልቻልንም ። የዛሬው ፍቅራችን መሠረቱ ስሜት ነው ። ስሜት የጀበና ቱግታ ነው ። በትንሽ ውኃ ይበርዳል ፣ ወይም የተሸከመውን ሸክላ አቆሽሾ ፣ ራሱም አልቆ ይበርዳል ። የተሸከማቸውን የሚያቆሽሹ ዛሬ ማነስ ፣ ነገ ማለቅ ይከተላቸዋል ። ክርስቶስ ግን የወደደን አውቆን ነው ። አውቆን ብቻ ሳይሆን አውቆልንም ነው ። እኔ ልሙትለት እርሱ ይኑር ብሎ የወደደን ነው ። ነገ የምንወዳቸውን አናውቅም ። ይህች ጀምበር ብዙ ወዳጆችን ታሳጣናለች ። ክርስቶስ ግን ባልተጀመረ ነገ ፣ ባልታየ ነገ የሚወደን ነው ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ትላንት ይወዳቸው ነበር ። እንደ ሕፃን ሁለንተናቸውን ግልጥ ባደረጉበት ዘመን ፣ ሰማይን እየነገራቸው የእስራኤል መንግሥት በሚናፍቃቸው ትላንት ፣ የሚናገረውን ሳይሆን የሚመኙትን በሚሰሙበት ወራት ይወዳቸው ነበር ። ዛሬም በምሴተ ሐሙስ ግራ ተጋብተው ፣ ከይሁዳ ጋር ለመቍረብ ተሰናድተው ፣ ከአሥራ ሁለት ቍጥር ውስጥ አንድ ከዳተኛ አፍርተው ክርስቶስ ይወዳቸው ነበር ። ነገ ሁሉም በቆሙበት አቅጣጫ ቀኝ ወደ ኋላ ዙር ብለው ሲሮጡ ፣ ጴጥሮስ ሲክድ ፣ ይሁዳ ሲሸጥ ፣ ጴጥሮስ ሲጸጸት ፣ ይሁዳ ሲብስበት ፣ አንድ ቀን እንኳ ከክርስቶስ ጋር መቆም ሲያቅታቸው ፣ ከአሥራ አንድ ወዳጅ ዮሐንስ ብቻ እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ሲጓዝ  ጌታ ይወዳቸው ነበር ። የትላንትን አለማወቅ ፣ የዛሬን ስሜት ፣ የነገን ፈቃድ የታገሠና እንደገና የሰበሰባቸው ይህ ፍቅር ነው ።
መሞቱን ያወቀ ሰው ሊወድ ይቸገራል ። ዘመኑን መራራ ያደረጉትን ሰዎች ሞት ሳያይ በመሄዱ ያዝናል ። መሞት ብቻውን አፍቃሪ አያደርግም ። ወደ አብ እንደምንሄድ ስናውቅ እንዳፈቀርን እንሞታለን ። ዓለም ከነሣችን የአብ ፍቅር የሚሰጠን ይበልጣልና ። ክርስቶስ እንኳ በዚህ ዓለም የነበሩት ወገኖች ነበሩ ። ሁላችንም በዚህ ዓለም ላይ ጥሩ ወገኖች አሉን ፤ ፍጹም ወገኖች ግን የሉንም ። ሞት ወደ አብ የምንሄድበት ብርሃናዊ መንገድ የሆነው ከክርስቶስ ቤዛነት በኋላ ነው ። ጌታችንም በመስቀል ላይ የተናገረው የመጨረሻው ጩኸት፡- አባት ሆይ ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” የሚለው ነው ። /ሉቃ. 23፡46/ ። እስከዚህ ቀን ድረስ ሞት ነፍስ በዲያብሎስ እጅ የምትወድቅበት ነበረ ። ጌታችን ይህን አዋጅ በታላቅ ጩኸት ተናገረ ። የነፍስ አድራሻዋ በአፍቃሪው አብ እጅ ሆነ ።
የወደድናቸውን እስከ መጨረሻ መውደድ መልካም ነው ። ፍቅር ፌርማታ የለውምና ባንወርድ ጥሩ ነው ። አመስግነን ባንራገም ፣ የፍቅር ጦማር ጽፈን የሞት ደብዳቤ ባንቸከችክ መልካም ነው ። ከፍቅሩ ጋር የሚሞት ክቡር ነው ። ፍቅር ርቆን ልከኛ ጠብ እንደ ጽድቅ በሚታይበት በዛሬው ዘመን እስከ መጨረሻው መውደድን ከክርስቶስ መማር አለብን ። የተሰጠን ዕድሜ እንኳን ለጠብ ለፍቅር አይበቃም ። ይህን ጥቅስ በማንበብም በመዘከርም ባለንበት በዚህ ጊዜ እስከ መጨረሻ መውደድን ለልባችን መንገር አለብን ።
እስከ መጨረሻው ድረስ የወደደን አንድ አለ ። ከሰው ወገን የነገ ወዳጄ እገሌ ነው ብለን በእርግጠኝነት መናገር አንችልም ። እስከ ነገ የሚወደን አምላክ  ግን አለ ።
ጸሎት
ጌታዬ ሆይ ያንተ ፍቅር ምንኛ ውብ ነው ። አይቼ ልተነትነው ፣ ተመልክቼ ልጠግበው በፍጹም አልችልም ። ከሚሸጥህ ጋር እንጀራ የሚቆርስ ፣ ከሚክድህ ጋር ገበታ የሚቀመጥ ያንተ ፍቅር እንዴት ድንቅ ነው ። ድሀና ምስኪንን የማይጠየፍ ፣ ሰውን በልብስ የማይለካ ፣ የትላንት አለማወቅን ፣ የዛሬ ስሜትን ፣ የነገ ክዳትን በይቅርታ የሚያይ ያንተ ፍቅር ሰማያዊ ነው ። ኦ ያንተ ፍቅር ጠፍቼ የተገኘሁበት ፣ በትከሻ ላይ የተሳፈርኩበት ፣ የሞት ሸለቆን የተሻገርኩበት ነው ። ፍቅርህ ማልዶ አዲስ ነው ። የማይለመድ አዲስነት ነው ። ራሱን ለጠላ ዋስ ፣ ሰው ገሸሽ ላለው መደበቂያ ነው ። ኦ ያንተ ፍቅር እንደገና የተወደድኩበት እውነት ነው ። ይህ ፍቅርህ ይቆጣጠረኝ ። ለዓለም ሳይሆን ላንተ መገበር ይሁንልኝ ። እስከ መጨረሻው መውደድን አስተምረኝ ። ሳልደርስ ወረት አያውርደኝ ። በታዳጊው ፍቅርህ ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ 1
ሚያዝያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ