የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እነሆ፥ ክረምት አለፈ

እንኳን ከ2009 ዓ.ም ወደ 2010 ዓ.ም ከዘመን ዘመን በሰላም አሸጋገራችሁ !
“ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፡- ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቊርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ” /መኃ. 2፡10-13/ ።
ከተወደዱ የፍቅር ቅኔዎች አንዱ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ነው ፡፡ ቅኔ ስለሆነ እስካሁን ድረስ ፍቺውን ማወቅ ቀርቶ የመዝሙሩን አድራሻ ማወቅም አስቸግሯል ፡፡ ቅኔ በመንፈሳዊ ዓለም የምሥጢር ቁጥር ነው ፡፡ ቅኔን ለመረዳት መንፈሳዊ እውቀትና ማስተዋል ያስፈልጋል ፡፡ ጌታችን በምሳሌ ማስተማሩ ፣ ነቢዩ ዳንኤል ፣ ነቢዩ ሕዝቅያስ ፣ ነቢዩ ዘካርያስ እና ወንጌላዊው ዮሐንስ ራእይን በሥዕላዊ መንገድ ማየታቸው መንፈሳዊውን ምሥጢር ከኢአማንያን ለመወሰር ነው ፡፡ ጌታችንም “ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ”  ማለቱ ቃሉን በጥንቃቄ መያዝ እንዳለብን ያስረዳል /ማቴ. 7፡6/ ፡፡ ቅኔ ያለ ቦታው ማባከን ነው ፡፡ መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞንም ህብር የሆነ ፍቺ ያለው መዝሙር ነው ፡፡ መዝሙሩ በአንድ ወዳጅና በአንዲት ተወዳጅ መካከል ያለውን ምልልስ የያዘ ነው ፡፡ ይህ ወዳጅ ሁልጊዜ የሚወዳትን ውዱን ተነሺ ይላታል ፡፡ በፍቅር ዓለም ወንዶች የሚወዱት ንቁ ሴትን ነው ፡፡ ይህ ወዳጅ ግን የሚወዳት በሁሉ ነገር እየተኛች አስቸግራዋለች ፡፡ ስለዚህ በቁጣ ሳይሆን በፍቅር ድምፅ ይቀሰቅሳታል ፡፡ በወቅቱ መፈራረቅና በአትክልቱ መለምለም ልቧን ያነቃቃዋል ፡፡
ይህች ተወዳጅ የእያንዳንዳችን ነፍስ ስትሆን ወዳጅዋም ክርስቶስ ነው፡፡
ይህ ተወዳጅ ድምፁን እያሰማ ነው ፡፡ ይህ ወዳጅ የሚናገር ነው ፡፡ እርሱ ካልተናገረ ነፍስ አድራሻዋን ማወቅ አትችልም ፡፡ ስለ ራስዋም በዙሪያዋም ስለሚከናወነው ነገር አታውቅም ፡፡ ይህ ውድ የሚቀሰቅሳት  የሠራላትን ሥራ እያሳያት ነው ፡፡ በኀዘን ፣ በስብራት ውስጥ ተይዛ ወደ ውስጧም እያየች የምታነባዋን ነፍስ የወቅቱን መለወጥ ያበስራታል ፡፡ የአበቦችን ፍካት ፣ የወይኑን ማበብ ተመልከቺ ይህ ሁሉ እኮ ላንቺ ነው እያለ ይቀሰቅሳታል ፡፡ የእግዚአብሔርን መግቦት አለማስተዋል ትልቅ እንቅልፍ ነውና ተነሺ ይላታል ፡፡ ውበቴ ሆይ እያለ ይጠራታል ፡፡ እያንዳንዱ ምእመን የክርስቶስ መቅደስ ነውና በርግጥም ውበቴ ሆይ ይለናል ፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናትና ውበቴ ሆይ ይላታል ፡፡ በአገራችን ቋንቋ መልኬ ሆይ እያላት ነው ፡፡ ልጃቸውን መልኬ እያሉ የሚጠሩ ከመውለዳቸው በፊት ቆንጆ የነበሩ አሁን ግን ውበታቸው የረገፈባቸው ሰዎች ናቸው ፡፡ ስለ መልካቸው መርገፍ ብዙም አይጨነቁም ፡፡ ምክንያቱም ልጃቸውን አስገኝቷልና ፡፡ በቀራንዮ ውብ መልኩ ስለ እኛ ኃጢአት የረገፈው ክርስቶስም ውበቴ ሆይ ይለናል ፡፡ የእርሱ መጎሳቆል እኛን ወልዷልና ፡፡ ይህችን የተኛች ነፍስ የሚቀሰቅሳት በቀራንዮ ፍቅሩ ነው ፡፡
 ክረምቱ አለፈ ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ ይላታል ፡፡ ሰዎችን ያራራቀው ክረምት ፣ ከቤት መውጣትን የገታው የውኃ ሙላት ፣ ብርድና ጭጋግ የነበረበት ወራት አለፈ ፡፡ ፍርድ ቤቶችን ያዘጋው ፣ ፍትሕ ያሳጣው የወራቱ የሕይወትም ክረምት አለፈ ፡፡ ውበቴ ሆይ ተነሺ ፡፡ አዲስ ዘመን መጣ ፡፡ ያለፈውን የሚያስረሳ ቀን ተጨመረ ፡፡ ትላንት ላይ አትቆዪ ፣ ያልሆነልሽ ሳይሆን የሆነልሽን ተመልከቺ ፡፡ ውበቴ ሆይ ከብስጭት ፣ ከመጎዳት ስሜት ውጪ ፡፡ ከሰው የጎደለውን ሳይሆን ከእኔ የተሰጠሽን አስቢ ፡፡ ውበቴ ሆይ ከቂም ፣ ከበቀል ፣ ከቁጣ ወንበርሽ ተነሺ ፡፡ ያኛው ዓመት የእኔ አልነበረም አትበዪ ፡፡ ያንቺ የሆነው ብርሃን እየመጣ ነው ይላታል ፡፡ እውነተኛ ወዳጅ ብርሃን ያሳያልና የነፍስ ወዳጅ ክርስቶስ ለምስጋና ተነሺ ይላል ፡፡
ከላይ ዝናብ ፣ ከሥር ማጥ ፤ ከላይ በረዶ ከሥር ረግረግ የሆነበት መጠለያ ፣ መቆሚያ የጠፋበት ያ ክረምት አለፈ ፡፡ የሦስት ወር ጭጋግ በዘጠን ወር ብርሃን ተተካ ፡፡ ውበቴ ሆይ ስለማይመለሰው ትላንት ሳይሆን እየመጣ ስላለው ነገ ደስ ይበልሽ ፡፡ ከክረምቱ በረዶ የተነሣ ውበታቸውን የሸሸጉት አበቦች መስኩን እያለበሱ ነውና ውበቴ ሆይ ይህ ሁሉ ላንቺ ነውና ተነሺ ፡፡ አበባን በብርጭቆ እንጂ በሜዳ የሚዘረግፍ ወዳጅ ከቶ የለም ፡፡ እኔ ውድሽ ግን በዝርግፍ አበባ ፣ መስኩን በሞላው ቁንጅና እየጠበኩሽ ነው ፡፡ ራስሽን ካሰርሽት ጠባብ ጎጆ ፣ ዓለም ይህ ብቻ ናት ካልሽበት ስንጥቅ ዓለት ውጪና ያዘጋጀሁልሽ አስደናቂ ነገር ተመልከቺ ፡፡ አንቺ ስታዝኚ እኔ ደስ አይለኝም፡፡
 የዜማ ጊዜ ደረሰ ፡፡ የተሰደዱ ወፎች ፣ ክረምቱ ያሸሻቸው እነዚያ ወዳጆች ተመልሰው ሊመጡ ነው ፡፡ ማታ ያለያየውን ሰው ቀን ያገናኘዋልና ውበቴ ሆይ ተነሺ ፡፡ የሄዱ የሚመጡበት ፣ ያስለቀሱ የሚያዜሙበት ጊዜ ደረሰ ፡፡ በራሳቸው አልመጡም ፣ እኔ ላንቺ የሠራሁልሽን ብርሃንና ደስታ ሲያዩ ይኸው መጡ ፡፡ የቁርዬዎች ድምፅ ተሰምቷል ፡፡ ወታደራዊ ማርሹ አስተጋብቷል ፣ ንጉሥሽ መጥቷልና ውበቴ ሆይ ከጭጋጋማው ስሜት ውጪ፡፡ በለሱ እየጎመራ ነው ፡፡ ክርስቲያኖች በአዲስ ፍቅር የሚነቃቁበት ዘመን ደረሰ ፡፡ አፍንጫን የሚማርከው የአበቦች መዓዛ ፣  ልብን ደስ የሚያሰኘው ሽታ እየመጣ ነው ፡፡ ውበቴ ሆይ ተነሺ ፡፡ ውድሽ ክረምትን በበጋ ፣ ሌሊትን በቀን ፤ ኀዘንን በደስታ የሚለውጥ ነውና ውበቴ ሆይ ተነሺ ፡፡ እኔ ብዙ እያለኝ አንቺን እፈልጋለሁ ፤ ማንም የሌለሽ አንቺ ሆይ እኔን ፈልጊኝ ፡፡ በወቅቱ ፣ በፍጥረቱ ፣ በትልቅ ፣ በትንሹ እኔ እታያለሁ ፡፡ እንዳትታወኪም በቀኝሽ ቆሜአለሁ ፡፡ ማንም የማይሰጠውን ዘመን ይኸው ሰጥቼሻለሁ ፡፡
“እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ ።…የዜማም ጊዜ ደረሰ ።”
     
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ