መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » እኔው ነኝ

የትምህርቱ ርዕስ | እኔው ነኝ

ተስፋ የሚያስቆርጡ ውሎዎችና ሰዎች ጋር ውዬ ተስፋ የምቆርጥ እኔው ነኝ ። የሚፈልጉኝን ትቼ የማይፈልጉኝን ሳሳድድ ፣ ነፋስን ለመጨበጥ የምሮጥ እኔው ነኝ ። የውስጤን የውስጥ ላልሆነ ሰው ነግሬ ምሥጢሬን የምዘራ እኔው ነኝ ። ያለ መንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊነትን የምሻ ፣ በምድራዊ ፍልስፍናና ልምምድ ክርስቲያን ለመሆን የምሻ እኔው ነኝ ። የተከፈቱ ደጆች ሳሉ የተዘጋ በር በመደብደብ እጄን ያቆሰልሁ እኔው ነኝ ። ድሀ ላይ መዝራት ሲገባኝ ገንዘብን እየበተንሁ ፣ በአልባሌ ነገር የምከስር ብኩን እኔው ነኝ ።

ሁሉም የእኔ ይሁን ብዬ ከሁሉ ጋር የምጣላ ፣ ሁሉም የእኔ ካልሆነ ብዬ እርካታዬን ጽንፍ ላይ የወረወርሁ እኔው ነኝ ። በደካሞች ፈርጄ እነርሱ በወደቁበት ገደል ገብቼ ፣ ራሴን መሳቂያ ያደረግሁ እኔው ነኝ ። ዓመቶቼን በከንቱ እያሳለፍሁ ዘመኔ ተቃጠለ የምል ፣ የዕድሜዬ ፀር እኔው ነኝ ። ወደሚረዳኝ ጌታ ሳይሆን ወደዚህ ዓለም ጌቶች እጄን ዘርግቼ ማመኔን ከንቱ ያደረግሁ ፣ ባዶ እጄንም የተመለስሁ እኔው ነኝ ። ያልበላቸውን ሳክክ ፣ ከማስደሰት ያሳዘንኩኝ ፣ በማያገባኝና ባልጋበዙኝ በሰው ነገር ዘው ብዬ በመግባት የዳከርኩኝ እኔው ነኝ ። በይሉኝታ የምረክስ ፣ ሰው እንዳይቀየመኝ ብዬ የምሞት ፣ ዓላማ ቢስ እኔው ራሴ ነኝ ። ለራሴ ፋታ ነሥቼው ከመድከሜ የተነሣ ፣ ደቃቁ ነገር ተራራ ሁኖ የሚታየኝ በወኔ ብቻ የቆምሁ እኔው ነኝ ።

በራሳቸው እንዳይቆሙ አድርጌ ፣ ልጆቼን የምወቅስ ፤ መድረኩን ሳልለቅ ከመድረክ የራቁትን የምከስስ ግራ የተጋባሁ ፍጡር እኔው ነኝ ። እግዚአብሔር ያላሸከመኝን ሸክም ተሸክሜ የምንገዳገድ ፣ አጋዥ ያጣሁ እኔው ነኝ ። መከራ ሳይመጣብኝ ወደ መከራ ሄጄ አምላኬን የማማርር ዓይነ ደረቅ እኔው ነኝ ። ሰዎችን መርዳት እንጂ ማስደሰት የእኔ አለመሆኑን ዘንግቼ ሲከፉ የምከፋ እኔው ነኝ ። ኀዘኔን ገደብ ሳልሰጠው መደሰት የሚያምረኝ ፣ በሥልጣነ እግዚአብሔር እየገባሁ ከራሴ ጋር የምጣላ ፣ ለሰው የመከርሁትን ለራሴ መኖር ያቃተኝ እኔው ነኝ ። የማይገባ ፍላጎት ውስጥ እንዲገቡ አነሣሥቼ ሰውን የምታዘብ ፣ የጀመርኩትን ለምን ፈጸሙት ብዬ የምበሳጭ አስመሳይ እኔው ነኝ ።

ሕልሜን ለአጨናጋፊዎች አውርቼ ጠላት በዛብኝ የምል ፣ ሳይሞቅ እንዲፈላ የምመኝ እኔው ነኝ ።

እኔን ከራሴ ታድነኝ ዘንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ቶሎ ና !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ነሐሴ 4 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም