የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እንኳን ለ2016 ዓ.ም. ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ !

ድንግል ሆይ !

ሰው አምላክ መሆን አይችልም ። ሰው አምላክ ለመሆን ፈለገ ፣ ነገር ግን ሞትን አመጣ ። አምላክ ግን ሰው መሆን ይችላል ። አምላክ ሰው ሆኖ ሰውን አምላክ አደረገው ። ሰው በዕፀ በለስ አምላክ ለመሆን ፈለገ ። በዕፅ ያልተገኘን አምላክነት በዕፅ ፈለገው ። አዳም በዕፀ በለስ አምላክነትን ሲፈልግ ፣ አምላክ አምላክነትን ያገኘው በቅጠል ነው ብሎ ማመኑ ነው ። በዚህም እግዚአብሔርን ተዳፈረ ። በቅጠል ያልተገኘ አምላክነትን በቅጠል መፈለግ ትርፉ ውርደት ነው ። ቅጠል ሐሰተኛ ትልቅነትን ያመጣል ። ዛሬም አደንዛዥ ዕፁ ያልሆኑትን እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል ። ድንግል ሆይ አምላክነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ፣ በኃይል የሚነጥቀው የሌለ ፣ በፈቃዱ ለሰው አምላክነትን የሰጠ እርሱ ቡሩክ ነው ። ቃል ሥጋ ሆነ ። አምላክ ሰው ሆነ ። አምላክ ሰው ነው አይባልም ። በሁነት/በመሆን ግን አምላክ ሰው ሆነ ። አምላክ ሰው በመሆኑም ሰው አምላክ ሆነ ። ድንግል ሆይ ይህን ባየሽ ጊዜ የሰው ሩጫ በልብስ እሳትን ለመጫር ፣ በዋሻ ፀሐይን ለማሰር መሞከር አይደለም ወይ 

አምላክ የእርሱ ያልሆነውን ሰውነት ገንዘብ ባደረገ ጊዜ ፣ ሰውም ከተዋሕዶ የተነሣ የእርሱ ያልሆነውን አምላክነት ገንዘብ አደረገ ። የምድር ገዥው አዳም ፣ በበደሉ እርሱንም አጣ ። በተዋሕዶ ግን በሰማይና በምድር ሥልጣን አገኘ ። የከበረው ጥቁር ወይም ነጭ የሰው ዘር ሳይሆን መለኮት የተዋሐደው ባሕርየ ሰብእ ነውና ሰው የአምላክ ዘመድ ሆነ ። ዛሬ በመቃብር ሥጋችንን ብናየው ፣ በሥላሴ ዙፋንም እያየነው ነው ። “ትንሽ ሥጋ ከመርፌ ትወጋ” እንዲሉ መለኮትም ሥጋን ለዘላለም በመቃብር አይተወዉም ። ሙሴ ከቤተ መንግሥት ተሰድዶ ልዑል መባልን አስቀምጦ በኮሬብ ተገኘ ። የልዑል አብ ልጅም ክብሩን ትቶ መጣ ። ክብሩን አላጣም ። ክብሩን ሸፍኖ በሥጋ ትሕትና ተገለጠ ። ልዑል በዚህ ምድር ተሰደደ ፣ ሙሴ በወገኑ ቅንዓት ክርስቶስም በሰው ልጆች ቅንዓት ይህን አደረገ ። ሙሴ በደብረ ኮሬን ለቀናለት ሕዝብ የነጻነት ዜና ሰማ ፣ ክርስቶስም በደብረ ቀራንዮ ለቀናለት የሰው ልጅ ድኅነት አመጣ ። እርሱ በዚህ ልክ ዝቅ ካላለ እኛ ከፍ ማለት አንችልም ። የሰው ብልሽት አያል ነውና የሠራው እጅ ካልሆነ ማንም አያበጀውም ። ሰው ዘመደ አምላክ በመሆን ዳነ ። ድንግል ሆይ ለዚህም ድልድይ እንድትሆኚ የተመረጥሽ አንቺ ነሽ !

ምስጋና በመቅደስ ፣ ምስጋና በሰማይ ይሰማ ነበር ። አሁን ግን በማኅፀንሽ የምስጋና አደባባይ ተሠራ ። ሰማይን ለማየት ቀድሞ ቀና ማለት ይገባ ነበር ፣ አሁን ግን ዝቅ ብለሽ የመላእክትን ምስጋና ሰማሽ ። ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ የሚገባባት ኅቱም መቅደስ አንቺ ነሽ ። ሊቀ ካህናት ክርስቶስ በገባበት ማኅፀንም ፍጡር ሊቀመጥ አይችልም ። የወልድ እናቱ ፣ ወላዲተ አምላክ ተብለሽ የምትጠሪ ፣ ሁሉን አጥተሸ ሁሉን ያገኘሽ ፣ በነፍስሽ ሰይፍ አልፎ እሞሙ ለሰማዕታት የተባልሽ አንቺ ነሽ ። ድንግል ሆይ ልጅሽን በወለድሽ ጊዜ የተሰማሽ ደስታ በእኛም በምንወድሽ ይደርብን ! አሜን !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ