የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንሄዳለን

“አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ።” ዘፍ. 15፡15 ።

“አንተ ግን” የሚለው ሌሎች ወደ አባቶቻቸው በሰላም እንደማይሄዱ ፣ በመልካም ሽምግልና እንደማይቀበሩ ያሳያል ። ሞታቸው ሕይወት የሚሆንላቸው ቅዱሳን እንዳሉ ሁሉ ሞታቸው ሞት የሚሆንባቸው ኃጥአን አሉ ። ዐረፈ ብለን የምንናገርለት ሟች ካለ አሳራፊውን እግዚአብሔር ያመነ ብቻ ነው ። ከመቃብር ባሻገር ያለውን ትንሣኤ ፣ ከሞት ወዲያ ያለውን ሕይወት ለማሰብ ሃይማኖት ያስፈልጋል ። የቤተ ሙከራ መነጽሮች ፣ ዘመናዊ ማክሮስኮፕ መሣሪያዎች ሰማይን አያሳዩም ፣ የእምነት መጽሔት/ መስተዋት ግን ሰማይን ያሳያል ። ሞት ጠቃሚ የሚሆንለት ክርስቶስ ሕይወት ለሆነለት ሰው ነው ። ለዚህ ነው ሐዋርያው፡- “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና” ያለው ፤ ፊልጵ. 1፡21 ። በሞታችን ቀን የሚነበበው የሕይወት ታሪክ ፣ የሰዎች ምስክርነት በሰማይ ግልባጩ አይላክም ። በዕድሜአችን የሬሳ ክፉ አይተንም ፣ ሰምተንም አናውቅም ። ሁሉም ሟች ቀና ብሎ የሕይወት ታሪኩን ቢሰማ “እኔን ነው ወይ?” ብሎ ይገረም ነበር ። ይልቁንም በአገራችን በሕይወት ያለውን ጻድቅ ስሙን መበከል ፣ የሞተውን ኃጥእ ደግሞ ስሙን መቀደስ እንወዳለን ። በአጭር ቃል የሬሳ ፍቅረኞች ነን ።

አባቶቻቸው ቅዱሳን ወዳሉበት ፣ ወደ ህፅነ አብርሃም/ የአብርሃም እቅፍ ያልሄዱ ብዙ ወገኖች አሉ ። አብርሃምን በሥጋ ልደት ሳይሆን በሃይማኖት በመዛመድ ወደ አባቶች መሰብሰብ ይቻላል ። አብርሃም እንዲያ አምኖ ፣ ዘሮቹ ግን ክርስቶስን ሰቅለውታል ። እርሱ በምሳሌ ያገለገለውን እነርሱ በአካል አግኝተው ገድለውታል ። ጽድቅ የዘር ውርስ ሳይሆን ውሳኔ እንደሆነ እናያለን ። ደግ ፣ ደግ ላይወልድ ይችላል ። የልበ አምላክ የዳዊት ልጆች እነ አምኖን ፣ እነ አቤሴሎም ናቸው ። የደጉ ሕዝቅያስም ልጅ ፣ እጅግ ክፉ የነበረው ምናሴ ነው ። ክፉም ደግ ሊወልድ ይችላል ። በደለኛው አዳም ጻድቁን አቤልን ወለደ ፣ ጣዖት ጠራቢው ታራ አብርሃምን ወለደ ።

በሰላም መሄድ ያልቻሉ አባቶች አሉ ። ሎጥ ከሰዶም እሳት አምልጦ በመጠጥ ምክንያት ከልጆቹ ወልዷል ። ከእርሱ የተወለዱትም የእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላት የነበሩት አሞንና ሞዓብ ናቸው ። እነዚህ ወደ እግዚአብሔር ጉባዔ እንዳይገቡ የተከለከሉ ናቸው ። ሕዝቅያስ ለእግዚአብሔር አምልኮ ቀንተው ጣዖታትን ከተዋጉ ነገሥታት ተርታ የሚመደብ ፣ የእነ ዳዊትና የእነ ኢዮስያስ የምግባር እኩያ ነው ። በመጨረሻ ግን እስራኤል ለባቢሎን ምርኮ የተዳረገችበትን ስህተት ሠራ ። ስህተቱና ውጤቱ በተነገረው ጊዜ፡- “ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፦ የተናገርኸው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው አለው። ደግሞም፦ በዘመኔ ሰላምና እውነት የሆነ እንደ ሆነ መልካም አይደለምን? አለ።” 2ነገሥ. 20፡19 ። መልካም ነው ያለው የባቢሎን ምርኮን ነው ፣ በእኔ ዘመን አይሁን እንጂ ምን ቸገረኝ ? አለ ። ለትውልድ አስቦ አምልኮ ጣኦትን ያራቀ ፣ አሁን ትውልድ ገደል ይግባ ብሎ ፈረደ ። በሰላም መሄድ ማለት በአልጋና በጦር ሜዳ መሞት ላይሆን ይችላል ። በእምነት ክብር ጸንቶ ማለፍም ነው ። ከሐዋርያት አንዱም በአልጋው ላይ አልሞተም ። በእሳት ተጠብሶ ፣ በዘይት ተቀቅሎ ፣ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ፣ በሰይፍ ተመትሮ ያለፈው ብዙ ነው ።

መሄድ የሚለውን ቃል ስንሰማ ሞት መንገድ ፣ ጉዞ ተብሎ ተጠርቷል ። በአየር ማረፊያ ብዙ ሸኚ አለ ። መለየት ከባድ ነውና ወዳጅ ሁሉ ይሸኛል ። የሞት ትርጉሙም መለየት ማለት ነው ። መጥፋት አይደለም ። የኑሮና የዓለም ለውጥ ነው ። በሞታችን ሰዓትም ብዙ ሸኚ አለ ። አንድ ጠያቂ ያጣው ታማሚ ፣ ሬሳ በሆነ ጊዜ ሺህ ሰው ይሸኘዋል ። በቁማቸው ሰው የናፈቃቸው ችግረኞች “ስሞት አትቅበሩኝ” ብለው ይናገራሉ ። ቀብር ለጤናና ለሕሊና ካሣ የሚከፈል ነው ። ለሰውዬው ግን የሚጠቅመው በቁሙ አለሁልህ ማለት ነው ። በአየር ማረፊያዎች ለጊዜው ለሚለያቸው ሰው እንባ ያፈስሳሉ ። ነገ ሞተን በሰማይ ለምናገኘው ሰው ዛሬ በሞቱ እናለቅሳለን ። ፊትና ኋላ መሆን እንጂ ቀሪ የለም ። የምናለቅሰው ስለቀደሙን እንጂ እኛ ቀሪ ስለሆንን አይደለም ። በአየር ማረፊያው የሚለቀስለት መንገደኛ ሩቅ አገር የሚሄድ ነው ። እንደ ሞት ያለ ሩቅ መንገድ የለም ። ሞት እስከ ዕለተ ምጽአት ይግባኝ የለውም ። አልአዛር ቢነሣም እንደገና ሙቷል ። ሞት ከሌለ ትንሣኤ አይነገርምና ። ደግሞም አያስፈልግም ።

ሞት ብዙ ትርጉሞች ተሰጥተውታል ። መሄድ ፣ መሰብሰብ ፣ ማንቀላፋት ፣ መዘራት ፣ መከማቸት … የሚሉ መጠሪያዎች አሉት ። የሚገርመው በብሉይ ኪዳን ይህን ፍቺ ማግኘቱ ነው ። ብሉይ ኪዳን ትንሣኤ ሙታንን ያምናል ። አዲስ ኪዳን አዲስ ትምህርት አላመጣም ። በማን ሥልጣን እንደምንነሣ ግን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ እርግጥ ሆነ ። አልነሣም ብሎ የሚያምን ካለ ክርስቶስ ከሞት አልተነሣም ብሎ መካዱ ነው ። ሞት መሄድ ነው ። ያለ መንገድ መድረስ የለም ። ያለ ሞትም ሰማይን ማየት አይቻልም ። ሞት መሰብሰብ ነው ፣ የተዝረከረከው ሰው ሽክፍ የሚልበት ነው ። ብዙ በሽታዎች መድኃኒት የላቸውም ይባላል ፣ ሞት ግን መድኃኒትና ዕረፍት ነው ። ሞት ማንቀላፋት ነው ። ማታ የተኛ ጠዋት ይነሣል ። እንደሚነሣ እርግጠኛ ሁኖ ቀጠሮ ይይዛል ። ሞት ማታ ነው ፣ ትንሣኤ ጠዋት ነውና እንነሣለን ። ከወዳጆቻችን ጋርም እንገናኛለን ። በሰማይ መተዋወቅ አለ ። መተዋወቁ ደግሞ ኃጥእ ነፍስም የሚያውቅበት ነው ። ነዌ ተባለው ባለጠጋ አብርሃምን በዓለመ ነፍስ አውቆታል ። በሰማይ ያሉ ቅዱሳንም በምድር ላይ የሚከናወነውን ነገር ያውቃሉ ። /ሉቃ. 16፡24፤ ራእ. 6፡10/ የምንሞተው ለመላቅ እንጂ ለማነስ አይደለም ። የሥጋ መጋረጃ ሲገፈፍ ሁሉም ነገር ግልጽ ይሆናል ።

መንገደኛ ስንቅ ያስፈልገዋል ። እኛም አንድ ቀን ዓለም ከኋላዬ ፣ ክርስቶስ ከፊቴ ብለን ጉዞ እንጀምራለንና ስንቅ ያስፈልገናል ። እርሱም ንስሐና የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው ።

“በሉ እናንተም ሂዱ ፣ እኛም ወደዚያው ነን
ወትሮም መንገደኛ ፊትና ኋላ ነው” ተብሏል ።

“ሞት ይቅር ይላሉ ፣ ሞት ቢቀር አልወድም ፤
አፈሩም ድንጋዩም ከሰው ፊት አይከብድም” አለ ፣ አግኝቶ ያጣው ሰው ።

በምድር ላይ የሚቀር ሰው እንደሌለ ያወቀው ደግሞ፡-

“እኔስ ፍረድ ቢሉኝ ሞት በደለኛ ነው ፣
አንድ ሰው ለምስል ቆሞስ ቢቀር ምነው” ብሏል ።

ያጋሩ