የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

‹‹እንሻገር››


የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…….ዓርብ ጳጉሜን ፮ /፳፻፯  ዓ.ም
                                           (ማቴ. 8&23-34)፡፡
ንጉሡ ባሕታዊውን፡- ‹‹አባቴ ዘመኑ ምን ይመስላል?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ባሕታዊውም ሲመልሱ ‹‹ዘመኑ አንተን ይመስላል›› አሉት፡፡ ንጉሡም፡- ‹‹እንዴት?››  ቢላቸው ‹‹ደግ ከሆንህ ዘመኑ ደግ ነው፤ ክፉ ከሆንህ ዘመኑ ክፉ ነው›› አሉት ይባላል፡፡ አዎ ዘመን የራሱ መልክ የለውም፡፡ በራሱ ክፉና ደግ አይደለም፡፡ ዘመን የእኛን መልክ የሚያሳይ መስተዋት ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአንድ ወቅት፡- ‹‹ከአሁኑ ዓመት ያለፈው ዓመት ይሻል ነበር አትበሉ፤ ያለንበትንና የምንኖርበትን ዘመን በእግዚአብሔር ፈቃድ  የተሻለ የምናደርገው እኛ ነን›› ብለዋል፡፡ አብርሃም ሊንከንም በጊዜ ውስጥ የሚለዋወጠውን የሕይወት ሂደት ሲገልጥ፡- ‹‹ቀን ወዳጅህን ጠላት እንዳደረገብህ ያው ቀን መልሶ ጠላትህን ወዳጅ ያደርገዋልና ታገሥ›› ብሏል፡፡ የአገራችንም ሰው፡- ‹‹ቅዝምዝምንና የቀን ሰባራን ጎንበስ ብለው ያሳልፉታል›› በማለት የትሕትናን ክብር ይገልጣሉ፡፡ በጎውም ሆነ ክፉው የሕይወት ገጠመኝ በቀን ውስጥ የሚፈጸም ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን የቀኑ ባለቤት ነው፡፡ ሰውም የቀን ጌታ እንጂ ቀን የሰው ጌታ እንዲሆን አልተፈጠረም፡፡ ቀን ቢያዙበት ታማኝ ሎሌ ነው፡፡ ዘመን ቢሠሩበት መልካም ገበያ ነው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን፡- ‹‹እንሻገር›› አላቸው፡፡ በመሻገር የበለጠ ሊያሳያቸው፡፡ ማቴዎስ ‹‹እንሻገር›› የሚለውን ቃል አልመዘገበልንም፣ ተአምራቱን ግን መዝግቧል፡፡ ማርቆስ ግን፡- ‹‹በዚያም ቀን በመሸ ጊዜ፡- ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው›› (ማር. 4፡35) በማለት ጽፎልናል፡፡ በክረምት ማንም ሰው መሻገር አይፈልግም፤ በምሽትም ባሉበት መቅረት እንጂ መሻገር ማንም አይሻም፡፡ ጌታችን ግን፡- ‹‹…በመሸ ጊዜ ወደ ማዶ እንሻገር አላቸው፡፡›› ከቀን ምሽት የዘመን ምሽት ይከብዳል፡፡ መኖር አያስመኝም፡፡ ምንም ዘመን ቢከፋ ከጌታ ጋር መሻገር ግን ብዙ ተአምር ያሳያል፡፡
መሻገርን መርጠው በታንኳ እንደ ተሳፈሩ ብርቱ ማዕበል ገጠማቸው፡፡ ከዚህስ ፈተና አለመኖር ጥሩ ነው የሚያሰኘው አስቸጋሪ ሰዓት መጣ፡፡ ቢሆንም ሕይወት በችግር አትወሰነም፡፡ ሌላው የአካል ክፍል ቢቆረጥ መኖር ይቻላል፤ ከአንገት በላይ ተቆርጦ ግን መኖር አይቻልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስም የሕይወት ራስ ነው፡፡ ያለ እርሱ ብቻ መኖር አይቻልም፡፡ ደቀ መዛሙርት በማዕበል ስጋት ሲንገላቱ ጌታ ግን በታንኳ ውስጥ ተኝቶ ነበር፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የአድነን ጥሪ ሲያሰሙ መጀመሪያ የጥርጣሬአቸውን ማዕበል ገሰፀ፤ ከዚያም ማዕበሉን ፀጥ አሰኘ (ማቴ. 8&23-27)፡፡
ከታንኳም እንደ ወረደ በአስከፊ ሁኔታ በአጋንንት የተያዘ ሰው አገኘ፡፡ ይህን የመቃብር ሰው ከዘመናት እስራት ፈታውና ከሰው ጋር ቀላቀለው (ማር. 5&1-20)፡፡ የጌርጌሴኖኑ እብድ እንደ ተፈወሰም ኢያኢሮስ የሚባል የምኩራብ አለቃ ልጄ ልትሞት ነውና ድረስልኝ አለው፡፡ ኢየሱስም ልጁን ሊያድንለት ወደ ቤቱ ሲሄድ ለአንዲት መከረኛ ሴት ጉዞውን አዘገየው፡፡ ይህችም ሴት ዐሥራ ሁለት ዓመት ያለ ማቋረጥ ደም ይፈሳት የነበረች ሴት ናት፡፡ ለሐኪም ገንዘቧን ሁሉ ጨርሳ ልትድን አልቻለችም፡፡ አሁን ግን የኢየሱስን ልብስ ነክታ ተፈወሰች (ማር. 5፡21-34)፡፡
ወደ ኢያሮስ ቤት ሲገቡ ልጅቱ  ሞታ አልቃሾች ሙሾ እየተቀባበሉ ያሟሹ ነበር፡፡ የሞተችዋን እንደ እንቅልፍ ቀስቅሶ ዝማሬ ሰጣቸው (ማር. 5&35-43)፡፡ እርሱ ብቻ ለሞተው ነገር ሕይወት መስጠት ይችላል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ፡- ‹‹እንሻገር›› ሲላቸው ‹‹አይ ምሽት ነው›› ቢሉ ኖሮ ይህን ሁሉ ተአምር ለማየት ባልታደሉ ነበር፡፡ ከጌታ ጋር መሻገር በመፍቀዳቸው ግን ማዕበል ሲታዘዝ፣ የመቃብሩ ዕብድ ከሰው ቁጥር ሲደመር፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት የፈሰሰው ደም ሲቆም፣ የሞተችው ብላቴና ስትነሣ አዩ፡፡
እኛስ ዘመኑን በመፍራት ሞትን እየለመንን ይሆን? ያመኑት ሲክዱ የእኛ መጨረሻ አስደንግጦን ይሆን? ከማያቋርጠው የሕይወት ትግል የተነሣ በሞቱት ወገኖቻችን ቀንተን ይሆን? ከጌታ ጋር እንሻገር ብዙ ድንቅ እናያለን፡፡ አዎ ችግሮች ያልፋሉ፡፡ ጠንካራ ሰዎች ግን አያልፉም!!
ያሳለፍነው ዓመት ትዝታው ምንም ይሁን፡፡ ማዕበል ያለበት፣ ለሰሚው ጭው የሚያደርግ፣ ጥበበኞች የማያውቁት፣ ዘመዶችም የተዘጋ ፋይል ነው የሚሉትም ይሁን፡፡ ደቀ መዛሙርቱ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ሕያው ሆነው መሻገርን ፈለጉ፡፡ የበለጠም አዩ፡፡ ለእግዚአብሔር ተአምር አንሠራለትም፤ የሚሠራውን ተአምር ለማየት ግን እንኖራለን፡፡ ስለዚህ ከጌታ ጋር እንሻገር!!  
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ